1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተራዘመው የሶማሊያ ምርጫና መዘዙ 

ረቡዕ፣ የካቲት 3 2013

በበርካታ ችግሮች የተተበተበችው ሶማሊያ በጎርጎሪዮሳዊው የካቲት 8 ቀን 2021 ልታካሂድ የነበረውን ምርጫ አራዝማለች። ይህም በሀገሪቱ የፖለቲካ አለመረጋጋት እንዳያስከትል ስጋት አሳድሯል። የፕሬዝዳንት ሞሃመድ አብዱላሂ ሞሃመድ የሥራ ዘመን ያለፈው ሰኞ በመጠናቀቁም የተቃዋሚ ፓርቲዎች ከአሁን በኋላ ለፕሬዚዳንቱ ዕውቅና እንደማይሰጡ እየገለፁ ነው።

https://p.dw.com/p/3pBJS
Somalia Mogadischu Parlament
ምስል STRINGER/AFP/Getty Images

«የተመድ የፖለቲከኞች ውይይት እንዲደረግ ጠይቋል»

በበርካታ ችግሮች የተተበተበችው ሶማሊያ ያለፈው የካቲት 8 ቀን 2021 ልታካሂድ የነበረውን ምርጫ አራዝማለች።ይህም በሀገሪቱ የፖለቲካ አለመረጋጋት እንዳያስከትል ስጋት አሳድሯል። የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ሞሃመድ አብዱላሂ ሞሃመድ የስራ ዘመን ያለፈው ሰኞ በመጠናቀቁም የተቃዋሚ ፓርቲዎች ከአሁን በኋላ ለፕሬዚዳንቱ ዕውቅና እንደማይሰጡ እየገለፁ ነው። 

ያለፈው የካቲት 8 ቀን ተቆርጦለት የነበረው የሶማሊያ ምርጫ ከተራዘመ ወዲህ በፖለቲካ አመራሮች መካከል እየታዬ ያለው መከፋፈል ሀገሪቱን ወደተራዘመ የፖለቲካ ቀውስ ሊወስዳት ይችላል የሚል ስጋት አሳድሯል።  ምርጫው ሳይካሄድ የቀረው የማዕከላዊ መንግስት እና የፌደራል መንግስታት በድምጽ አሰጣጡ ሂደት ላይ መስማማት ባለመቻላቸው ሲሆን፤ ጉዳዩን የበለጠ ያወሳስበው ደግሞ በጎሳ ላይ የተመሠረተውና 4 ነጥብ 5 ተብሎ የሚጠራው የሀገሪቱ ልዩ የምርጫ ሥርዓት ነው ተብሏል፡፡ቀጥተኛ ባልሆነው በዚህ የምርጫ ሥርዓት ከመላ ሀገሪቱ የመጡ የጎሳ ተወካዮች የፓርላማ አባላትን ይመርጣሉ።ለታህታይ እና የላዕላይ ምክር ቤቶች የተመረጡ የፓርላማ አባላት ደግሞ የሀገሪቱን ፕሬዚዳንት ይመርጣሉ፡፡ 
የአፍሪቃ ቀንድ የፖለካ ተንታኝ ማቲው ብሬደን እንደሚለው ይህ የጎሳ ስርዓት እኩል እድል የሚሰጥ አይደለም። 
«4.5 ተብሎ በሚጠራው ስርዓት በፓርላማው አራቱ ዋና ዋና ጎሳዎች እኩል አናሳ ጎሳዎች ደግሞ ግማሽ ቦታ ይሰጣቸዋል። ያ ማጋራት በተወሰነ ደረጃም በሥራ አስፈፃሚዎቹ እና በሌሎች የመንግሥት አካላት ይዘልቃል ፡፡» 
በመሆኑም፤ይህ ሥርዓት በተራ ዜጎችም ሆነ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ በስፋት እየተተቸ ነው። ከሞቃዲሾ፤ የዩኒቨርሲቲ መምህርና የፖለቲካ ተንታኝ የሆኑት ነጂብ አብዱቃድር በየአራት ዓመቱ የሶማሊያን ህዝብ የወደፊት እጣ ፈንታ በጥቂት ግለሰቦች መወሰኑ አሳዛኝ ነው ይላሉ። 
«ምርጫው እውነተኛ ምርጫ ሳይሆን ያለተፎካካሪ መምረጥ ነው ።ይህንን የጎሳ ስርዓት ለብዙ ዓመታት ስንጠቀምበት ቆይተናል።ነገር ግን ፖለቲከኞቹ ከዚህ ስርዓት ለመላቀቅና ህዝባዊ ምርጫ ለማካሄድ ፈቃደኞች አይደሉም ፡፡ የሶማሊያ ህዝብ መብት አለው እናም በአንድ ሰው አንድ ድምፅ ምርጫ ድምፁ እንዲሰማ ይፈልጋል ፡፡ » 
በሶማሊያ የአንድ ሰው ፣ የአንድ ድምፅ ቀጥተኛ ምርጫ በፖለቲካ እና በፀጥታ ጉዳዮች ሳቢያ የተተዉ ሲሆን በሀገሪቱ ለመጨረሻው ጊዜ በቀጥተኛ የህዝብ ድምጽ ምርጫ ያካሄደችው በጎርጎሪያኑ 1969 ዓ/ም ነበር። 
በሌላ በኩል ለሀገሪቱ የፖለቲካ መረጋጋት ሕገ-መንግስቱ ውስጥ ያሉ ክፍተቶች መፍትሄ ያስፈልጋቸዋል የሚሉ አሉ።የሶማሊያ ህገ-መንግስት ለአገር ህልውና ፣ለዜጎች መብትና ግዴታዎች እንዲሁም የመንግስት አወቃቀር ሕጋዊ መሠረቶችን አስቀምጧል።የአፍሪካ ቀንድ የፖለቲካ ተንታኝ ማቲው ብሬደን እንደሚለው ግን ሶማሊያ በፖለቲካ መረጋጋት ወደፊት መጓዝ ከፈለገች በሀገሪቱ ህገ-መንግስት መስተካከል ያለባቸው ሶስት ዋና ዋና ክፍተቶች አሉ ። 
«አንደኛው ሕገ-መንግስቱን የተሟላ ለማድረግ መከለስና ማሻሻል ነው።ሌላው እስካሁን ባልታወቀው በፌዴሬሽኑ አወቃቀር ላይ ማብራሪያ መስጠት ሲሆን፤ የመጨረሻው ደግሞ አዲስ የምርጫ ስርዓት ማምጣት ነው ። » 
የሶማሊያ የምርጫ እና የፖለቲካ ቀውስ የተከሰተው ሀገሪቱ ከገጠሟት የምግብ እጥረት ፣ የአንበጣ ወረራና የአልሸባብ የሽብር ጥቃትን ከመሳሰሉ ከባድ ችግሮች በተጨማሪ ነው። እነዚህ ጉዳዮች ተደማምረው ሶማሊያ ወደማትወጣው ቀውስ ሊገፋት እና የአመታትን የልማት ስራ ዋጋ ሊያሳጣ ይችላል የሚል ስጋት አሳድሯል።የሶማሊያ የምጣኔ ሀብት ባለሙያ መሀሙድ ኢባሂም ይህ ለሶማሊያ ህዝብ ጥሩ ዜና አይደለም ይላሉ። 
"«ብዙ ተግዳሮቶች አሉ።የሰብዓዊ ጉዳዮች፣ የአንበጣ ወረራ እንዲሁም በሀገሪቱ ውስጥ የፖለቲካ አለመረጋጋት ችግሮች አሉ። እነዚህ ነገሮች ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ መሻሻሎችና እድገት ሊያደናቅፉ ይችላሉ። ይህ ለሶማሊያ ህዝብ ጥሩ ዜና አይደለም።» 
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሞሃመድ አብዱላሂ ሞሃመድ የስራ ዘመን በይፋ የተጠናቀቀው ያለፈው ሰኞ ሲሆን ፤የተቃዋሚ ፓርቲዎችም ከአሁን በኋላ ለፕሬዚዳንቱ ዕውቅና እንደማይሰጡ እየገለፁ ነው። ስለሆነም ከፓርላማ አባላት ፣ከተቃዋሚ መሪዎች እና ከሲቪል ማህበረሰብ አባላት የተውጣጣ ሀገሪቱን የሚመራ ምክር ቤት እንዲቋቋም ሀሳብ አቅርበዋል ፡፡ 
የአውሮፓ ህብረት በበኩሉ ሶማሊያ መጪውን አጠቃላይ ምርጫ በተመለከተ ስምምነት ላይ መድረስ አለመቻሏ፤ በሀገሪቱ የፖለቲካ እድገት ላይ የአለም አቀፉ ማህበረሰብ የነበረውን እምነት የሚሸረሽር ነው ብሏል ፡፡ የአውሮፓ ህብረት የውጭ ግንኙነት ሃላፊ ጆሴፕ ቦሬል በሰጡት መግለጫ የአውሮፓ ህብረት በበኩሉ በማንኛውም መንገድ ተገቢ ባልሆነ ሁኔታ የተቋማቱን ወቅታዊ ስልጣን ማራዘም እንደ ከባድ ውድቀት ይቆጠራል። ብሏል ፡፡ 
የፕሬዚዳንቱ የሥልጣን ዘመን በይፋ ቢጠናቀቅም፤ፓርላማው ተተኪዎች እስኪመረጡ ድረስ የተሾሙት ፕሬዚዳንት እና የሕግ አውጭዎች በቦታው እንዲቆዩ የሚያስችለውን ውሳኔ ያለፈው ዓመት ጥቅምት ወር አፅድቋል። 

Somalia Anschlag auf Hotel Afrik in Mogadischu
ምስል Farah Abdi Warsameh/AP Photo/picture alliance
Kenia Nairobi | Präsident Somalia | Mohamed Abdullahi Mohamed
ምስል Yasuyoshi Chiba/AFP/Getty Images

ፀሐይ ጫኔ 
ነጋሽ መሀመድ