1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሁለተኛው የዓለም ጦርነት አፍሪቃውያን አርበኞች 

ማክሰኞ፣ ግንቦት 4 2012

ካበቃ ባለፈው አርብ 75 ባስቆጠረው በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከአንድ ሚሊዮን በላይ አፍሪቃውያን ወታደሮች በቅኝ ገዥዎቻቸው ጦር ኃይሎች ውስጥ ተሰልፈው ተዋግተዋል።በጦርነት የተካፈሉት አብዛኛዎቹ አፍሪቃውያን አካላዊ እና ስነ ልቦናዊ ጉዳት ቢደርስባቸውም ለአገልግሎታቸው እውቅናም ይሁን ካሳ አላገኙም።

https://p.dw.com/p/3c8Sj
Senegal Französische Kolonialsoldaten
ምስል picture-alliance/AP Photo

የተረሱት የሁለተኛው የዓለም ጦርነት አፍሪቃውያን አርበኞች

ጎርጎሮሳዊው ግንቦት 8፣1945 ፣ሁለተኛውን የዓለም ጦርነት የለኮሰው ናዚ ጀርመን ድል የተደረገበትና ጦርነቱም በአውሮጳ ያበቃበት እለት ነው።ባለፈው አርብ የዋለውን የዚህን ታላቅ ድል 75 ተኛ ዓመት በተለያዩ የአውሮጳ ከተሞች በደማቅ ስነ ስርዓት ለማክበር ታቅዶ የነበረ ቢሆንም በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት እቅዶቹ ተሰርዘው ዕለቱ በቀዘቀዘ መንገድ ነው የታሰበው። የናዚ ጀርመን ተባባሪ ጃፓን ውጊያውን ቀጥላ ለሽንፈት የበቃችው አሜሪካን በሂሮሽማ እና ናጋሳኪ ከተሞች በነሐሴ 1945 አቶሚክ ቦምብ ከጣለች በኋላ ነበር።ጀርመን ፖላንድን በጎርጎሮሳዊው መስከረም አንድ 1939 ስትወር በተጀመረው ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከ60 ሚሊዮን ህዝብ በላይ አልቋል። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ከአንድ ሚሊዮን በላይ አፍሪቃውያን በቀድሞ ቅኝ ገዥዎቻቸው ጦሮች ስር በተዋጊነትና ለጦርነቱ አስፈላጊ በሆኑ ልዩ ልዩ አገልግሎቶች ተካፍለዋል።ከነዚህም ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በብሪታንያ የተቀሩት ደግሞ በፈረንሳይና በቤልጂግ ጦር ስር ነው የዘመቱትት።አንዳንዶቹ በአውሮጳ በአፍሪቃ እና በመካከለኛው ምሥራቅ እንዲሁም በህንድ ምያንማር እና በፓስፊክ ደሴቶች የውጊያ ዐውዶች ተሰልፈዋል።አብዛኛዎቹ ቆስለዋል አለያም ሞተዋል።ይሁን እና እነርሱን በተዋጊነት ባሰለፏቸው የቀድሞ ቅኝ ገዝዎች ዘንድ ያን ያህል እውቅና አልተሰጣቸውም።ያም ሆኖ ቢያንስ አሁን አንዳንድ ለውጦች እየታዩ ነው ይላል የዶቼቬለ አንቶንዮ ካስካይስ በዘገባው። በዘንድሮው የድሉ የ75 ተኛ ዓመት መታሰቢያ ያኔ ፈረንሳይን ወሮ የነበረው የጀርመንን ጦር ድል ያደረጉት የተባበሩት ኃይሎች በገቡበትት በፈረንሳይዋ በፕሮቨንስ የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑዌል ማክሮ  የአፍሪቃ ወታደሮች ላበረከቱት አስተዋጽኦ እውቅና ሰጥተዋል።ማክሮ እንዳሉት በሺህዎች የሚቆጠሩ አፍሪቃውያን ከነርሱ እጅግ ርቆ ለሚገኝ እና ለማያውቁት አገር ተሰልፈው በጦርነቱ መሰዋታቸውን አስታውሰው ለዘላለምም ደማቸውን ባተሙት አፍሪቃውያን ምክንያት ፈረንሳይ የአፍሪቃ አካል አላት ብለዋል። 
በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ለቅኝ ገዥ ኃይሎች የተሰለፉትን አፍሪቃውያን ወታደሮች የአውሮጳ የዜና አውታሮች በወቅቱ በፈቃዳቸው የተሰለፉ ወታደሮች ነበር የሚሏቸው። ይሁን እና አብዛኛዎቹ የአፍሪቃ ወታደሮች በግዳጅ ተመልምለው በቅኝ ገዥዎቹ ኃይሎች ውስጥ እንዲሰለፉ መደረረጉን ነው ከዚህ ቀደም ለዶቼቬለ በሰጡት ቃለ ምልልስ የተናገሩት።ከመካከላቸው አንዱ ኮንጎዋዊው አልበርት ኩኒዩኩ ናቸው።ኩኒዩኩ እንደሚሉት ያኔ ለኮንጎ ቅኝ ገዥ ለቤልጂግ ጦር በግዳጅ ነበር የተሰለፉት። 
«መጥተው ሲወስዱን በጨርቃ ጨርቅ ማምረቻ ፋብሪካ ውስጥ ነበር የምሰራው።ከዛ በኋላ ደግሞ ወደሌሎች ፋብሪካዎች ሄዱ።የተመለመሉት በሙሉ ወጣት ሠራተኞች ነበሩ። አንዳቸውም ከ30 ዓመት አይበልጡም።»
የ97 ዓመት እድሜ ባለጸጋው ኩኒዩኩ በሕይወት ከሚገኙት በሁለተኛው ዓለም ጦርነት ከተካፈሉ የኮንጎ አርበኞች አንዱ ናቸው።በያኔ አጠራሩ ከአፐር ቮልታ ከአሁኗ ከቡርኪናፋሶ፣ አውሮጳ የዘመቱት ቤቢ ሲ የተባሉት ሌላው አርበኛ እንደሚሉት ጦርነቱ በምን ምክንያት እንደሚካሄድ እንኳን ሳይረዱ ነው ለውጊያ የተሰለፉት።ከ5 ዓመት በፊት ለዶቼቬለ በሰጡት ቃለ ምልልስ እንዳሉት ለምን አውሮፓ ለውጊያ እንደመጡ ትክክለኛውን ምክንያት አያውቁም ነበር።
«ከኛ ጋር የነበሩ ሰዎች ስለ ፋሺዝም ሲነገር ስለምን እንደሚወራ አያውቁም ነበር።ለኛ የሚነግሩን ጀርመኖች እኛን እንዳጠቁን እና አፍሪቃውያንንም ዝንጀሮዎች አድርገው እንደሚቆጥሩን ነበር  ፣እኛም እንደ ወታደር የሰው ልጆች መሆናችንን እናረጋግጣለን።ይህን ነበር የምናውቀው።ይህ ነበር በወቅቱ የሚሰጠን ፖለቲካዊ ማብራሪያ ።» 
ጀርመናዊው ጋዜጠኛ ካርል ሩሰል በጉዳዩ ላይ ጥናት እና ምርምር አካሂዷል።በርሱም አስተያየት አፍሪቃውያኑ ወታደሮች የሚዘምቱበትን ምክንያት በግልጽ አያውቁም ነበር። የሚሰጣቸው ክፍያም እጅግ ዝቅተኛ ነበር ። 
«በሀሰት በጎ ፈቃድ እያሉ  ሰው እንዳይራብ ያህል በማዕድን ማውጫዎች ወይም በአውሮጳውያን የእርሻ ስፍራዎች ለሚሰሩ የአፍሪቃ ሠራተኞች ከሚሰጠው ክፍያ በጥቂት ሳንቲሞች የሚበልጥ ክፍያ ነበር የሚሰጣቸው።ያም ማለት በጣም ጥቂት የኤኮኖሚ ማነቃቂያ ነበር።በዚያን ጊዜ አብዛኛዎቹ ሰዎች ቤተሰቦቻውን መመገብ ባለመቻላቸው ተስፋ ቆርጠው ነበር።በዚህም ምክንያት አንዳንዶቹ ውትድርና ገብተው ነበር።ብዙውን ጊዜ የሚዘምቱበት ምክንያትም ሆነ በአጭር ጊዜ ውስጥ በመርከብ ተሳፍረው አውሮጳ ወደ ሚገኝ የጦር ግንባር መሄድ እንዳለባቸው አይነገራቸውም ነበር።»
አልበርት ኩኒኡኩ ይህን ዛሬም ይመሰክራሉ
«የማገኘው 5 ሺህ የኮንጎ ፍራንክ ማለትም ወደ 5 ዩሮ ብቻ ነበር በጡረታ የማገኘው።ይህ ለቤልጂግ ጥቅም ሲባል ለተዋጋ ሰው የሚገባ አይደለም።» 
አፍሪቃውያኑ የዘር መድልዎም ይፈጸምባቸው እንደነበርም ይናገራሉ።ኮንጎዋዊው ኩኒዩካ ከቤልጂጎቹ ጋር ሆነው በሚዋጉበት ጊዜም ሳይቀር በዘረኝነት ይሰቃዩ እንደነበር በቅርቡ በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ ተናግረዋል።ርሳቸው እንዳሉት ወደ ጦርነቱ በዘፈቋቸው በቤልጂጎች እንደ ባርያ ነበር የሚታዩት።ምንም መናገርም አይችሉም ነበር።ዓለም አቀፉ ዜና ማሰራጫ አልጀዚራ ባለፈው ዓመት ባካሄደው ምርመራ በብሪታንያ ጦር ስር የተሰለፉት አፍሪቃውያን ወታደሮች ያገኙ የነበረው ገንዘብ ነጭ ወታደሮች ከተከፈላቸው ጋር ሲነጻጸር እጅግ በጣም አነስተኛ ነበር።የአፍሪቃውያኑን አያያዝ ከባርነት ጋር የሚመሳሰል ብሎታል።
ይህ የጦርነቱ አንዱ ጠባሳ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ አፍሪቃውያኑ ከጦርነቱ ያገኙት ልምድ በተለይም ከአውሮጳ ወታደሮች ጋር መቀራረብ መቻላቸው እና በአውሮጳ የነበራቸው ሕይወት የአብዛኛዎቹን አፍሪቃውያን ንቃተ ሕሊና ለውጧል። ከጊዜ በኋላ ወደ ሃገራቸው ሲመለሱም ንቁ የፖለቲካ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ረድቷቸዋል።  በጋዜጠኛ ካርል ረስል አስተያየት ልምዱ ለአፍሪቃውያኑ ጠቅሟል።በተለይ በየሃገሮቻቸው የነጻነት ትግሎች እንዲያካሂዱ አበረታቷል።ይሁንና በክፍለ ዓለሙ ባበቡት የነጻነት ንቅናቄዎች ውስጥ ሁሉም አርበኞች ተቀባይነት አላገኙም ይላሉ አሜሪካዊው የኮልቢ ኮሌጁ የታሪክ ተመራማሪ ራፋኤል ሼክ።አፍሪቃውያኑ አርበኞች ለጨቋኞቹ ቅኝ ገዥዎች አገልጋይ በመባል በአብዛኛዎቹ የነጻነት ታጋዮች ይተቹ ነበር።አሁን በሕይወት ያሉት አፍሪቃውያን አርበኞችም ፋሺዝምን ድል ለማድረግ ቢዋጉም ያን ያህል እውቅና አለማግኘታቸው ያሳዝናቸዋል።አርበኞች እውቅና  የተነፈጋቸው ያኔ ብቻ አይደለም አሁንም እንጂ ።የአውሮጳ ሃገራት በተለይም ጀርመን ለነዚህ አርበኞች ምስጋናም ሆነ እውቅና አለመሰጠትዋ ሊቀየር የሚገባ ጉዳይ መሆኑን ነው ረሰል የሚያስረዱት።የቀድሞ ጠባሳ እንዲሽርም አሁንም ጊዜው አልረፈደም ይላሉ።
«ከዚህ ቀደም የተፈጸመውን ለመካስ የምር ሙከራ የማድረግ ጥረት ካለ እኛን ነጻ ያወጡንን ሰዎች ዘር ማንዘሮች አሁን ካለው የስደተኞች መርህ በተለየ መንገድ ልንይዛቸው ይገባል።በጦርነቱ ምክንያት በዓለም ዙሪያ ለተከተለው መዘዝ ካሳ ሊከፈል ይገባል።ሆኖም የትም ቦታ ማለት ይቻላል ከጦርነቱ በኋላ የተካሄዱ ግንባታዎች የሉም።»
ይላሉ ረስል የኮንጎው አርበኛ አልበርት ኩኒዩኩ ፣በያኔው አጠራር ቤልጆግ ከጃፓን ጋር በርማ ውስጥ ባካሄደችው ጦርነት ከተካፈሉ በኋላ በ1946 በጎርጎሮሳዊው አቆጣጠር ነው ወደ ሃገራቸው የተመለሱት።በበርማ ወታደራዊ አገልግሎትዎ ይኮራሉ ወይ ተብለው ሲጠየቁ እንባ እየተናነቃቸው የለም ሲሉ ነበር የመለሱት።ኩኒዩኩ በጦርነቱ ሕይወታቸው ባለፈው አፍሪቃውያን ጓዶቻቸው ጥልቅ ሃዘን ይሰማቸዋል።ከርሳቸው ጋር ወደ ደቡብ ምሥራቅ እስያው ግንባር ከዘመቱት 25 ሺህ አፍሪቃውያን ወታደሮች ጥቂቱ ናቸው በሕይወት ወደ ሃገራቸው የተመለሱት።

Die "Schwarze Armee" - Afrikaner im 1. Weltkrieg
ምስል picture-alliance/Gusman/Leemage
Frankreich Macron, Ouattara und Conde gedenken Kolonialtruppen im 2. Weltkrieg
ምስል picture-alliance/AP Photo/E. Gaillard
Die "Schwarze Armee" - Afrikaner im 1. Weltkrieg
ምስል picture-alliance/Mary Evans Picture Library
Senegal Französischer Offizier mit Kolonialsoldat
ምስል picture-alliance/AP Images

ኂሩት መለሰ

አዜብ ታደሰ