1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተመድ 75ኛ ጠቅላላ ጉባኤና ግጭቶች

ሰኞ፣ መስከረም 18 2013

ዓለም የጋራ ማሕበር ያቆመችበት75ኛ ዓመት የሚዘከረዉ ከተፈጥሮ ጥበቃ እስከ ንግድ፣ ከስደተኞች ፍልሰት እስከ አካባቢዊ ሠላም ለጋራ ችግሮች የጋራ መፍትሔን ከሚሹ ይልቅ የተናጥል ጉዞን የሚያቀነቅኑ ቀኝ ፖለቲከኞች የዋሽግተን፣ የለንደን፣ የብራዚሊያ፣ የደልሒ፣ ግራዎቹ ደግሞ የቤጂንግ፣ የሞስኮና የሌሎችንም አብያተ መንግስታት በተቆጣጠሩበት ወቅት ነዉ።

https://p.dw.com/p/3j84u
USA, New York I 75. Jahrestag der Vereinten Nationen
ምስል Mike Segar/Reuters

መሪዎች ሥለሰላም  የሚያዉቁ-የሚጨነቁበት ጊዜ ይመጣ ይሆን?

የዓለምን ሠላም በጋራ የማስከበር ዓላማና ተልዕኮ ያነገበዉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የተመሠረተበት 75ኛ ዓመት እየተዘከረ ነዉ።ዓለም ግን ዛሬም ሠላም የላትም።ሠላሟን የማስከበር ኃይል፣ሐብትና ብልሐቱ ሞልቶ የተረፋቸዉ ሐገራት መሪዎችም ሰሞኑን ባስተላለፉት መልዕክት ከመቀራረብ ይልቅ መነጣጠላቸዉን፣ ከትብብር ይበልጥ መቃረናቸዉን፣ከመቻቻል ይብስ መወቃቀስ መወጋገዛቸዉን እያረጋገጡ ነዉ።በዚሕ መሐል ከቀዝቃዛዉ ጦርነት ፍፃሜ በኋላ «በይደር» የተተወዉ የአርሜንያና የአዘርበጃን ጠብ አዲስ ዉጊያ ቀስቅሶ እያጋደለ ነዉ።ለሠላም የቆመ መንግስት ይኖር ይሆን? ላፍታ አብረን እንጠይቅ።

የፍልስጤም-እስራኤሎች ጠብ ዛሬም እንደ 1948ቱ (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) አይሁድ-ፍልስጤምን እያጋደለ፣ አይሁድ-አሜሪካ-አረብ-ፋርስን እያሻጠረ ነዉ።ሚሊዮኖችን ያረገፈዉ የኮሪያ ልሳነ ምድር ጦርነት አሸናፊም-ተሸናፊም ሳይለይበት ኑክሌር የታጠቁ ኃይላትን ሰሜን ደቡብ እንዳፋጠጠ ሰባኛ ዓመቱን ያዘ።

እርግጥ ነዉ የቬትናም-አሜሪካኖች ጦርነት በቬትናም ኮሚንስትቶች ድል አድርጊነት በመጠናቀቁ ሠላም ነዉ።የሲኖ-ታይዋን-አሜሪካኖች ፍጥጫ ግን ዛሬም እንደ 1950ዎቹ እንደናረ ነዉ።በሕንድና ፓኪስታን፣ በቻይናና ሕንድ፣ በጃፓንና ቻይና መካከል ሠላምም ጦርነትም የለም።

የአፍሪቃ ሐገራት ከቅኝ አገዛዝ እንዲላቀቁ ዓለም አቀፉ ድርጅት በ1960ዎቹ ያደረገላቸዉ ድጋፍና እገዛ በቀላሉ የሚገመት አይደለም።አብዛኛዉ አፍሪቃዊ ግን ዛሬም ፖለቲካ ከሚዘዉረዉ ግጭት፣ጥፋት፣ ስደትና ረሐብ አልተላቀቀም።

ኃያላኑ መንግሥታትና ተከታዮቻቸዉ በቅርብ ዓመታት የወረሩና ያወደሟቸዉ ኢራቅ፣አፍቃኒስታን፣ ሊቢያ እና የመን  ላይ ሠላም ለማዉረድ፣ጠንካራ መንግስት ለማቆምም ሆነ መልሶ ለመገንባት ዓለም ያደረገዉ ጥረት ኢምንት ነዉ።

ሶሪያ ዘንድሮም ለዘጠኛ ዓመት እየወደመች ነዉ።የዩክሬንና የሩሲያ ጠብ መፍትሔ አላገኝም።በ2015 ዓለም አቀፍ ስምምነት ተበጀለት» የተባለለት የዋሽግተንና የቴሕራን የኑኩሌር መርሐ ግብር ጠብ በአንድ ሰዉ ተቃዉሞና ጥላቻ ብቻ ዛሬ የዓለምን ሰላም ከሚያሰጉ ፍጥጫ ግጭቶች አንዱ ሆኗል።

የበርሊን ግንብ ተደርምሷል።የሩሲያና የአዉሮጳ ሕብረት፣የአሜሪካና የቻይና፣የቱርክና የግሪክ፣ የኢራንና የሳዑዲ አረቢያ፣የኢራንና የእስራኤል ፍጥጫ፣ ጠብ ቁርቁሶች ግን በያሉበት እየተንተከተኩ ነዉ።ኮቪድ 19 ደግሞ የድፍን ዓለምን ዜጋ እኩል እየፈጀ፣ ድፍን ዓለምን እያርበደበደ ነዉ።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬሽ ባለፈዉ ሰኞ እንዳሉት ኮቪድ 19 የዓለምን (አንድነት) ለፍስፍስነትን ያጋለጠ ነዉ።

«ዓለምን የሚገዙ መንግስታትን ማንም አይሻም፣ የዓለምን የጋራ  አስተዳደርን ለማሳደግ ግን በጋራ መጣር አለብን። የኮቪድ 19 ወረርሺኝ የዓለምን (አንድነት) ለንቋሳነት ያጋለጠ ነዉ።መፍትሔ ልናገኝለት የምንችለዉ በጋራ ሥንጥር ብቻ ነዉ።ዛሬ የጋራ ጥረት የሚሹ የተትረፈረፉ ፈተናዎች ግን  የጋራ መፍትሔ የመስጠት ከፍተኛ እጥረት አለብን።»

USA I UN-Generalversammlung I Antonio Guterres
ምስል UNTV/AP/picture-alliance

ዓለም የጋራ ማሕበር ያቆመችበት 75ኛ ዓመት የሚዘከረዉ ከተፈጥሮ ጥበቃ እስከ ንግድ፣ ከስደተኞች ፍልሰት እስከ አካባቢዊ ሠላም  ለጋራ ችግሮች የጋራ መፍትሔን ከሚሹ ይልቅ የተናጥል ጉዞን የሚያቀነቅኑ ቀኝ ፖለቲከኞች የዋሽግተን፣ የለንደን፣ የብራዚሊያ፣ የደልሒ፣ ግራዎቹ ደግሞ የቤጂንግ፣ የሞስኮና የሌሎችንም ሐገራት አብያተ መንግስታት በተቆጣጠሩበት ወቅት ነዉ።

መሪዎቹ ለድርጅቱ ጉባኤ ከያሉበት በቪዲዮ ያስተላለፉት መልዕክት ደግሞ የተናጥል ጉዞን ከመምረጣቸዉም በላይ የከፋ ጠብና ፍጥጫ የሚሹ መሆናቸዉን የሚያረጋግጥ ነዉ።የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ግንባር ቀደም መሥራች፣በኃብት፣ በጉልበት፣ በሳይንስም የዓለም ቀዳሚዋ ሐገር መሪ ቀዳሚዉ ናቸዉ።ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ።

«ይሕንን ወረርሺኝ በዓለም ያሰራጨችዉን ሐገር ተጠያቂ ማድረግ አለብን።ቻይናን።በቫይረሱ የመጀመሪያ የስርጭት ወቅት፣ ቻይና የሐገር ዉስጥ ጉዞን አግዳ ከቻይና ወደሌላዉ ዓለም የሚደረግ በረራን ፈቅዳ፣ ዓለም በተሕዋሲዉ እንዲያዝ አድርጋለች።የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቻይና ላደረሰችዉ ጥፋት ተጠያቂ ሊያደርጋት ይገባል።»

ታሕሳስ 2015 ፓሪስ-ፈረንሳይ ላይ የተፈረመዉን የዓለም የተፈጥሮ ጥበቃ ዉልን ያፈረሱት ዶናልድ ትራምፕ ናቸዉ።የዓለምን የተፈጥሮ ሐብት በመበከል በቀደም ተጠያቂ ያደረጉትን ግን ቻይናን ነዉ።

  «ከዚሕ በተጨማሪ ቻይና በየዓመቱ ብዙ ሚሊዮን ቶን የሚመዝን ፕላስቲክና ቁሻሻ ባሕር ዉስጥ ትጨምራለች።ከሌሎች ሐገራት ዉሐ ዉስጥ አሳዎችን አለቅጥ ታመርታለች።እጅግ በርካታ የዉሐ ዉስጥ ተፈጥሯዊ ሐብትን ታወድማለች።ከየትኛዉም ሐገር የበለጠ መርዛማ ንጥረ ነገር ወደከባቢ ዓየር ትለቃለች።»

ቻይኖች ቅኔ ካላቸዉ  ቺ ጂፒንግ በቀደም ዘርፈዉታል።የቻይናዉ ፕሬዝደንት ለአሜሪካዉ አቻቸዉ ባስተላለፉት አፀፋ «ቀዝቃዛም ሙቅም» ጦርነት አንሻም አሉ።በር ዘግቶ ብልፅግናም አንፈልግም።                                                    

«እኛ ከማንኛዉም ሐገር ጋር ቀዝቃዛም ሆነ ሞቃት ጦርነት የመዋጋት ፍላጎት የለንም።ከሌሎች ጋር ያሉንን ልዩነቶች ለማጥበብና ዉዝግቦችን በዉይይትና ድርድር ለማስወገድ ጥረታችንን እንቀጥላለን።እራሳችንን ብቻ ማበልፀግና የዜሮ ድምር ዉጤት ጨዋታን አንፈልግም።በር ዘግተን መበልፀግ አንፈልግምና።»

ዓለምን የሚዘዉሩት ኃያላንና ተከታዮቻቸዉ ለተናጥል መርሕ-ጉዟቸዉ ማረጋገጪያ የዓለምን የጋራ ማሕበር መድረክን በቢዲዮ መልዕክት ሲፈነጩበት ባለፈዉ ሳምንት፣ የአዉሮጳ ሕብረት መሪዎች ሊያደርጉት የነበረዉን ጉባዜ በኮሮና ተሕዋሲ ስጋት  ሠርዘዋል።ጉባኤዉ ባይሰረዝ ኖሮ በቤሎሩስ ፖለቲካዊ ቀዉስ፣በግሪክና በቱርክ ፍጥጫ ላይ ለመወሰን ያለመ ነበር።

Bildkombo | 75. Sitzung UN-Generalversammlung | Rede Xi und Trump
ምስል UNTV/AP/picture alliance

መሪዎቹ ባለመወሰናቸዉ ፖለቲካዊዉ ቀዉስ፣ ፍጥጫዉ ቢያንስ እስከያዝነዉ ሳምንት በነበረበት መቀጠሉ አነጋግሮ ሳያበቃ ትናንት የዛሬ ሰላሳ ዓመት ግድም የተዳፈነዉ የአርሜኒያና የአዘርበጃን ጠብ ምርጊቱን በርቅሶ ፈነዳ።ሌላ ጦርነት፣አዲስ ግድያ፣ ነባር ዉዝግብ።

 የ1920ዎቹ የመጀመሪያ አጋማሽ ለእስከዚያ ዘመኑ ዓለም በተለያም ለአዉሮጳና ለእስያ አዳዲስ መንግሥታት፣ አስተዳደር አገዛዝ የተመሰረተ፣ አዳዲስ ካርታ የተሳለበት ዘመን ነዉ።

ዘመኑ ከ1200ዎቹ ማብቂያ ጀምሮ ገሚስ ዓለምን ያስገበረዉ የኦስማን ቱርክ የመጨረሻ ስቅታዉን አጓርቶ ያሸለበበት፣ የመጀመሪያዉ የዓለም ጦርነት በለንደን-ፓሪስ ኃያላን ድል አድራጊነት የተጠናቀቀበት፣ክሬምሊንን የተቆጣጠሩበት የሩሲያ ኮሚንስቶች ተጠናክረዉ ባዲስ ሥልት አዳዲስ ግዛት የተቀራመቱበት ዘመን ነበር።

የሩሲያ ኮሚንስቶች ሶቬት ሕብረት ባሉት አዲስ ኮሚንስታዊ ሥርወ-መንግስት ሥር «ሪፐብሊክ» ከሚል ቅድመ-ቅፅል ጋር ከተጠቀለሏቸዉ የአካባቢዉ ሐገራት ሁለቱ አርሜንያና አዘርበጃን ናቸዉ።ከኦስማን ቱርክ የረጅም ዘመን አጋዛዝ ተላቅቀዉ ነፃነታቸዉን ባወጁ በጥቂት ዓመታት ዉስጥ የሞስኮዎች ክርን የደፈለቃቸዉ ሁለቱ ሐገራት በተመሳሳይ ጊዜ በሞስኮዎች እጅ እንደወደቁ ሁሉ በተመሳሳይ ወቅት በ1991 ሶቬት ሕብረት ስትፈረካከስ የየራሳቸዉን  ነፃ መንግሥት መሠረቱ።

በ190 ታላቁ የአርታዚያድ ሥርወመንግሥት የተመሠረተባት አርሜኒያ ጥንታዊ፣ ተራራማ፣ ወደብ አልባ እና የ3 ሚሊዮኖች ሐገር ናት።አዘርበጃንም ታሪካዊ፣ ምስራቅ አዉሮጳና ምዕራብ እስያን የሚያገናኝ መንገድ የሚያልፍባት፣ የካስፒያን ባሕርን የምትዋሰን ሥልታዊ፣ከሁሉም በላይ ከአጠቃላይ ግዛትዋ ሁለት-ሶስተኛዉ በነዳጅ ዘይትና ጋስ የበለፀገ ሐብታም ሐገር ናት።የሕዝቧ ብዛትም ከአርሜንያ ከሶስት እጥፍ በላይ ይበልጣል።10.1 ሚሊዮን።

Aserbaidschan Berg-Karabach Militärkonflikt
ምስል Armenian Defense Ministry/Reuters

አርሜንያ ክርስቲያኖች፣ አዘርበጃን ደግሞ ሙስሊሞች የሚበዙባቸዉ ሐገራት ናቸዉ።ሁለቱን ሐገራት የሚያዋስነዉ ናጎርኖ ካራባሕ የተባለዉ ግዛት በሶቭየት አገዛዝ ዘመን የራስ ገዝ አስተዳደር ሥልጣን የነበረዉ፣ ነገር ግን በመልከዓ ምድር አቀማመጡ የአዘርበጃን ግማደ ግዛት አካል ሲሆን አብዛኛ ነዋሪዎቹ የአርመን ዝርያ ያላቸዉ ናቸዉ።

በአርሜንያ የሚታገዙት የናጎርኖ ካራባሕ ሸማቂዎች በ1994 በአዘርበጃን ላይ ጦርነት ከፍተዉ እራሱን የአርትሳክሕ ሪፐብሊክ ያሉትን መንግሥት መመስረታቸዉን አስታዉቀዋል።የአማፂያኑ መንግስት ከአርሜንያ ድጋፍ ከማግኘቱ በስተቀር ግን ዓለም አቀፍ እዉቅና ዓላገኘም።የዓለም አድራጊ ፈጣሪዎች ታይዋንና ሶማሊያ ላንድን የመሳሰሉ ግዛቶች የየራሳቸዉ መንግስት መመስረታቸዉን ሳይቃወም፣ አዉቅናም ሳይሰጥ ዓመታት እንዳስቆጠረ ሁሉ የናጎርኖ ካራባሕ ዉዝግብንም በይደር አለፈዉ ወይም ዘነጋዉ።

በ30 ዓመት የተዳፈነዉ ዉዝግብ አርሜንና ናጎርኖ ካራባሕን ባንድ ወገን አዘርበጃንን በሌላዉ አሰልፎ እነሆ  ዳግም ደም እያቃባ ነዉ።ግጭቱ ቱርክ፣ ሩሲያ እና ኢራንን በቀጥታ የአዉሮጳና የአሜሪካ ኃላንን በተዘዋዋሪ የሚነካ ነዉ።የክሬምሊን ቃል አቀባይ ድሚትሪይ ፔስኮቭ እንዳሉት ሞስኮ ጦርነቱን ለማስቆም የምትችለዉን ሁሉ እያደረገች ነዉ።

«በናጎርኖ ካራባሕ የመገናኛ መስመር በኩል ትናንት የተፈጠረዉ ሁኔታ በጣም መጥፎ ነዉ።ለሞስኮም፣ ለሌችም ሐገራት በጣም የሚያሳስብም ነዉ።ዉጊያ ከተጫረበት ሰዓት ጀምሮ፣ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ ከየርቫንና ከባኩ አቻዎቻቸዉ ጋር እየተናኙ ነዉ።»

ከአዘርበጃን ሕዝብ አብዛኛዉ የቱርክ ዝርያ አለዉ።በፖለቲካ አሰላለፍም አንካራ የየርቫን ጠላት፣የባኩ ጥብቅ ወዳጅ ናት።በዚሕም ምክንያት ጦርነቱ ከቀጠለ ቱርክ ከአዘርበጃን ጎን እንደምትሰለፍ የቱርኩ ፕሬዝደንት አስታዉቀዋል።የአዉሮጳ ሕብረት ግን እንደ ዲፕሎማሲዉ ወግ ተፋላሚ ኃይላት ዉጊያዉን እንዲያቆሙ ጠይቋል።የሕብረቱ ኮሚሽን ቃል አቀባይ ፔተር ስታኖ እንዳሉት ጦርነቱ ከቀጠለ ከሁለቱ ሐገራትም አልፎ አካባቢዉን ያብጣል።

«ሁሉም ወገኖች የለየለት ሙሉ ጦርነት ከማቀጣጠል ለመቆጠብ የሚችሉትን ሁሉ እንዲያደርጉ እናሳስባለን።ያደርጋሉ የሚል ተስፋም አለን።ምክንያቱም አካባቢዉ የሚሻዉ ዋና ነገር ይሕንን ነዉ።ናጎርኖ ካራባሕ ዉስጥ ዉጊያ መቀጣጠሉ በጣም አሳሳቢ ነዉ።ምክንያቱም ለአካባቢዉ ሠላምና መረጋጋት በጣም አስጊ መዘዝ ማስከተሉ አይቀርም።የአዉሮጳ ሕብረት፣ ሁሉም ወገኖች ዉጊያዉን ከሚያባብስ እርምጃ እንዲታቀቡ፣የጠመንጃዉን ዉጊያ ባስቸኳይ እንዲያቆሙ በጥብቅ ያሳሰበዉም ለዚሕ ነዉ።»

Azerbaijan Nagorno-Karabakh Escalation
ምስል Ibrahim Hashimov/dpa/picture-alliance

ዓለም ጠቡን ምናልባት ዳግም ለማዳፈን  በየፊናዉ ቢጣደፍም ተፋላሚዎች እስካሁን ዉጊያዉን የማቆም አዝማሚያ አላሳዩም።ዛሬ እስከ ቀትር በተደረገዉ ዉጊያ ከሁሉቱም ወገን 40 ሰዉ መገደሉ ተዘግቧል።ከ75 ዓመት በፊት የዓለምን ሠላም ሚያስከብር የጋራ ማሕበር የመሰረተዉ ዓለም መሪዎች ሥለሰላም  የሚያዉቁ-የሚጨነቁበት ጊዜ ይመጣ ይሆን? መቼ? ነኝ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

ኂሩት መለሰ