1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቦምብ ፍንዳታ ምርመራ

Merga Yonas Bula
ሰኞ፣ ሰኔ 18 2010

በመስቀል አደባባይ ቅዳሜ ዕለት በደረሰው የቦንብ ፍንዳታ ተጠርጥረው የተያዙት ሰዎች ቁጥራቸዉ 30 መድረሱን የአገር ዉስጥ ዘገባዎች ያመለክታሉ። አስራ አምስት የአዲስ አበበ ፖሊስ ኮሚሽን አባላትም «በፀጥታ ጥበቃው ረገድ ክፍተት ታይቷል» በሚል በቁጥጥር ስር መዋላቸዉም ተገልጿል።

https://p.dw.com/p/30FbV
Äthiopien Kundgebung Premierminister Abiy Ahmed in Addis Ababa | Explosion
ምስል Oromo Media Network

በቅዳሜ ዕለት የተፈፀመዉ ወንጀል ዉስጥ የተሳተፉት ግለሰቦች ድርጊታቸዉ እጅ ከፍንጅ ወይም ፍላግራንት ጥፋቶች ናቸዉ የሚሉት የሕግ ባለሙያ እና ጠበቃ ተማም አባቡልጉ የቦምቡም ፍንዳታ እየተካሄደ ያለዉን ለውጥ የማይፈልጉ በጀርባ አሉ የሚል ግምት ሊሰጠዉ እንደሚችል ይጠቅሳሉ። የተጠርጣርዎችን ምርመራ በተመለከተ ተከታዩን ብለዋል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ግርማ ካሳን ጨምሮ 20 ተጠርጣሪዎች በዛሬዉ ዕለት ልደታ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ከቀትር በኋላ መቅረባቸዉን የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል። የተፈፀመዉ ጥቃት በወንጀለኛ መቅጫ ወይም በፀረ-ሽብር ሕግ ሊዳኝ እንደሚችል የሚናገሩት የሕግ ባለሙያ እና ጠበቃ ተማም፤ በሕጉ መሠረት ተጠርጣርዎቹ በ48 ሰዓት ዉስጥ ፍርድ-ቤት ቀርበው ጉዳያቸው እንደሚታይም ተናግረዋል።

በተጠርጣርዎች ላይ የሚካሄደው ምርመራ «በውጭ አገር መርማሪዎች» እንዲሁም በ«ዘመናዊ የምርመራ ማሽኖች (ፎሪንሲክ)» እንደሚደገፍ ዛሬ ይፋ ሆኗል። ፍንዳታዉን ለመመርመርም የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት ከኤፍ ቢ አይ ባለሙያዎችን እንደሚልክ ባለስልጣናቱ አስታውቀዋል።

የምርመራዉን አካሄድ እንዴት ይመለከቱታል? ብለን የፌስቡክና የዋትስአፕ ተከታታዮችን አስተያየት ጠይቀን ነበር። ምርመራው ቶሎ በፍጥነት ተጠናቆ ውጤቱ ለሕዝብ ይፋ መደረግ እንዳለበት ያሳሰቡ ሲኖሩ፤ ሌሎች ደግሞ ምርመራው በገለልተኛ አካል መደረግ እንዳለበት አስተያየታቸዉን አጋርተዋል። ምርመራዉ በዉጭ ባለሙያዎች ይደገፋል የምለዉን በበጎ የተቀበሉ ሲኖሩ ሌሎች ደግሞ የውጭ አገር መርማሪዎች መሳተፋቸውን እንደሚይደግፉ ገልፀዋል።

ዘገባዉን ሙሉ ለማዳመጥ አዉዲዮዉን ይጫኑ።

መርጋ ዮናስ

ሸዋዬ ለገሠ