ብርጋዴር ጀኔራል ተፈራ ማሞ ባህር ዳር ከተማ 9ኛ ፖሊስ ጣቢያ ናቸው ተባለ
ረቡዕ፣ ግንቦት 10 2014የአማራ ክልል የልዩ ኃይል የቀድሞው ዋና አዛዥ ብርጋዴር ጀኔራል ተፈራ ማሞ ባህር ዳር ከተማ 9ኛ ፖሊስ ጣቢያ ውስጥ እንደሚገኙ መልእክት እንደደረሳቸው ባለቤታቸው ወይዘሮ መነን ኃይሌ ማምሻውን ለዶቼቬለ ተናገሩ። ወደ ባህር ዳር መቼ እንደተወሰዱ ያውቁ እንደሆን የተጠየቁት ወይዘሮ መነን " የተወሰዱት ዛሬ ይሁን የታገቱ እለት አላወቅንም" ብለዋል። መረጃውን ከማን እንደሰሙትና ምን ያህል እውነተኛ እንደሆነ ለቀረበላቸው ጥያቄም " ባህርዳር ለሚገኝ ሰው እዚያ [ 9ኛ ፖሊስ ጣቢያ ] መሆናቸውን መልእክት ልከውልኝ ነው ያወቅሁት " ብለዋል።
ባለቤታቸው ወይዘሮ መነን ኃይሌ የፌዴራልና የክልል መንግሥታት እንደሚበሳጩባቸው መረጃ ሲነግሯቸው በሀቅ ከማገልገላቸው በቀር የሚሰጧቸው መግለጫዎች ለእሥርም ሆነ ከሌሎች ጋር ለግጭት እንደማይዳርጋቸው ይገልፁ እንደነበር ተናግረዋል።
ትናንት በሄዱበት የፍትሕ ተቋም ሁሉ ባለቤታቸው የት እንደሚገኝ የሚነግራቸው አለማግኘታቸውን የገለፁት ወይዘሮ መነን ዛሬ ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ ሄደው መጠየቃቸውንና ጉዳዩን እንዲያስመዘግቡ እንደተነገራቸው ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል ዳይሬክተር አቶ ያሬድ ኃይለማርያም "አንድን ሰው ከሕግ ውጪ ማሰር፣ ያለበትን መደበቅና መሰወር የፍትሕ ተቋማትን ትርጉም አልባ ያደርጋቸዋል፣ በተጨማሪም ሰዎች በመንግሥት እና በሕግ የበላይነት ላይ ያላቸው እምነት እንዲሸረሸር በማድረግ ሕገወጥነትንም ያስፋፋል" ብለዋል።
ሰሎሞን ሙጬ
ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር
ኂሩት መለሰ