1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ትምህርት

የተማሪዎች የብሔራዊ ፈተና ዝግጅት

Merga Yonas Bula
ዓርብ፣ ግንቦት 17 2010

የ10ኛ ክፍል ወይም የኢትዮጵያ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት እንዲሁም የ12ኛ ክፍል ወይም የዩንቨርስቲ መግቢያ ፈተና ከግንቦት 22 እስከ 30፣ 2010 ዓም ድረስ በሀገር አቀፍ ደረጃ ይሰጣል።

https://p.dw.com/p/2yLLf
20.06.2013 DW Online Karten Basis Aethiopien spanisch

ብሔራዊ ፈተና በኢትዮጵያ

ለዚህ ብሔራዊ ፈተና 1,200,676 የ10ኛ እና 284,312 የ12ኛ ክፍል ተፈታኞ እንደተመዘገቡ፣ ከዚህ ውስጥ 883,555 የ10ኛ እና 243,982 የ12ኛ መደበኛ ተማሪዎች መሆናቸዉን የሀገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ የሕዝብ መረጃ ያመለክታል።

ተማሪዎች ለዚህ ፈተና ዝግጅታቸዉ ምን እንደሚመስ ለማጠያየቅ ሞክረናል። በአዲስ አበባ በተለምዶ ቤቴል ተብሎ የሚጠራው አካባቢ ነዋሪ መሆኑን የነገረን ግን ስሙ እንዳይገለፅ የፈለገ የ10ኛ ክፍል ተማሪ ከጓደኞቹ ጋር ሆኖ ለፈተናዉ እየተዘጋጀን ነው ይላል።

የሙከራ ፈተና ወይም በተለምዶዉ ሞዴል ፈተና እንደወሰዱ የምናገረው ይህ ተማሪ አጋጣሚው የብሔራዊ ፈተና ዝግጅቱን ለመፈተሸ እንደረዳዉ ገልጿል። የሚማርበት ትምሕርት ቤት የብሔራዊ ፈተናዉን ለመፈተን በቂ ዝግጅት ለማድረግ መጻሕፍትና ሌሎች አስፈላጊ ቁሳቁሶች እንዳሉትም አክሎበታል።

በዶይቼ ቬሌ ዋትስአፕ ገፅ ላይ ለፈተናው ስለሚያደርጉት ዝግጅት ስማቸዉን ሳይጠቅሱ አስተያየታቸዉን የላኩልን ተማሪዎችም አሉ።

«እኔ አሁን የአስረኛ ክፍል ተፈታኝ ነኝ፤ ዝግጅቱ አሪፍ ነው፤ አሁን ዝግጅቴን አጠናቅቄአለሁ፤ ፈተናውን መጠባበቅ ይዣለሁ» ይላል አንዱ፤ ሌላው ደግሞ፤ «በመጀመርያ ለዚህ ያደረሰን አምላክ እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን!! ዝግጂታችን ያው እንግዲህ የማትሪክ ዋዜማ 6 ኪ.ግ ካሮት በልተን እንጠብቀዋለን፡፡ ከዛ ዓይናችን ጥርት/ፍክት/ይላል፣ ከዛ በኋላ መኮምኮም ነው፤ ኮድ ከገጠመልን ጋር» ሲል በቀልድ መልክ ዝግጅቱት ያለውን ገልጿል።

የተማሪዎችን  የፈተና ዝግጅት የታዘበ ሌላ ወጣት ተማሪ «ሁሉም ተማሪ ማለት ይቻላል ጊዜውን በአግባቡ እየተጠቀመበት ይገኛል፤ ማለትም የተለያዩ የሙከራ ጥያቄዎች በመስራት ላይ የገኛል» ብሏል።

የዛሬ ሁለት ዓመት የአገሪቱ የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተና ሾልኮ ወጥቶ በማህበራዊ ድረ-ገጾች ከተሰራጨ በኋላ የትምህርት ሚኒስቴር ፈተናውን ማቋረጡ ይታወሳል። ይህንን በማስታወስ ሌላ አስተያየት ሰጭ ፈተናዉን እንደ ባለፈዉ ሁለት ዓመት ሾልኮ ካላወጡት «እኛ እንደተለመደዉ ዝግጁ ነን» ይላል።

የፈተናውን ደህንነት ከወትሮው በተሻለ መልኩ ለማስጠበቅ የፈተና ደህንነት ስራውን አጠናክሮ እየሰራ እንደ ሆነ፤ ከፈተና ዝግጅት፣ ህትመት፣ ስርጭትና አሰጣጥ ጋር የተያያዙ ችግሮችም ዳግም ሳይከሰቱ ሰላማዊና በተረጋጋ ሁኔታ ፈተናውን ለመስጠት መዘጋጀቱን የሀገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ ያወጣው መረጃ ያመለክታል።

«ለፈተናው ምንም አይነት ዝግጅት የምናደርገበት ግዜ የለም፣ ምክንያቱም በየሰአቱ እረብሻ ነው፣ አንድ ተማሪ አጋጣሚ ሆኖ ዩኒፎሮም ሣይለብሥ ከወጣ ወይም ከጥናት ሢመለሥ ሁለት ወይም ሦስት ሆኖ ሢሄድ ከታዬ እረብሻ ሊያነሡ ነው ተብሎ ይታሠራል» የሚል ሌላ አስተያየትም በፅሁፍ በዋትስአፕ መስመራችን ተልኮልናል።

በኦሮሚያ ክልል በምሥራቅ ወለጋ ዞን የነቀምት ከተማ ነዋሪ የሆነ ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ የ10ኛ ክፍል ተማሪ አንድ ለሰባት በሚል አደረጃጀት አንድ በትምህርት ጎበዝ የሆነ ደከም ያሉትን ተማሪዎች እንደሚያስጠና ይናገራል። ይሁን እንጅ ተማሪዉ የፀጥታ ኃይሎች/ በትምህርት ቤት ቅጥር ግቢ ዉስጥ የሚገኙበት ሁኔታ በተማሪዎች ስነ-ልቦና ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳሳረፈ ያምናል። ወታደሮች ወደ ካምፕ ሲመለሱ ብቻ የተማሪዎች ስነ ልቦና ሊረጋጋ እና ለፈተና የሚያደርጉት ዝግጅትም ሊሻሻል እንደሚችል ይገምታል።

በኦሮሚያ ልዩ ዞን በሰበታ ከተማ ተወልዶ ያደገዉ ተማሪ ጋዲሳ ዋጊ ባለፈዉ ዓመት የ12ኛ ክፍል የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ወስዷል። ይሁን እንጅ በነበረዉ የፖለቲካ አለመረጋጋት ወደ 11ኛ ክፍል የሚወስደዉን ነጥብ ማምጣት እንዳልቻለ፤ አሁን አዲስ አባባ በሚገኘዉ በሬፍት ቫሊ ዩኒቨርሲቲ የነርስነት ትምህርት በመከታተል ላይ እንደሚኝ ገልጾልናል። እንደ ጋዲሳ አስተያየት፣ በኦሮሚያ ክልል የተከሰተው የፖለቲካ ቀዉስ በዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ውጤት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ነበረዉ።

የፖለቲካ አለመረጋጋት የፈጠረዉ የትምህርት ሂደት መቆራረጥን ከግምት በማስገባት በአማራ ክልል በደብረ ማርቆስ የቴክሚክና ሙያ የልዩ ፍላጎት አማካሪ ነኝ ያለዉ ወጣት አማረ ዋርቁ የሚከተለዉን ጽሑፍ በዋትስአፕ ልኮልናል፤ «ፈተናውን ለማለፍ ውድድሩ አገር አቀፍ ከሆነ ከባድ ነው። ነገር ግን ውድድሩ ክልልን መሠረት ያደረገ ከሆነ/ ከታዳጊ ክልሎች/  ጋር እኩል ከሆን የአማራ እና ኦሮሞ ልጆች መፈተን ይችላሉ» ይላል።

በ2010 የትምህርት ዘመን 2,850 የ10ኛ ክፍል እና 1,200 የሚሆን የ12ኛ ክፍል የፈተና ጣቢያዎች እንደተዘጋጁ የሀገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ የሕዝብ መረጃ ያሳያል። ይህንንም ፈተና ለማቀናጀት ከ50,774 በላይ የትምህርት ባለሙያዎች በፈተና ጣቢያ ኃላፊነት፤ በተቆጣጣሪነት እንዲሁም በፈታኝነት እንደሚሰማሩም ኤጀንሲው ገልጿል።

መርጋ ዮናስ

ሸዋዬ ለገሠ