1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የብልፅግና ባለስልጣን መገደል፣ ጠቅላይ ሚንስሩ ማስጠንቀቂያ፣ ድርድር---

ዓርብ፣ ሚያዝያ 27 2015

በሰዉ እጅ የተገደሉ የገዢዉ ፓርቲ ፖለቲከኛ ሽኝትና የመገደላቸዉ ሰበብ-፣ የጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አሕመድ ማስጠንቀቂያ፣ የኢትዮጵያ መንግስትና የኦሮሞ ነፃ አዉጪ ሠራዊት (ኦነሠ) ድርድር የተስፋና ቀቢፀ-ተስፋ ቃርጮሽ፣ የጀርመኑ መራሔ መንግስት የኢትዮጵያ ጉብኝትና በጎ-መጥፎ መልዕክቱ

https://p.dw.com/p/4QxzJ
Äthiopien | Bundeskanzler Scholz in Addis Abeba
ምስል Michael Kappeler/dpa/picture alliance

ጤና ይስጥልኝ እንደምን ዋላችሁ።ሳምንቱ ለኢትዮጵያ በአብዛኛዉ ሐዘን፣ቅሬታና ሥጋትን ከተስፋ ጋር የቀየጡ ሁነቶች የተዘገቡበት ነበር።ከብዙዎቹ፣ የብዙዎችን የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተከታታዮች ትኩረትን የሳቡትን አራት ርዕሶች መርጠናል።በሰዉ እጅ የተገደሉ የገዢዉ ፓርቲ ፖለቲከኛ ሽኝትና የመገደላቸዉ ሰበብ-፣ የጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አሕመድ ማስጠንቀቂያ፣ የኢትዮጵያ መንግስትና የኦሮሞ ነፃ አዉጪ ሠራዊት (ኦነሠ) ድርድር የተስፋና ቀቢፀ-ተስፋ ቃርጮሽ፣ የጀርመኑ መራሔ መንግስት የኢትዮጵያ ጉብኝትና በጎ-መጥፎ መልዕክቱ።ከተሰጡት አስተያየቶች ከስድብና ዘለፋ የፀዱትን ነቅሰን በዚሁ ቅደም ተከተል እንቀጥላል።አብራችሁን ቆዩ።
ባለፈዉ ሳምንት ሰሜን ሸዋ ዉስጥ በታጣቂዎች የተገደሉት በአማራክል ክልል የኢትዮጵያ ገዢ ፓርቲ የብልፅግና የበላይ የግርማ የሽጥላ አስከሬን ከአዲስ አበባ የተሸኘዉ፣ የተቀበረዉም ባለፈዉ ዕሁድ ነበር።የአቶ ግርማና የአንጋቾቻቸዉ መገደል ያስከተለዉ ሐዘን፣ቁጣ፣ የመንግስት እርምጃም እንደቀጠለ፣ ሰበብ ምክንያቱ አሁንም እያነጋገረ ነዉ።
የግድያ፣ ሽኝቱን ዜና የሰሙ አብዛኞቹ የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አስተየት ሰጪዎች ለሟች ምሕረትን ለዘመድ ወዳጆቻቸዉን መፅናናትን ተመኝተዋል።«ነብስዎ በሰላም ትረፍ» ፣ «ነብስ ይማር» ና ወይም «RIP» የሚለዉ መልዕክት ብዙ ነዉ። አንድግመዉም።
ሞላ ማሩ ወሎ ግን ወደ ኋላ ሔዶ ሰኔ 2011 ባሕርዳርና አዲስ አበባ ላይ የተደረገዉን የባለስልጣናት ግድያ ያስታዉሳል።«ቀጣይ ሰኔ 15 /2015  ይደገማል» ብሎ በፌስ ቡክ።ዲሌዋን ጁ በራ-ግን የገዳዮች ማንነት አልታወቀም መባሉ ሳያስገርማት አይቀርም።«ባልታወቁ ታጣቂዎች ማለት!?» ትጠይቃለች-በቃለ አጋኖ ምልክት አዳምቃ በፌስ ቡክ።ቀጠለች «እዛ አከባቢ ከአማራ ውጭ ሌላ ማህበረሰብ ወይም ብሄር አለ እንዴ !?» እንደገና ጥያቄ።አዳሙ ቤንያ  ምክር ቤት አለዉ «የመገዳደል ጉጂ ባህል መወገድ አለበት» የሚል

እዉነት ዘገየ በፌስ ቡክ በእንግሊዝኛ ባሰፈረዉ አስተያየት «ይሕቺ ሐገር ምንነካት፣ አንድ ርምጃ ወደፊት ሶስት ርምጃ ወደ ኋላ እየሔድን ነዉ።ወደ ሕሊናችን መመለስ አለብን።ይሕ እብደት ነዉ።መረገም አለበት።» የእዉነት ዘገየ አስተያየት ነዉ።አንዱዓለም ፍሰሐ ምንዳዬ እሱም በፌስ ቡክ አጭር ጥያቄ አለዉ «መንግስት አለ?» የሚል።
                                   
ወደ ሁለተኛዉ ርዕስ እንለፍ።የኢትዮጵያ ሠራተኞች ባለፈዉ ሰኞ (ሚያዚያ 23) የዋለዉን የሠራተኞች ቀን አዲስ አበባ ዉስጥ በአደባባይ ሰልፍ ለማክበር የነበራቸዉ ዕቅድና ፍላጎት ስላልተፈቀደላቸዉ ከሽፏል።የዕለቱ ዕለት ከወደ ደቡብ መሰማት የነበረበት ዜና የአዲስ አበባዉን ቅሬታ የሚያለዝብ፣በተለይ ቱጃር ቅንጡዎችን የሚያስደስት የመዝናኛ ሥፍራ ምረቃ መሆን ነበርበት።በርግጥም ሐላላ ኬላ የተባለዉ የተመቻቸዉ የሚዝናኑበት ሥፍራ ተመርቋል።በምረቃዉ ሥርዓት ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አሕመድ ባስተላለፉት መልዕክት «ኢትዮጵያዉያን ያልሆኑ» ያሏቸዉ ወገኖች «በኢትዮጵያ ጉዳይ መፈትፈት እንዲያቆሙ» ማስተጠንቀቃቸዉ ግን የምረቃ-ደስታ ትችቱን ሁሉ በጥያቄ ቀይረዉ።«እነማን ይሆኑ» በሚል ጥያቄ።
ተመስገን በትዊተርና በእንግሊዝኛ «መልሱን እያወቃችሁ ለምን ትጠይቃላችሁ» ይልና ይመልሳል-«ኤርትራ» ብሎ።ሙኡዝም በትዊተር ግን ባማርኛ «የኤርትራ መንግስት እና ኤርትራውያን» ይላል ኦሜድላ ግን አይቀበለዉም «ማንም ያልተጋበዘ እንግዳ እስከ ሆነ ድረስ በኢትዮጵያ ጉዳይ ጣልቃ እየገባ ነው ለማለት እንደፍራለን። ኤርትራ ግን ተጋብዛለች።»ኦሜድላ ነዉ በትዊተር።
ቦ ጊዜ ለኩሉ ደግሞ በፌስ ቡክ ይጠይቃል «አይ!! ኢሱም ፅንፈኛ ተባለ?»፣ እምነት ተስፋ ፍቅር «አሜሪካ የላከችው ሆኖ ነው አትፍረዱበት ከኤርትራ ህዝቦች ጋር ጥሩ ግንኙነት የነበረውን ህዝብ ዳግም ደም ልታቃባው እየተንደረደረች ነው» ይላል ወይም ትላለች-በፌስ ቡክ።
ስቴፋን ሐበሻ ማስጠንቀቂያዉ ለኤርትራ ነዉ የሚለዉን አይቀበለዉም።«ሱዳንና ግብፅ የት ሄደው። ኢሳያስ ቀጥተኛ ሰው ነው» እያለ ይቀጥላል።ድምክልይ ድብሌይ የሚል የፌስ ቡክ ያለዉ አስተያየት ሰጪም ከስቴፋን ጋር ተቀራራቢ አስተያየት አለዉ «ግብፅ ናት» ይላል በእንግሊዝኛ።
ሐና ተክሌ ግን በፌስ ቡክ «ሊፋቱ ትንሽ ቀን ነው የቀራቸው» ግን ልክ እንደ ጠቅላይ ሚንስትሩ ስም አልጠቀሰችም።ብቻ ቢንያም ተሰማ ለሐና መልስ አለዉ።«ዝም ብሎ መፋታት የለም፤ድርሻዬን ስጡኝ ማለቱ አይቀርም» የሚል ምፀት ብጤ መልስ።
የኢትዮጵያ መንግስትና መንግስት ኦነግ ሸኔ በሚል ስም በአሸባሪነት የፈረጀዉ ግን ራሱን የኦሮሞ ነፃ አዉጪ ሠራዊት (ኦነሠ) የሚለዉ አማፂ ቡድን ተወካዮች ለዘጠኝ ቀናት ያደረጉት ድርድር ባለፈዉ ሮብ ተጠናቅቋል።ዛንዚባር ታንዛኒያ ዉስጥ በዝግ የተነጋገሩት የሁለቱ ወገኖች ተወካዮች በየፊናቸዉ ባወጡት መግለጫ እንዳሉት ድርድሩ ለወደፊት ይቀጥላል ከሚል ተስፋ ባለፍ የደረሱበት ሁነኛ ስምምነት የለም።ወደፊት የሚቀጥልበትን ጊዜ፣ የተግባቡበትንም ሆነ የተፋረሱበትን ምክንያትም በይፋ መናገር አልፈጉም።
መስፍን ብሩ በትዊተር ይጠይቃል «የተስማማችሁባቸውንና ያልተስማማችሁባቸውን ነጥቦች ለምን ለኢትዮጵያ ህዝብ ግልጽ አታደርጉም?» ሌላም ሁለት ጥያቄዎች አሉት።ቤካ ቤካ እሱም በትዊተር ግን በእንግሊዝኛ አንድ አራት ጥያቄዎች ደርድሯል «እንዳትስማሙ ያደረጋችሁ ምክንያት ምድነዉ?»-ጥያቄ አንድ።ኦሮሚያን ነፃ ማዉጣት? ጥያቄ-ሁለት ኦነግ (ኦነሠ አላለም) አሁን የሚፈልገዉ ነዉ»---እየጠየቀ እየመለሰ ቀጠለ። 
ቤቲ ታደሰ «ቀልዳቸው ደስ ይላል» ትላለች።«ሲጀመር» ቀጠለች የጭቃ ጅራፏን «የአብይ መንግስት እራሱ ሸኔ ነው»
ሊዲያ ሐበሻ ለረጅም ጊዜ የዶቸ ቬለ የቀጥታ ስርጭት ተከታታይ ነች።«መቼም እነስም አይጠሬ ፀጉራቸውን ነሰነሱብን አይደል ይገባቸዋል» አለች በፌስ ቡክ።
ያደታ የሚል የትዊተር ስም ያለዉ አስተያየት ሰጪ የኢትዮጵያ መንግስትን ይወቅሳል።ረዘም ካለዉ  አስተያየት ጥቂቱን እንጥቀስ።«ከመጀመሪያዉ ጀምሮ ጦርነቱን የፈለገዉ መንግስት ነዉ።ይህ የታንዛኒያዉ ድርድር ሲካሄድ እንኳ ተመስክሯል።አዲስ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ የፌደራል ፖሊስና የመከላከያ ወታደሮች ወደ ከፊል ኦሮሚያ እየዘመቱ ነዉ» እያለ ይቀጥላል።
አባይ አየነዉ ግን እሱም በፌስ ቡክ «አምሪካ የለችበትም ማለት ነዉ?» ይጠይቃል።መለሰም «ከወያኔጋም ዋናዋ ተዋናይ አመሪካ ነች» የአባይ አየነዉ ጥያቄና መልስ ነዉ።መሳይ መኒሳ በትዊተር የመብት ጥያቄ አለዉ።«የእነሱ ጥያቄ ምንድነዉ? ግልፅ አድርጉልን።ያልተስማማችሁበትን ማወቅ መብታችን መሰለኝ።» 
ከአራተኛና መጨረሻዉ ርዕስ ላይ ደርሰናል።የጀርመን መራሔ መንግስት ጉብኝት።መራሔ መንግስት ኦላፍ ሾልስ በኢትዮጵያና በኬንያ የሚያደርጉትን የሶስት ቀናት ጉብኝት ትናንት ከአዲስ አበባ ጀምረዋል።ባለፈዉ ሮብ ስለ ጉብኝቱ በትዊተር ያሰራጨነዉን ዘገባ ያነበበዉ አብረሐም «እና ምን እናድርግ» ብሎ ነበር።ጌቱ ወንድ ወሰን ግን በፌስ ቡክ «ቶሎ ና እንጂ እየጠበቅንሕ» አለ።
መራሔ መንግስቱ አልዘገዩም ባሉት ቀን አዲስ አበባ ገቡ።ትናንት።የጉብኝቱ አላማ፣ የጀርመን ባለስልጣናት እንዳሉት ብዙ ነዉ።የኢትዮጵያ መንግስትና ሕወሓት የተፈራረሙስ የሰላም ስምምነት ገቢራዊነት፣ ሰብአዊ ርዳታ፣ የሱዳን ጦርነት፣ ንግድና የተፈጥሮ ጥበቃን ያካትታል።ሾልስ ትናንት አዲስ አበባ ሲገቡ የተቀበሏቸዉ የዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ደ ኤታ ብርቱካን አያኖ ናቸዉ።
የማሪያምነኝ የሚል የፌስ ቡክ ስም ያለዉ አስተያየት ሰጪ አቀባበሉ ያረካዉ አይመስልም «የአንድ ኃያል ሐገርን መሪ በአንድ ተራ ሚንስትር» ይላል የማሪያምነኝ ጥያቄ አዘል አስተያየት።

Symbolbild Soziale Netze
ምስል Axel Heimken/dpa/picture alliance
የጀርመን መራሔ መንግስት ኦላፍ ሾልስና የአፍሪቃ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ
የጀርመን መራሔ መንግስት ኦላፍ ሾልስና የአፍሪቃ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪምስል Michael Kappeler/dpa/picture alliance

አስናቀ አጥናፉም ይጠይቃል-አቀባበሉን። «ምነዉ» እያለ  በፌስ ቡክ።የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር፣ ምክትላቸዉ፣ፕሬዝደንቷ የትሔዱ እያለ? የደረጀ ዮናስ አስተያየትም ተመሳሳይ ነዉ።«የሐገር መሪን በሱ ደረጃ ያለ ሰዉ መቀበል ነበረበት።ይኸ ጥሩ አይመስለኝም።-ደረጀ ዮናስ ነዉ-ይሕን ባዩ በፌስ ቡክ።መራሔ መንግስት ሾልስ ቦርሳ ይዘዉ የተነሱትን ፎቶ ያየዉ ዱብሮ ቭስኪ በፌስ ቡክ እንዲሕ ይላል«ቦርሳዉን ለምን እኔ አልይዝላቸዉም»
አበቃን።

ነጋሽ መሐመድ ነኝ

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር