1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቤኒሻንጉል ክልል ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የምርጫ ጥሪ

ሰኞ፣ መጋቢት 18 2015

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት እስከ ግንቦት 30 2015 ዓ.ም በክልሉ ምርጫ እንዲካሄድ ጥሪ አቀረበ፡፡ በምርጫ ቦርድ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ቀረበ የተባለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ምክረ ሀሳብ እንዳልደረሰው ጠቋሟል፡፡

https://p.dw.com/p/4PJ6z
Äthiopien Benishangul Region, Stadt  Metekel
ምስል Negassa Dessakegen/DW

ሰባት የፖለቲካ ፓርቲዎችን ያቀፈው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች ምክር ቤት

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት እስከ ግንቦት 30 2015 ዓ.ም በክልሉ ምርጫ እንዲካሄድ ጥሪ አቀረበ፡፡ በክልሉ ባለፉት ዓመታት በጸጥታ ችግር ምክንያት ምርጫ ሳይካሄድ የቆየ መሆኑን የጠቀሰው ምክር ቤቱ ክረምቱ ከመግባቱ በፊት ምርጫ ተካሂዶ በክልሉ ህጋዊ መንግስት እንዲደረጅ የሚል ምክረ ሀሳብ ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አቅርቧል፡፡ በምርጫ ቦርድ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ቀረበ የተባለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ምክረ ሀሳብ እንዳልደረሰው ጠቋሟል፡፡

Äthiopien | Babekir Halifa,Asosa
ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልምስል Negassa Desalegn/DW

ሰባት የፖለቲካ ፓርቲዎችን ያቀፈው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች ምክር ቤት በክልሉ ሰላም በመስፈኑ ምርጫ እንዲካሄድ ምክረ ሀሳብ አቅርቧል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምክር ቤት ስራ አስፈጻሚ አባል የሆኑት አቶ ዩሐንስ ተሰማ በ2013 ዓ.ም ሰኔ ወር በክልሉ አሶሳ ዞን ተካሂዶ የነበረው ምርጫ በመሰረዙ በክልሉ  እስካሁን ህጋዊ መንግስት አለመደራጀቱን አመልክተዋል፡፡ በክልሉ አብዛኛው ስፍራዎች ሰላም በመስፈኑ በሚቀጥሉት 3 ወራት ውስጥ በክልሉ ምርጫ እንዲካሄድ የጋራ ምክር ቤቱም ለምርጫ ቦርድ ምክረ ሀሳብ ማቅረቡን ጠቁመዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ አዳድስ ዕጮዎችን ለማቅረብ ቦርዱ እንዲፈቅዳላቸው ም/ቤቱ ባቀረበው ምክረ ሀሳብ ተካተዋል፡፡

ያነጋገርናቸው የአሶሳ ከተማ ነዋሪዎችም በክልሉ እንደሌሎች አካባቢዎች ምርጫ እንዲካሄድ ሀሳባቸውን አቅርቧል፡፡ በ2013 ዓ.ም በተካሄደው ምርጫ የተፈጠሩ ስህተቶችን በማረም ዳግም በክልሉ በፈጥነት ምርጫ መካሄድ እንደነበረበትም ነዋሪዎች አክለዋል፡፡

Young Graduates in  Benishangul Gumuz Complain of unemployment
ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልምስል Negassa Desalegn/DW

በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ታደሰ ለማ ምክር ቤቱ አቀረብኩ ያለው ምክረ ሀሳብ እንዳልደረሳቸው ጠቁመዋል፡፡ ምክር ቤቱ የሚያቀርበው ምክር ሀሳብ ለቦርዱ ድጋፍ እንደምሆንም ገልጸዋል፡፡

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በ2013 ዓ.ም በአሶሳ ዞን ምርጫ ተካሂዶ የነበረ ሲሆን በወቅቱ ባጋጠመው የኮድ ስህተት ምርጫ ለጊዜው መቋረጡ ተገልጾ ነበር፡፡ በክልሉ መተከል እና ካማሺ ዞን ደግሞ በጸጥታ ችግር ምክንያት ምርጫ ሳካሄድ ቆይቷል፡፡ በክልሉ ብልጽግና ፓርቲን ጨምሮ ሰባት የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

 

ነጋሳ ደሳለኝ

 

አዜብ ታደሰ

ዮኃንስ ገብረግዚአብሔር