1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጀርመን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ወቀሳ

ሐሙስ፣ ሐምሌ 18 2011

የአዲስ አበባ ባለአደራ ም/ቤት የተባለው ስብስብ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ኤርሚያስ ለገሠ የሚገኙባቸውን እነዚህኑ መድረኮች «የተደራጁ ኃይሎች»ያሏቸው እንደሚረብሹ ለአዘጋጆቹ ማስጠንቀቂያዎች ልከዋል።የኢትዮጵያ ኤምባሲ ሠራተኞች ሲሉ የገለጹዋቸው በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች «የባልደራስ አባላት መድረክ ሊሰጣቸው አይገባም በማለት ጽፈዋል»ሲሉም ወቅሰዋል።

https://p.dw.com/p/3MkJG
Berlin Brandenburg Gate (Brandenburger Tor)
ምስል picture-alliance/robertharding/M. Lange

የባልደራስ የአውሮጳ መድረክ አዘጋጆች ነን የሚሉ ኢትዮጵያውያን ወቀሳ

ጀርመን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን  በፍራንክፈርት እና በበርሊን እንዲሁም በሌሎች የአውሮጳ ከተሞች  በዚህ ሳምንት መጨረሻ ሊያደርጉ ያቀዱትን ውይይት ፣እንደሚያውኩ «የተደራጁ ኃይሎች» ካሏቸው ኢትዮጵያውያን  ዛቻ እና ማስፈራሪያ እንደደረሳቸው አስታወቁ። የመድረኩ አዘጋጆች ነን የሚሉት ለዶቼ ቬለ DW፣ እንደተናገሩት እነዚሁ «የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ» ደጋፊ ነን የሚሉ ኃይሎች የአዲስ አበባ ባለአደራ ምክር ቤት የተባለው ስብስብ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ኤርሚያስ ለገሠ የሚገኙባቸውን እነዚህኑ መድረኮች እንደሚረብሹ ለአዘጋጆቹ በተለያየ መንገድ ማስጠንቀቂያዎች ልከውላቸዋል። በጀርመን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ሠራተኞች ሲሉ የገለጹዋቸውም በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች «የባልደራስ አባላት መድረክ ሊሰጣቸው አይገባም የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል»ሲሉም ወቅሰዋል።

አዘጋጆቹ በስም የጠቀሷቸውን የኤምባሲውን ባልደረባ ለማነጋገር በተደጋጋሚ ብንደውልም ልናገኛቸው አልቻልንም። የባልደራስ የአውሮጳ መድረክ አስተባባሪዎች  ለቅዳሜ ሐምሌ 20፣2011 ዓም በፍራንክፈርት፣ በማግሥቱ ለእሁድ ሐምሌ 21፣2011 ዓም በበርሊን ስብሰባ ለማድረግ ነው ጥሪ ያስተላለፉት።አቶ ሱራፌል አስፋው ከባልደራስ የአውሮጳ መድረክ አስተባባሪዎች አንዱ መሆናቸውን ተናግረዋል። ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የበርሊኑ መድረክ አስተባባሪ ነኝ ያሉ ግለሰብ ለዶቼቬለ እንደተናገሩት የባልደራስን አቋም ይቃወማሉ የተባሉት እነዚሁ ኢትዮጵያውያን ስብሰባው ሊካሄድበት የነበረው አንድ ምግብ ቤት ድረስ በመሄድ ዝግጅቱ በዚያ እንዳይደረግ ባለቤቶቹን አስጠንቅቀዋቸዋል።የምግብ ቤቱን ባለቤት ስለ ጉዳዩ ለማነጋገር በተደጋጋሚ ስልክ ብንደውልም መልስ አልሰጡንም።የበርሊኑ መድረክ አዘጋጆች ስብሰባውን በሌላ ቦታ እንደሚያካሂዱ እና የፖሊስ ጥበቃም እንደሚጠይቁ ገልጸዋል። የፍራንክፈርቱ ስብሰባ አዘጋጆች በበኩላቸው ጉዳዩን ወደ ሕግ እንደሚወስዱት እና ለቅዳሜው ስብሰባቸው ጥበቃ እንዲደረግላቸው ለፖሊስ እንደሚያሳውቁ ተናግረዋል።

Deutschland Frankfurt Skyline
ምስል Getty Images/R. Orlowski

በአስተባባሪዎቹ በስም ከተጠቀሱት አንዱ በጀርመን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ባልደረባን በኤምባሲው ማዞሪያ፣ በቀጥታ ስልካቸው እና በእጅ ስልካቸው ላይ ተደጋጋሚ ጥሪ ብናደርግም ስልኮቹ ባለመነሳታቸው ልናገኛቸው አልቻልንም። ለበርካታ ዓመታት በጀርመን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚቴ ሰብሳቢነት የሰሩት አቶ ስዩም ሃብተ ማርያም የበርሊኑን እና የፍራንክፈርቱን ስብሰባዎች ለማደናቀፍ ተደረጉ የተባሉትን ሙከራዎች  ሕገ ወጥ እና በጀርመን ሕግም የሚያስጠይቁ ብለዋቸዋል።ዓላማችን በሰላማዊ መንገድ ሃሳብ መለዋወጥ ነው የሚሉት የቅዳሜ እና የእሁዱ የፍራንክፈርት እና የበርሊኑ መድረክ አዘጋጆች፣ ተቃዋሚዎች ከዛቻ እና ማስፈራራት ይልቅ በመድረኩ ተገኝተው ቢሞግቱ መልካም ይሆን ነበር ብለዋል።

ኂሩት መለሰ

ተስፋለም ወልደየስ