1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የባህርዳሩ አማራ ክልል ምሁራን መማክርት ጉባዔ 

ዓርብ፣ መስከረም 9 2012

መንግስት ከምሁራን ጋር ተባብሮ ባለመስራቱ ችግሮችን የማቃለል እድል ሳይኖረው መቆየቱ ተነገረ። ይህ የተገለፀዉ በባህር ዳር ዛሬ በተጀመረው የአማራ ክልል ምሁራን መማክርት ጉባዔ ላይ ነዉ። ከመክፈቻ ንግግሮች በኋላ ዉይይቱ ለጋዜጠኞች ዝግ በመሆኑ የዉይይቱ ይዘት በርግጥ ምን ላይ መሆኑ ለማወቅ አለመቻሉ ተመልክቶአል። 

https://p.dw.com/p/3Pxa3
Äthiopien | Grundschulen in Amhara Region
ምስል DW/A. Mekonnen

መንግስት ከምሁራን ጋር ተባብሮ ባለመስራቱ ችግሮችን የማቃለል እድል ሳይኖረው መቆየቱ ተነገረ። ይህ የተገለፀዉ በባህር ዳር ዛሬ በተጀመረው የአማራ ክልል ምሁራን መማክርት ጉባዔ ላይ ነዉ። በጉባዔዉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንንን ጨምሮ የክልልሉ ዋና መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ ምሁራን ተሳታፊ ናቸዉ። ጉባዔዉ ከመክፈቻ ንግግሮች በኋላ ዉይይቱ ለጋዜጠኞች ዝግ በመሆኑ የዉይይቱ ይዘት በርግጥ ምን ላይ መሆኑ ለማወቅ አለመቻሉ ተመልክቶአል። የአማራ ክልል ምሁራን መማክርት ጉባዔ በ2010 ዓም ነሀሴ ወር ላይ ተቋቋመ ሲሆን ዋና ዓላማውም የአማራ ክልል ህዝቦችንና ተወላጆችን አንድነት ለማጠናከርና በአገር ልማትና በዴሞክራሲ ግንባታ የምሁራንን ተሳትፎ ለማሳደግ እንደሆነ የመማክርት ጉባዔው ሰብሳቢ ዶክተር ገበያው ጥሩንህ ተናግረዋል፡፡ ለአገራችን የሚበጃት መገፋፋትና መነቃቀፍ ሳይሆን ትብብርና ቅርርብ አንደሆነም ነው ዛሬ በባህር ዳር በተጀመረው የአማራ ክልል ምሁራን መማክርት ጉባዔ ላይ ያመለከቱት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ በበኩላቸው ክልሉ በርካታ ስመ ጥር ምሁራንን ያፈራ ቢሆንም ለህዝቡ አንዳችም ለውጥ እንዳላመጡ ጠቁመዋል፡፡ ያስተመራቸው ህብረተሰብ አሁንም ከሺህ ዓመታት በፊት ይጠቀምበት የነበረውን የስራ መሳሪያ እየተጠቀመ መሆኑን አመልክተው አሁን ግን ምሁራን  በቁጭት ሊነሱና ለውጥ ሊያመጡ ይገባል ብለዋል፡ ፉክክራችንም ከጎረቤቶቻችንና ከወገኖቻችን ሳይሆን ከድህነታችን ጋር ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡ በክብር እንግድነት የተገኙት የኢፌድሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስተር አቶ ደመቀ መኮንን እንዳሉት ቀደም በሉት ዓመታት መንግስትና ምሁራን ተቀራርበው መስራት ባለመቻላቸው በቀላሉ ሊፈቱ የሚችሉ ችግሮች ሳይፈቱ ቆይተዋል ሲሉ አስታውሰዋል፡፡ አሁንም በርካታ ያልተፈቱ ችግሮች በክልሉ መኖራቸውን የተናገሩት አቶ ደመቀ ምሁራን ዉለታ የምትከፍሉበት ሳይሆን በሙያችሁ ያለባችሁን ኃላፊነት የምትወጡበት አጋጣሚ በመሆኑ በምርምርና በጥናት ላይ ተመስርታችሁ ችግሮችን ፍቱ ነው ያሉት፡፡ በጉባዔው 4 ጥናታዊ ጽሁፎች የቀረቡ ቢሆንም ከመክፈቻ ንግግሮች በኋላ ውይይቱ ለጋዜጠኞች ዝግ በመሆኑ ይዘታቸውን ማወቅ አልተቻለም፡፡ ጋዜጠኞች መቅረፀ ድምፅና ሞባይል ስልክ ይዘው እንዳይገቡ በመከልከላቸው መሳሪዎችን ተጠቅመው ፎቶግራፍ፣ ቪዲዮና ድምፅ ለማውድ ሲቸገሩም ተስተውሏል፡፡

ዓለምነዉ መኮንን 

አዜብ ታደሰ 
ኂሩት መለሰ 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ