1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቢያፍራ ጦርነት 50ኛ ዓመት

ቅዳሜ፣ ጥር 9 2012

ናይጀሪያ በዚህ ሳምንት ረቡዕ ዕለት ከአንድ ሚሊየን በላይ ሕዝቧን የፈጀውን የቢያፍራ ጦርነት 50ኛ ዓመት አስባለች። የጦርነቱ ጦስ ለቋት ይሆን? የአንበጣ መንጋ የምሥራቅ አፍሪቃ ሃገራትን አሁንም መውረሩን ቀጥሏል። ከኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ወደ ኬንያ ተዛምቷል። የዕለቱ ትኩረት በአፍሪቃ መሰናዶ ይህን ያስቃኛል።

https://p.dw.com/p/3WNjJ
Bildergalerie Biafra-Krieg
ምስል Getty Images/AFP

ትኩረት በአፍሪቃ

በ30 ወራት ውስጥ ከ1 እስከ 2 ሚሊየን የሚገመቱ ሰዎች ያለቁበት የናይጀሪያው የቢያፍራ ጦርነት በዚህ ሳምንት ረቡዕ ዕለት 50ኛ ዓመቱ ታሰበ። በአብዛኛው ልጆች ያለቁበት የዚህ ጦርነት መዘዝ ዛሬም ናይጀሪያን እንዳልለቀቃት ነው የሚነገረው። ዑቼና ቺክዋንዱ ስለጦርነቱ እጅግም አያወሩም። አሁን የ67 ዓመት የዕድሜ ባለፀጋ የሆኑት ቺክዋንዱ በምሥራቅ ናይጀሪያዋ ግዛት ኢኑጉ ነዋሪ ናቸው። በጎርጎሪዮሳዊው 1970 ጥር 15 ቀን የተጀመረው የእርስ በርስ ጦርነት ሲካሄድ አፍላ ወጣት ነበሩ። አንድ ነገር ግን ዛሬ ድረስ አልረሱም። «መኪና ስላልነበረ በየጊዜው ረዥም መንገድ መጓዝ ነበረብን። መኪና ያለው ሰው ከኖረም መደበቅ ይኖርበታል ምክንያቱም ወታደሮች ካገኙ ይወስዱበታል። ቀላል ጊዜ አልነበረም። ለምሳሌ በጫካ ውስጥ በጠባብ መንገዶች እየሾለክን ነበር የምንሄደው፤  ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ተነስተን ከንጋቱ 11 ሰዓት ገበያ እንደርሳለን። ከዚያም የምንገዛውን በፍጥነት ሸምተን ሳያዩን ተደብቀን ቶሎ ወደቤታችን እንመለሳለን።»
250 ጎሳዎች የሚገኙባት ናይጀሪያ ከታላቋ ብሪታንያ ቅኝ ተገዢነት ነፃየወጣችው በጎርጎሪዮሳዊው 1960 ነው። ያኔም ቢሆን ከ45 ሚሊየን የሚበልጥ ሕዝብ ነበራት። አብዛኞቹ ሃውሳ፣ እና ፊላኒ በስተሰሜን፤ ዩሩባዎች በምዕራብ እንዲሁም ኢግቦዎች ደግሞ በምሥራቅ ይገኛሉ። ከቅኝ ግዛት ወጥተው ነፃነታቸው ካገኙ በኋላ ብዙም አልቆዩም በቡድን ተከፋፍለው ለሥልጣን እና ለተፈጥሮ ሃብት ቅርምትእንዲሁም ለሌሎች ጥቅማ ጥቅሞች መሻኮት መጋጨት ሲጀምሩ። ያኔም ሁለት ጊዜ መፈንቅለ መንግሥት ተካሂዷል። የመጀመሪያው ከሀውሳ ጎሳ የመጡት ጠቅላይ ሚኒስትር አቡባከር ታውፋ ባላዋ በወታደሮች አመፅ ሲገደሉ፤ ጆንሰን አጉይ ኢሮንሲ ሥልጣን ያዙ። ከስድስት ወራት በኋላ «የሐምሌ ዳግም ዘመቻ» በመባል የሚታወቀው የአፀፋ መንግሥት ግልበጣ ተካሄደ። በዚህ መፈንቅለ መንግሥት ተሳታፊዎች አብዛኞቹ ከሰሜን ናይጀሪያ የሆኑ ጀነራሎች ናቸው። በጎርጎሪዮሳዊው 1967 ግንቦት 30 ቀን የምሥራቃዊ ናይጀሪያ አገረ ገዢ የነበሩት ጀነራል ቹክዌሜካ ኦዱሜጉ ኡኩኩዋ ከፍተኛ የጎሳ ጥቃት ከታየበት አመፅ በኋላ የአካባቢውን ነፃ ግዛትነት አወጁ። 
በኢባዳን ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ፕሮፌሰር የሆኑት ኢግሆሳ ኦሳጋሄ እንደሚሉት 500 ሺህ እስከ 3 ሚሊየን የሚገመቱ ዜጎች ያለቁበት ጦርነት መዘዝ ዛሬም ያን ያህል አልተለወጠም። ስለናይጀሪያ የውስጥ መከፋፈል ፕሮፌሰሩ ሲናገሩ እንዲህ ነው የሚሉት። «ሰዎች ዛሬም ደቡብ ምሥራቅ የሀገሪቱ ክፍል አሁንም በጣም የተገለለ ወይም ምንም አቅም የሌለው አድርገው ይገምታሉ። ይህ ደግሞ ለእርስ በርስ ጦርነት አንዱ መዘዝ መሆኑ አይቀርም። ይህ ደግሞ በዋነኛነት ያለ የብዙዎች ግንዛቤ ነው።» በእርግጥም እሳቸው የሚሉትን ዑቼና ቺክዋንዱ በምሳሌነት ያሳያሉ።  ቺክዋንዱ እንደሚሉት ከናይጀሪያዊነታቸው ይልቅ ጎሳቸው ለልባቸው ቅርብ ነው። 
«ናይጀሪያዊነት በፍፁም አይሰማኝም። የምደሰተው ኢግቦ በመሆኔ ብቻ ነው። ናይጀሪያ? ይህ ለኔ የሚሰጠኝ ምንም ነገር የለም። ለእኔ ናይጀሪያ የሚባል ነገር የለም። ናይጀሪያዊ በመሆን የምኮራበት ምንም ነገር የለም።»
በዚህ መሃል ሚሊዮኖች ከቦታ ቦታ በብዛት ይንቀሳቀሳሉ። የመንቀሳቀሳቸው ዋና ምክንያት ደግሞ ጦርነቱ እንኳ ሊያስቆመው ያልቻው፤ ንግድ ነው። በርካታ የሀውሳ ጎሳ አባላት ኢኑጉ ውስጥ በኦጉይ ጎዳና አካባቢ ይኖራሉ። የእነሱ ሳሪኪ ማለትም ንጉሣቸው አቡበከር ዩሱፍ ሳምቦ ቤተሰቦች ከአዳማዋ ወደ ኢኑጉ የመጡት ከመቶ ዓመታት በፊት ነው። ሃውሳ በመሆኑ ምንም የመገለል ስሜት እንደማይሰማው ነው የሚገልፀው። «ከጦርነቱ በኋላ ብዙ ሰዎች ከሰሜን ወደዚህ በፍጥነት ተመለሱ፤ ልክ ኢግቦዎች ወደሰሜን እንደሄዱ ማለት ነው። ዕድሜ ዘመኔን እዚሁ ኢንጉ ውስጥ ነው ያሳለፍኩት። እዚሁ ነው ያደኩት፤ ይህ ነው የእኔ ማኅበረሰብ፣ እዚሁ ነው የተማርኩት። በራሴ ግዛት አዳማዋ ካሉት ይልቅ ከኢንጎ ማኅበረሰብ ነው በርካታ ጓደኞች ያፈራሁት። እዚህ ይመቸኛል።»
 በሌላ በኩል የናይጀሪያ የውስጥ ፖለቲካ እጅግ ስሱ ነው። በተለይ ደግሞ የተፈጥሮ ሃብት ድርሻን የማግኘቱ ነገር ከፍተኛ ፉክክር እና ትግል ያለበት ነው። ፕሮፌሰር ኢግሆሳ ኦሳጋሄ ይህና ተያያዥ ፉክክሮች ለእርስ በርስ ጦርነት መንስኤ መሆናቸውን ያስረዳሉ። «ከሌሎች ጉዳዮች መካከል ሥልጣንን ሚዛናዊ የማድረጉ ነገር ወደየእርስ በርስ ጦርነት የሚከት ነው። ችግሩም ተባብሶ መቀጠሉንና የጦርነቱ ጦስም ዛሬም የናይጀሪያውያንን ግንኙት ፈርጅ እያበጀለት መሄዱንም ያመለክታሉ። ይህ ደግሞ በእርግጥም እሳቸው እንደሚሉት የፖለቲካ ሥልጣኑን በሚይዙት ሰዎች ማንነት የሚታይ ነው። ባለፈው ዓመት ፕሬዝደንት ሙሀማዱ ቡሀሪ ለሰሜን ናይጀሪያ ያደላሉ በሚል ክስ ቀርቦባቸዋል። ብዙሃን የሆኑት የሁሉም ዕድገት ምክር ቤት ፓርቲ APC እና የሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ PDP ሁሌም ቢሆን ፕሬዝደንታዊ እጩ ለማቅረብ ጠንክረው ይሠራሉ፤ በዚህም ሰሜኑ እና ደቡቡ፤ እግረመንገዱንም ሙስሊሙ እና ክርስቲያኑ ማኅበረሰብ መወከሉን ያረጋግጣሉ። እንዲህም ሆኖ ጥቂት የናይጀሪያ ማኅበረሰብ አይካተትም። ለምሳሌ በቀድሞዋ ቢያፍራ ግዛት ናይጀሪያ በታሪኳ ከኢግቦ የመጣ ፕሬዝደንት ሰይማ አታውቅም በሚል ይተቻሉ። ብዙዎቹ የመገፋት ስሜት ስላላቸው፤ የራስገዝነት ሃሳብን ለሚያቀነቅኑ እንደተጨማሪ ኃይል እያገለገሉ ነው። የቢያፍራ ጥንታዊ ሕዝቦች ንቅናቄ የሚባለው ለምሳሌ በቀላሉ ደጋፊዎችን ከእነዚህ ወገኖች ማግኘት አይከብደውም። ነገር ግን የአቡጃ በፍርድ ቤት ይህን ድርጅት በጎርጎሪዮሳዊው 2017 ዓም አሸባሪ ብሎ ፈርጆታል። 
የሰዎቹ ግንዛቤ እና ያለው እውነታ
በጎርጎሪዮሳዊው 2015 ዓም በብሔራዊ ደረጃ የወጣ መዘርዝር በምሥራቅ እና ደቡብ ናይጀሪያ የትምህር፤ የፆታ እኩልነት እንዲሁም የድህነት ቅነሳው ጥረት ከሰሜኑ ጋር ሲነፃፀር የተሻለ መሆኑን ያመለክታል። ፕሮፌሰር ኦሳጋሄ ግን የሰዎች ግንዛቤ እና ያለው እውነታ እንደሚጣረስ ነው የሚናገሩት። በርካቶቹ የደቡብ ምሥራቅ ናይጀሪያ ነዋሪዎች ስለሰሜ አካባቢ የሚያውቁት ባለመኖሩ በዚያ አካባቢ ያለው ወገን በማንኛውም ረገድ ከሀገሪቱ ሀብት የአንበሳውን ድርሻ እንደወሰደ ነው የሚያስቡት። መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ዛሬም 95 ሚሊየን የሚሆኑት ናይጀሪያውያን በከፋ ድህነት የሚኖሩ ናቸው። የዛሬ 50 ዓመት በእርስ በርስ ጦርነት የተተራመሰችው ሀገር አሁን የሕዝቧ ቁጥር  199 ሚሊየን ቢገመትም  50 በመቶው ዜጋዋ በድህነት የሚማቅቅ ነው። የቢያፍራ ጦርነት ከቅኝ ግዛት ነፃ ከወጡ በኋላ የተከሰተ እጅግ አስከፊ የታሪክ ጠባሳ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ዛሬም መዘዙ ያልተገታ መሆኑ ራሱን እንዳይዘነጋ አድርጎታል። 
 
የአንበጣ መንጋ ስጋት በምሥራቅ አፍሪቃ

Flüchtling im Biafra-Krieg 1967 - 1970
ምስል OFF/AFP/Getty Images
Bildergalerie Biafra-Krieg | Port Harcourt
ምስል picture-alliance/United Archives/TopFoto
Bildergalerie Biafra-Krieg | hungernde Kinder
ምስል picture-alliance/Leemage/MP/Lazzero
Nigeria Erinnerungen Biafra-Krieg Kriegsmuseum von Umuahia
ምስል DW/K. Gänsler


የዓለም የምግብ እና እርሻ ድርጅት FAO በዚህ ሳምንት ባወጣው ማስጠንቀቂያ፤ አሁንም በርካታ እና እጅግ ብዙ የአንበጣ መንጋ ለምሥራቅ አፍሪቃ የምግብ ዋስትና ያልተጠበቀ ስጋት ማስከተሉን አመልክቷል። ምሥራቅ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ውስጥ ተበራክቶ የታየው የአንበጣ መንጋ ቀጣይ ጉዞውን ወደ ምሥራቅ እና ሰሜን ኬንያ አድርጓል። እንደ FAO ገለፃም ኬንያ ላይ የአንበጣው መንጋ በርዝመት 60 ኪሎ ሜትር ወደ ጎን ደግም 40 ኪሎ ሜትር ሸፍኖ ታይቷል። በሰሜን ምሥራቅ ኬንያ ማንዴራ፣ እንዲሁም ከኢትዮጵያ ጋር በሚዋሰነው አካባቢ ሞያሌ እና መርሳቤት አካባቢ የታየው አንበጣ ወደማዕከላዊ የሀገሪቱ ክፍልም ሊዛመት እንደሚችል አስጠንቅቋል።  
ልክ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ውስጥ ቀደም ባሉት ወራት ሲታይ እንደነበረው ግራ የተጋቡት የኬንያ አርሶ አደሮች የአንበጣው መንጋ ማሳቸው ላይ ሰፍሮ ሰብላቸውን እንዳያወድምባቸው ትግል ይዘዋል። በሁለቱ ሃገራት የአንበጣው መንጋ 70 ሺህ ሄክታር መሬትን የሸፈነ ሰብል ላይ ጉዳት ማድረሱ ተመዝግቧል። በአካባቢው ከ70 ዓመታት በኋላ የታየው አስከፊው የአንበጣ መንጋ ወረራ የምግብ እጥረት እንዳያስከትል ስጋት አለ። ኬንያም ጉዳዩ አሳስቧታል። እስከቅርብ ጊዜ ድረስ የሀገሪቱ የግብርና ሚኒስትር የነበሩት ማዋንጊ ኪውንጁሪ ከጎረቤት ሃገራት ወደኬንያ የገባው የአንበጣ መንጋ ያስከተለውን ስጋት ይናገራሉ።
«የመጀመሪያው የአንበጣ መንጋ ከሶማሊያ ወደ ኬንያ ድንበር አልፎ የገባው ታኅሣሥ 18 ነው። ሌሎች መንጋዎች ደግሞ ከኢትዮጵያ በኩል መግባት ቀጥለዋል፤ ከሶማሊያም ሁለተኛው ገብቷል። የመጀመሪያውን ወረራ በማስተዋልም መንጋው ሊሄድባቸው እንደሚችል በገመትናቸው አካባቢዎች  መድኃኒት ረጭተናል፤ የአንበጣ መንጋው ወረራም ያልተጠበቀ የምግብ ዋስትና ስጋት አስከትሏል።»
በከፊል ደረቅ በሆነው ሰሜናዊ ኬንያ የአንበጣው መንጋ ብዙ ሄክታር መሬት ላይ ያለውን ሰብል አውድሞ ወደ ደቡብ እና ምዕራብ ኬንያ አቅጣጫ ተምሟል። የኬንያ የግብርና ሚኒስቴር የመረጃ ማዕከል በማቋቋም የአንበጣውን ወረራ የመከላከል ሥራ እያከናወነ ነው። «መንግሥት ወዲያው ነው መንጋውን ለመቆጣጠር አስፈላጊያውን እንዲያደርጉ የቴክኒክ ባለሙያዎችን በማሰማራት ርምጃ የወሰደው። አየር እና ምድሩን የወረረውን መንጋ ለመመከትም የአካባቢውን ነዋሪዎችም እያሰለጠኑ ነው።» የአንበጣው መንጋ ኢትዮጵያ ውስጥም አቅጣጫውን እየቀያየረ የተለያዩ አካባቢዎችን መውረሩን መቀጠሉ ተሰምቷል። በግብርና ሚኒስቴር የእፅዋት ጤና እና ጥራት ቁጥጥር ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ወልደ ሐዋርያት አሰፋ የአንበጣው መንጋ አሁን የሚገኝባቸውን አካባቢዎች እና እየተከናወነ ያለውን ለዶቼ ቬለ እንደሚከተለው ገልፀዋል። የዓለም የምግብ እና የእርሻ ድርጅት FAO እንደሚለው ትርጉም ያለው የመከላከል ተግባር እየተከናወነ ቢሆንም አሁንም አንበጣው በቀይ ባሕር ዳርቻ መጠነ ሰፊ በሚባል ደረጃ መራባቱን መቀጠሉን አመልክቷል። 

Wüste Locust schwärmt in Nord- und Ost Äthiopien
ምስል Ethiopian Ministry of Agriculture
Somalia Heuschreckenplage Bauern
ምስል Reuters/F. Omar
Äthiopien Heuschreckenschwarm in Tigray
ምስል DW/M. Haileselassie

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ