1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቆላው ማሳ ኢትዮጵያን ስንዴ ከመሸመት ይታደጋታል?

ረቡዕ፣ ጥር 12 2013

"በመንግሥት ኢትዮጵያ ማምረት ያለባትን ከ17 እስከ 20 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ አፋር እና ሶማሌ ክልልን በመሳሰሉ ሞቃታማ የአየር ጠባይ ባላቸው አካባቢዎች በማምረት የአገሪቱን ፍላጎት ለማሟላት እየተሰራ ነው" የሚሉት የፖሊሲ ጥናት እና የቴክኖሎጂ ሽግግር አስተባባሪ አቶ ካሌብ ቀለሙ የታቀደውን ለማሳካት ግን በርካታ ሥራዎች መኖራቸውን አይሸሽጉም።

https://p.dw.com/p/3oBAW
Äthiopien Adama | Welt ohne Hunger | Traditionelle Weizenernte
ምስል Stefan Trappe/Imago Images

ከኤኮኖሚው ዓለም፦ የቆላው ማሳ ኢትዮጵያን ስንዴ ከመሸመት ይታደጋታል?

በሶማሌ ክልል ጎዴ እና ቤራኖ ወረዳዎች ስንዴ በመስኖ ለማምረት የተጀመረ ውጥን በባለሥልጣናት ሲጎበኝ የአካባቢው ወጣቶች እንግዶቹን እየጨፈሩ ነበር የተቀበሏቸው። በሞቃታማው ሶማሌ ክልል በምዕራብ ጎዴ የሸበሌን ወንዝ በመጥለፍ በሚለማው የእርሻ ማሳ በ500 ሔክታር መሬት ላይ ስንዴ ማምረት ተጀምሯል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ከሸበሌ ወንዝ ባሻገር በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች መሰስ ብለው የሚፈሱ እንደ አዋሽ ያሉ ወንዞች እና በአካባቢያቸው የሚገኙ የእርሻ ማሳዎች ላይ ጭምር አይኑን ጥሏል። ለዚህ ደግሞ በተንዳሖ በተደረገ ሙከራ የተገኘ አበረታች ውጤት አለ። በኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ካውንስል ሴክሬታሪያት የፖሊሲ ጥናት እና የቴክኖሎጂ ሽግግር አስተባባሪ አቶ ካሌብ ቀለሙ "ተንዳሖ አካባቢ የመስኖ መሠረተ-ልማት የተሟላለት የእርሻ መሬት አለ። እዚያ ላይ በምርምር የወጡ ዝርያዎችን በመጠቀም በሔክታር እስከ 45 ኩንታል ድረስ ተገኝቷል። ይኸን መጠን ያለው ስንዴ ከማግኘትም ባለፈ በአፋር አካባቢ የተወሰኑ የደረቅ ወራቶች የመኖ እጥረት አለ። አብዛኛው ማህበረሰብ በእንስሳት እርባታ ስለሚተዳደር ከዚያ የሚገኘውን ተረፈ-ምርት ለአርብቶ አደሩ እንስሳት መኖ ስለሚያገለግል ጥሩ አይነት ተፅዕኖ የሚፈጥር ሆኖ ነው የተገኘው" ሲሉ ተገኘ ያሉትን ውጤት አብራርተዋል።

ከአርሲ እስከ ጎዴ፣ ከተንዳሖ እስከ ደቡብ ኦሞ ሳያቋርጡ ከሚፈሱ ወንዞች በሚጠለፍ መስኖ ሊመረት የታቀደው ስንዴ እንደተወጠነው ከተሳካ ኢትዮጵያ በየአመቱ የገበያውን ፍላጎት ከውጪ ሸምታ ለመሙላት የምታወጣውን ከፍ ያለ ጥሪት ያስቀርላታል።

አቶ ካሌብ "ኢትዮጵያ ስንዴ የምታመርተው በደጋ እና በወይናደጋ አካባቢ ነው። ነገር ግን ትልልቅ የውኃ ሐብት እና ሰፊ የእርሻ መሬት ያለበት ቆላማ አካባቢ መስኖን በመጠቀም፣ የመዝሪያ ወቅትን በመለየት እና ተስማሚ የሆኑ በምርምር የወጡ ዝርያዎችን በመጠቀም ስንዴን ማምረት ይቻላል። በአፋር፣ በሶማሌ እና በደቡብ ኦሞ አካባቢዎች ትልልቅ ወንዞች አሉ። እነዚህን በመጠቀም ስንዴ ቢመረት አሁን በደጋው አካካባቢ እየተመረተ ካለው ተጨማሪ ያለውን አጠቃላይ አገራዊ የስንዴ ምርት አቅርቦት ክፍተት የሚያስችል ዕድል ስለሚሰጥ ነው።" ብለዋል።  

ስንዴ ሸማቿ ኢትዮጵያ

በጎርጎሮሳዊው 2020/21 ዓ.ም. የኢትዮጵያ አመታዊ የስንዴ ፍጆታ 6.7 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ይደርሳል ተብሎ እንደሚገመት የአሜሪካ ግብርና ቢሮ የአዲስ አበባ ፅህፈት ቤት ባለፈው መጋቢት ይፋ ያደረገው ሰነድ ይጠቁማል። በዚሁ ሰነድ መሠረት አገሪቱ በተመሳሳይ አመት ታመርታለች ተብሎ የሚጠበቀው ስንዴ እስከ 5 ሚሊዮን ቶን ይደርሳል። ምንም እንኳ በአመቱ ይመረታል ተብሎ የሚጠበቀው ከቀደመው አመት በ2 በመቶ ገደማ ከፍ ቢልም የአገሪቱን ገበያ ፍላጎት ግን አሁንም ማሟላት አይችልም። በቀደሙት አመታትም የኢትዮጵያ አመታዊ የስንዴ ምርት ፍጆታዋን መሙላት እየተሳነው መንግሥት ስንዴ ይሸምት ነበር። ዩክሬን፣ ሩሲያ፣ ሮማኒያ፣ ቡልጋሪያ፣ ቱርክ እና ግብጽ አገሪቱ ስንዴ ከምትሸምትባቸው አገራት መካከል ይገኙበታል። 

"በየአመቱ ኢትዮጵያ ከ500 እስከ አንድ ቢሊዮን ዶላር ድረስ ለስንዴ ግዢ የምታወጣበት ሁኔታ አለ።" የሚሉት አቶ ካሌብ ቀለሙ  "መንግሥት በተደጋጋሚ ይኸንን ፍላጎት ለማሟላት በየጊዜው ጨረታ እያወጣ፤ ብዙ ዶላር እየመገበ ይኸን ስንዴ ያስገባል። ነገር ግን አገር ውስጥ ለማምረት እና ለመተካት የሚያስችል አቅም እያለ፤ የምርምር ቴክኖሎጂ እያለ ውጪ ሔዶ መግዛት አዋጪነት ስለሌለው መንግሥት ይኸንን ነገር ተገንዝቦ ከጠቅላይ ምኒስትሩ ጀምሮ የሚመለከታቸው ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች በቅርብ እየተከታተሉት ይኸንን ስንዴን በቆላማ አካባቢ የማምረት ሥራ ከሶስት እና አራት አመታት በፊት በስፋት እየተከናወነ ይገኛል" ሲሉ የኢትዮጵያን ውጥን አስረድተዋል።   

ደገኛው ስንዴ በኢትዮጵያ

Initiative Seeds for Needs
ባለሙያዎች እንደሚሉት ከዓለም ከ70 በመቶ በላይ የሚሆነው ስንዴ በቆላማ አካባቢዎች የሚመረት ቢሆንም በኢትዮጵያ ግን የለየለት ደገኛ ነውምስል Bioversity International/C. Fadda

አፋር እና ሶማሌ ክልሎችን ጨምሮ በቆላማ አካባቢዎች የሚገኙ የእርሻ ማሳዎች ዋንኛ ምርት የቅባት እህሎች እና ጥጥ ሆኖ ቆይቷል። የማሕበረሰቡም አኗኗር የቀንድ ከብት እርባታ ላይ የተመረኮዘ ነው። አቶ ካሌብ እንደሚሉት "እስካሁን ቆላማው አካባቢ ስንዴ ሳይመረት የቆየበት ምክንያት አንድ የትኩረት ችግር ነበረ። በቃ ያ አካባቢ ሞቃት ነው። ጥጥ እና የቅባት እህሎች ብቻ ይመረቱበት ተብሎ የተተወ ነበረ።" አቶ ካሌብ "በኢትዮጵያ ስንዴ በመስኖ ያውም በቆላማ አካባቢ የተለመደ አይደለም። ቆላማው አካባቢ ያለ ባለሐብቶች እና አርብቶ አደሮች ስንዴን በዚህ አይነት ሁኔታ በዚህ የአየር ጠባይ አምርተው አያውቁም" ብለዋል።

ባለሙያዎች እንደሚሉት ከዓለም ከ70 በመቶ በላይ የሚሆነው ስንዴ በቆላማ አካባቢዎች የሚመረት ቢሆንም በኢትዮጵያ ግን የለየለት ደገኛ ነው። "ስለዚህ ገና እነሱን ልታለማምድ ነው። ስንዴ እንዴት በመስኖ እንደሚመረት ታሳያለህ። ፍላጎት ትፈጥራለህ። አቅማቸውን እና እውቀታቸን ትገነባለህ። ከዚያ በኋላ ቀስ እያሉ እያዩት፤ እያመኑት እየተቀበሉት ራሳቸው ግብዓቶችን አሟልተው በስፋት ስንዴ እያመረቱ ለገበያ ያቀርባሉ። ያንን እየሰራን ከሥር ከሥር ፍላጎቱ ያላቸው፤ አቅማቸው የተገነባ ባለሐብቶች፣ አርብቶ አደሮች እና አርሶ አደሮች በወሰዱት ሥልጠናና እና ባገኙት ክህሎት ተንተርሰው ስንዴውን ማምረት ጀምረዋል።" ሲሉ አቶ ካሌብ አሁን ሥራው የሚገኝበትን ደረጃ አብራርተዋል።

ይኸን ዕቅድ የማሳካቱ ነገር አልጋ ባልጋ አይደለም። እርሻ አይደል- ያውም ኢትዮጵያ ለሺህ አመታት ብላው ብላው ፈቅ ያላለ የኑሮ ዘይቤ። አቶ ካሌብ እንደከዚህ ቀደሙ በሰው ኃይል አርሶ፤ በሰው እጅ ዘርቶ በሰው ጉልበት አጭዶ በሰው ጉልበት ምርት ሰብስቦ ከታሰበው መድረስ እንደማይሆን እርግጠኛ ናቸው። 

"በመንግሥት በዚህ ሁለት እና ሶስት አመት ውስጥ ኢትዮጵያ ማምረት ያለባትን ከ17 ስከ 20 ሚሊዮን ኩንታል የሚሆነውን ስንዴ በእነዚህ አካባቢዎች ተመርቶ የአገሪቱን ፍላጎት ለማሟላት ታቅዶ እየተሰራ ነው።" የሚሉት ባለሙያው የታቀደውን ለማሳካት ግን በርካታ ሥራዎች መኖራቸውን አይሸሽጉም።

"የመስኖ መሠረተ-ልማቶች በሚገባ መሟላት አለባቸው። ከዚህ በተጨማሪ የጨዋማነት ችግር አለ። መስኖ በተጠቀምክ ቁጥር ዘመናዊ መስኖን ካልተጠቀምክ የጨዋማነት ችግር እየተፈጠረ መሬቱ የሚበላሽበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል። ሌላው ደግሞ በአርብቶ አደሩ አካባቢ የሰው ኃይልም እጥረት አለ። በአብዛኛው ባለሀብቱ አረም የማረም፣ ምርት የመሰብሰብ ሥራዎች በጉልበት ነው የሚከናወነው። ይኸ ሙሉ በሙሉ በማሽን መሠራት አለበት። ዘር መዝራት፣ ምርት መሰብሰብ፣ አረም እና ተባይ መከታተል እና መቆጣጠርን የመሳሰሉ ሥራዎችን ሜካናይዝድ ካላደረክ የምትፈልገውን ምርት ለማግኘት አስቸጋሪ ይሆናል" ብለዋል አቶ ካሌብ።

ባለፉት አመታት ኢትዮጵያን ጨምሮ በምሥራቅ አፍሪካ አገሮች የበረታው የበረሐ አንበጣ መንጋ እና የኬሚካል ግብዓቶች እጥረት ሥራውን "በሚፈለገው ፍጥነት" እንዳይሔድ እንቅፋት ሊፈጥሩ እንደሚችሉ አቶ ካሌብ ሥጋት አላቸው። ይሁንና "በእርግጠኝነት በደንብ ጠንክሮ ከተያዘ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ የምንፈልገውን የስንዴ ምርት በእነዚያ አካባቢዎች አምርቶ ማሟላት እንደሚቻል እምነት አለን" ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ፈርጠም ብለው ተናግረዋል። 

እሸቴ በቀለ 

ሸዋዬ ለገሠ