1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቅጥር ተግዳሮት በአፍሪቃ

ቅዳሜ፣ መስከረም 29 2014

የሥራ አጥነት ቁጥር አፍሪቃ ውስጥ ጨምሯል። በተለይ ወጣቶች ሥራ ማግኘት ይቸገራሉ። ሆኖም ግን ኢ-መደበኛ ዘርፎች እያበቡ ነው። አስተሳሰብን መቀየር ወሳን ነው ይላል አንድ የቅርብ ጊዜ ጥናት።

https://p.dw.com/p/41S7q
Südafrika Kapstadt Menschen 2018 Township LANGA Schönheitssalon im Township Kapstadt Township
ምስል imago/W. Schmitt

ሥራ አጥነቱ ተባብሷል

የሥራ አጥነት ቁጥር አፍሪቃ ውስጥ ጨምሯል። በተለይ ወጣቶች ሥራ ማግኘት ይቸገራሉ። ሆኖም ግን ኢ-መደበኛ ዘርፎች እያበቡ ነው። አስተሳሰብን መቀየር ወሳን ነው ይላል አንድ የቅርብ ጊዜ ጥናት።  ናምህላህ ምቺምቢ 25 ዓመቷ ነው። ደቡብ አፍሪቃ ካፕሽታድት ውስጥ ነው ነዋሪነቷ። ሥራ አጥ ናት።

«በጣም ተስፋ አስቆራጭ ነው። ምክንያቱም ለራሴ ሆነ ለልጄ የምፈልጋቸውን በርካታ ነገሮች ማሟላት አልቻልሁም። ስለዚህ በጣም ተስፋ አስቆራጭ እና የተበላሸ ነው በአጠቃላይ። ሰዎች በሥራ ቦታዎቻቸው የራሳቸውን የአክስትና አጎት ልጆች እና እህቶቻቸውን ነው የሚያመጡት። እና ለአንተ ማንም ለማያውቅህ ሥ ማግኘት በጣም ከባድ ነው።»

ሥነ-ልቦና ያጠናችው ወጣቷ ናምህላህ ከፍተኛ ተቋም ውስጥ ለተማረችበት መክፈል የሚገባትን ማጠናቀቅ ተስኗት በአንድ ወቅት ሥራ አጥ ሆና እንደነበረም ለዶይቸ ቬለ ተናግራለች።  እናም ታዲያ የችግሩ ገፈት ቀማሽ ናምህላህ ብቻ አይደለችም። በርካታ አብረዋት የተማሩ ጓደኞቿም ተመሳሳይ ችግር እንደገጠማቸው ተናግራለች።

Südafrika Kapstadt Menschen 2018 Township LANGA Kindertreffpunkt Kapstadt Township Langa *** S
ምስል imago/W. Schmitt

ከሠሐራ በታች ባሉ የአፍሪቃ ሃገራት ውስጥ የሥራ አጡ ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መሆኑን አንድ በጀርመን የፍሬድሪሽ ኤበርት ተቋም የተደረገ ጥናት ይጠቁማል። የምጣኔ ሐብት ሳይንቲስቱ እና የአፍሪቃ ጉዳይ ባለሞያው ሮቤርት ካፔል የሥራ አጥ ቁጥሩ የሚጨምርበትን መጠን እንዲህ ይተነትናሉ።

«አፍሪቃ ውስጥ የሥራ ገበያው ማነቆ እየገባበት ነው። ምጣኔው አንድ ከመቶ እያደገ የሥራ ገበያው መቅጠር የሚችለው ግን ከግማሽ በመቶ ያነሰ ነው። ይኼ እጅግ በጣም ጠባብ ነው። ሌላው ቀርቶ ምጣኔው ለቀጣይ ዐሥር ዓመታት ከአምስት እስከ ስምንት በመቶ ቢያድግ እንኳን የሥራ ገበያውን እጥረት ማሸነፍ አይቻልም።»

Infografik Afrika Beschäftigungskrise DE

ያም በመሆኑ አፍሪቃ ውስጥ የሥራ አጡ ቁጥር ይበልጥ መጨመሩ እንደማይቀር ባለሞያው ተናግረዋል። በተለይ ወጣት ሴቶች ላይ ሥራ አጥነቱ ጎልቶ እንደሚታይም አክለዋል። ለአብነት ያህል ኢትዮጵያ ውስጥ የወጣት ሥራ አጥነት ቁጥር ከ25 ከመቶ በላይ መሆኑን  የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ለዶይቸ  ቬለ ገልጧል። ወጣት ዲያና ተክለአብ በዚሁ ኮሚሽን በኩል አነስተኛ ብድር አግኝታ ወደ ሥራ ገበያው መቀላቀሏን ለዶይቸ ቬለ ገልጣለች። ዲያና ያጠናችው ሥነ ሕንጻ  ሲሆን ጎን ለጎን ግን የቤት ውስጥ ማስዋብ ሞያን በግሏ አዳብራለች። ከምረቃ በኋላ ሥራ ለማግኘት ፍለጋው እጅግ አታካች እንደነበረም ተናግራለች።

«ከዩኒቨርኢቲ ከተመረቁ በኋላ ሥራ ለማግኘት እጅግ አዳጋች ነው። በርካታ ሰዎች ሥራውን ቀድመው ተቀጥረው ስለሚይዙት የሚሻለው የራስን ሥራ መፍጠር ነው። የሥራ ፈጣሪ ሆኖ ራስን መቅጠር ነው የሚያዋጣው። ራስን ረድቶ የቤተሰብን ሕይወት መቀየር።»

እናም ወጣቶች ሥራ አጣን ብለው ከመቀመጥ ይልቅም የሥራ ገበያው ጠባብ በሆነባቸው ቦታዎች የራሳቸውን ሥራ ለመፍጠር እንዲታትሩ ባለሞያዎች ያበረታታሉ

ማርቲና ሽቪኮቭስኪ/ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ