1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቀጠለው የትግራይ ኃይሎችና የኢትዮጵያ መንግስት ውዝግብ

ሐሙስ፣ ነሐሴ 12 2014

ኢትዮጵያ ፌዴራላዊ መንግስት በሰሜን የአገሪቱ ክፍል ለሁለት ዓመታት እየተጠጋ ላሉ ጊዜያት ከሚፋለሙት የትግራይ ኃይሎች ጋር በመደራደር የሰላም እልባት ለመፈለግ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን በተደጋጋሚ ይገልጻል።

https://p.dw.com/p/4FkQk
Karte Äthiopien Region Tigray DE

ተንታኞች የሚያቃርን ሁኔታዎች መስተዋላቸውን ቀጥለዋል ይላሉ

ኢትዮጵያ ፌዴራላዊ መንግስት በሰሜን የአገሪቱ ክፍል ለሁለት ዓመታት እየተጠጋ ላሉ ጊዜያት ከሚፋለሙት የትግራይ ኃይሎች ጋር በመደራደር የሰላም እልባት ለመፈለግ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን በተደጋጋሚ ይገልጻል። ትግራይ ክልልን እያስተዳደረ የሚገኘው ህዝባዊ ወያኔ ኃርነት ትግራይ (ህወሓት) በበኩሉ ድርድሩ በአፋጣኝ እንዲፈጸም ተደጋጋሚ መግለጫዎችን ቢሰጥም ከፌዴራል መንግስት ጋር ለመደራደር ግን መተማመን ላይ የተደረሰ አይመስልም። ፖለቲካውን በቅርበት የሚከታተሉት አንድ ፖለቲከኛ ለዶይቼ ቬለ እንዳሉት ግን በሁለቱ ወገኖች መካከል ከሚያቀራርብ ይልቅ የሚያቃርን ሁኔታዎች አሁንም መስተዋላቸውን ቀጥለዋል ይላሉ። 

የኢትዮጵያ መንግስት በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የተከሰተውን ጦርነት በሰላማዊ መንገድ እልባት ለመስጠት ያቋቋመው የሰላም አማራጭ አብይ ኮሚቴ ትናንት ባወጣው መግለጫ ግጭቱ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ መንግስት ለሰላም እድል ለመስጠት ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሶ፤ የሰላም ንግግር ያለቅድመ ሁኔታ በየተኛውም ቦታ እና ጊዜ ለመጀመር ያለውን ዝግጁነቱን እንደ ከዚህ ቀደሙ አሳውቃለሁ ብሏል። 

ኮሚቴው የሰላም አማራጭን በዘላቂነት እውን ለማድረግ እና በሰሜኑ የትግራይ፣ የአፋር እና የአማራ ክልል አካባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎች በእለት ተእለት ኑሮዋችው እየገጠማቸው ያለውን ዘርፈ ብዙ እክል በመቅረፍ የመሰረታዊ አገልግሎቶችን ዳግም ስራ ለማስጀመር ባጠረ ጊዜ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ መድረስ እንደሚገባ ጠይቋል።
በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የሚመራው የሰላም ኮሚቴ ይህን መግለጫ ባወጣበት በሰዓታት ውስጥ ግን የትግራይ ኃይሎች ጥቃት ተፈጽሞብናል ሲሉ ትናንት ማምሻውን መግለጫ አውጥተዋል፡፡ ትግራይ ክልልን የሚመራው የህይወሃት ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳም መግለጫው አስመልክተው በሰጡት ምላሽ የፌዴራል መንግስት ዲፕሎማሲያዊ ጥቅም ለማግኘትና ጊዜ ለመግዛት ካልሆነ በስተቀር ለሰላማዊ ድርድር ዝግጁ አይደለም በማለት መግለጫውን አጣጥለውታል፡፡

የትግራይ ፖለቲካን በቅርበት የሚከታተሉት የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) ምክትል ሊቀመንበር አቶ መስፍን ደሳለኝ ለዶይቼ ቬለ እንደገለጹት፤ መሰል የሁለቱ ተደራዳሪ ቡድኖች እሰጣገባ ተስፋ የተጣለበት የፌዴራል መንግስት እና የትግራይ ኃይሎች ድርድርን እክል እየገጠመው ለመሆኑ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡ በፌዴራል መንግስት የተቋቋመው ባለ ሰባት አባላቱ የሰላም አማራጭ ኮሚቴ ወደ ተኩስ አቁም ስምምነት ሊያደርስ የሚችል እና ለቀጣይ የፖለቲካ ውይይቶች መሰረት የሚጥል የሰላም ምክረ ሃሳብ በተቻለ ፍጥነት ለአፍሪካ ህብረት ከፍተኛ ወኪል እንዲቀርብ መወሰኑን በትናንት መግለጫው አብራርቷል። በጉዳዩ ላይ ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ማብራሪያ መሰጠቱም እንዲሁ ተነግሯል፡፡ 
ኮሚቴው ወደተኩስ አቁም ስምምነት ሲገባ በሚፈጠረው አስቻይ ሁኔታ፣ መሰረታዊ አገልግሎቶችን በተቻለ ፍጥነት መልሶ ማቅረብ ይቻል ዘንድ፣ አስፈላጊ ቅደም ዝግጅቶች መደረጉን፤ ብሎም የአፍሪካ ህብረትም የሰላም ንግግሩ በአስቸኳይ ተጀምሮ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንዲደረስ የሰላም ንግግሩ የሚካሄድበትን ቦታ እና ጊዜ በፍጠነት ወሰኖ ንግግሩ እንዲጀመርም ያለውን ፍላጎቱን ይፋ አድርጓል፡፡

የትዴፓ አመራር ፖለቲከኛ መስፍን ደሳለኝ ግን በሁለቱም ወገኖች በኩል ይወረወራል ባሉት የጥላቻ ንግግሮች ምክኒያት በሰላማዊ ድርድሩ መደረግ ላይ ብዙ ተስፋ አይታያቸውም፡፡  ከሁለት ሳምንታት በፊት የፌዴራል መንግስት እና የትግራይ ኃይሎችን ለማደራደር የተለያዩ የምዕራባውያን ልዑካን ወደ መቀሌም ጭምር ተጉዘው በትግራይ የወደሙ መሰረታዊ ልማቶች እንዲጀመሩ የጋራ አቋም በመያዝ ከትግራይ ክልል መሪዎች የተጻፈውን የሰራተኞች የደህንነት ማስተማመኛ ደብዳቤ መላካቸውም አይዘነጋም፡፡ የፌዴራል መንግስት ግን የጋራ የተኩስ አቁም ስምምነት ሳይደረስ ይህ የማይታሰብ ነው ይላል፡፡ ፖለቲከኛ መስፍን የምእራባውያኑ ልዑካን ይዘው የመጡት የመፍትሄ ሃሳብ አስቀድሞም እንደማይሰራ ግምታቸው እንደነበርም አንስተዋል፡፡

የትግራይ ኃይሎች ትናንት ረቡዕ ነሐሴ 11 ቀን 2014 ዓ.ም. ባወጡት መግለጫ የፌደራል መንግሥቱ ጦር በምዕራብ ትግራይ በኩል በከባድ መሳሪያ የታገዘ ጥቃት ፈጽሟል የሚል ክስ ማሰማታቸውን ተከትሎ፤ ዛሬ ሐሙስ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ የሰጡት የጠቅላይ ሚንስቴር ጽ/ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ቢልለኔ ስዩም መረጃውን ሐሰት ሲሉ ውድቅ አድርገውታል፡፡

ሥዩም ጌቱ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ