1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቀድሞዉ የህወሓት ተዋጊዎች አቤቱታ

ዓርብ፣ ታኅሣሥ 12 2016

በመጀመርያ ዙር 55 ሺህ የቀድሞ ተዋጊዎች ከትግራይ ሐይሎች መሰናበታቸው የተገለፀ ሲሆን፥ እነዚህ የቀድሞ ተዋጊዎች ወደሰላማዊ ኑሮ ለመመለስ በሚደረግ ጥረት ተሃድሶ ኮምሽን ጨምሮ ሌሎች ተቋማት የገንዘብ፣ ስልጠና እና ሌሎች ድጋፎች እንደሚያደርጉላቸው ቃል ተገብቶላቸው ነበር።

https://p.dw.com/p/4aUve
ባለፈዉ ኃምሌ 55 ሺሕ የቀድሞ የትግራይ ተዋጊዎች ከሰራዊቱ ተቀንሰዋል
የቀድሞ የትግራይ ተዋጊዎች በስልጠና ላይምስል Million Haileselasie/DW

የቀድሞተዋጊዎች የተገባላቸዉ ቃል ገቢር አልሆነም

 

የኢትዮጵያ መንግስትና ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) በተፈራረሙት የሰላም ስምምነት መሠረት የቀድሞ ተዋጊዎችን መልሶ ለማቋቋም የገቡትን ቃል ገቢር ባለማድረጋቸዉ የቀድሞ የህወሓት ተዋጊዎች ለችግር መጋለጣቸዉን አስታወቁ።የከሰላም ስምምነቱ በኃላ የኢትዮጵያ መንግስት በመቶሺዎች የሚቆጠሩ የቀድሞ ተዋጊዎች ወደሰላማዊ ሕይወት እንዲመለሱ ድጋፍ እንደሚያደርግ ቃል ገብቶ ነበር። ይሁንና እስካሁን የተፈፀመ ነገር የለም ተብሏል።

በፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት መሰረት ትጥቅ የፈቱት የትግራይ ሐይሎች በሂደትም ሰራዊት መቀነስ መጀመራቸው ይታወቃል። ባለፈው ሐምሌ ወር እንደተገለፀው በመጀመርያ ዙር 55 ሺህ የቀድሞ ተዋጊዎች ከትግራይ ሐይሎች መሰናበታቸው የተገለፀ ሲሆን፥ እነዚህ የቀድሞ ተዋጊዎች ወደሰላማዊ ኑሮ ለመመለስ በሚደረግ ጥረት ተሃድሶ ኮምሽን ጨምሮ ሌሎች ተቋማት የገንዘብ፣ ስልጠና እና ሌሎች ድጋፎች እንደሚያደርጉላቸው ቃል ተገብቶላቸው እንደነበረ በትግራይ የሚገኙ የተሰናበቱ የቀድሞ ተዋጊዎች ይናገራሉ። የ30 ዓመቱ ወጣት ጎይትኦም ፀጋይ፥ የቀድሞ የትግራይ ሐይሎች ተዋጊ የነበረ ሲሆን በጦርነቱ ወቅት የአንድ ዓይኑ ብርሃን ያጣ ጭምር ነው። በመጀመርያ ዙር በሺዎች የሚቆጠሩ ተዋጊዎች ከትግራይ ሐይሎች ሲሰናበቱ ጎይትኦም አንዱ ነበር። ከሰራዊቱ ስንሰናበት የማቋቋሚያ ድጋፍ እንደሚደረግልን ቃል ተገብቶ የነበረ ቢሆንም እስካሁን ግን የተፈፀመ ነገር አለመኖሩ ይናገራል። ጎይትኦም "ከሰራዊት ስንሰናበት የተገባልን ቃል የስራ ዕድል እንደሚፈጠርልን፣ የማንም ጥገኛ እንደማንሆን፣ መንግስት እንደሚደግፈን ነው የተነገረን። ከተሰናበትን በኃላ ግን ምንም ነገር የለም። እኔን ጨምሮ ሁሉም የተቀነሰ የትግራይ ሰራዊት አባል የነበረ ከፍቶት ነው ያለው" ይላል።

የቀድሞዉ የትግራይ ተዋጊዎች በከፊል
የቀድሞ የትግራይ ተዋጊዎች በሐዘን ሥርዓት ላይምስል Million Haileselasie/DW

ሌላው በመቐለ ያነጋገርነው 'ተጋዳላይ' ዕቁባይ ተስፋይ የተባለ የቀድሞ የትግራይ ሐይሎች አባል፥ የሰላም ስምምነቱ ተፈርሞ ወደ መደበኛ ሕይወታችን እንደምንመለስ ሲነገረን ትልቅ ተስፋ ፈጥሮብኝ ነበር ሲል ይገልፃል። ይሁንና አሁን ከአካል ጉዳት ጋር በጎዳና ተጥሎ እንዳለ ይናገራል። ዕቁባይ "ስብራት እና የነርቭ ችግር አለብኝ። የአካል ጉዳተኛ ነኝ። ሐምሌ 17 ከሰራዊት ስንሰናበት ለሶስት ወር ቀለብ ተብሎ 6 ሺህ ብር ነበር የተሰጠን። ከጥቅምት በኃላ ደግሞ የDDR ገንዘብ ይሰጣቹሀል ተብሎ ነበረ። ካልሆነ የሰራዊት ራሽን ይሰጣቹሀል ነበር የተባልነው። ይሁንና አሁን DDR የለም፥ ራሽኑም የለም። እኔ ከአካል ጉዳቴ ጋር ጎዳና ተጥያለሁ። መንግስት ረስቶናል" ብሏል።

በሀገር ደረጃ፥ የቀድሞ ተዋጊዎች ወደሰላማዊ ሕይወት ለመመለስ የሚያስችሉ ተግባራት ለማከናወን የተቋቋመው ብሔራዊ የተሃድሶ ኮምሽን በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ዓመታት 300 ሺህ የቀድሞ ተዋጊዎች ስልጠናና ድጋፍ በመስጠት ወደመደበኛ ሕይወት ለመመለስ እንደሚሰራ ገልፃ የነበረው ባለፈው ዓመት አጋማሽ ነበር። ኮምሽኑ ከወራት በፊት ብሎት እንደነበረ ከሆነ፥ እስካለፈው ሕዳር ወር ድረስ 75 ሺህ የቀድሞ ተዋጊዎች ወደሰላማዊ ሕይወት ለመመለስ ዕድቅ አውጥቶ የነበረ ሲሆን ከነዚህ መካከል 50 ሺህ የሚሆኑት ከትግራይ መሆናቸው ማስታወቁ ይታወሳል። ከዚህ ሁሉ እቅድ መካከል ግን እስካሁን የተፈፀመ ነገር የለም። በዚህ ጉዳይ ዙርያ ከኮምሽኑ ኮምሽነር፣ ምክትል ኮምሽነር፣ የህዝብ ግንኙነት ክፍል ምላሽ እና ማብራርያ ለማግኘት ለቀናት ያደረግነው ጥረት፥ ሐላፊዎቹ ምላሽ መስጠት ባለመቻላቸው አልተሳካም።

የቀድሞ የትግራይ ተዋጊዎች በሰልፍ ላይ
የቀድሞ የትግራይ ተዋጊዎች በሰልፍ ላይምስል Million Haileselasie/DW

ቃል በተገባው መሰረት የማቋቋሚያ ድጋፍ የሚሹት በትግራይ ያሉ የቀድሞ ተዋጊዎች ግን፥ ችግሮች ወደተባባሰ ደረጃ ከመሻገራቸው በፊት ድጋፍ እንዲደረግላቸው ይጠይቃሉ። የቀድሞ የትግራይ ሐይሎች አባል ጎይትኦም ፀጋይ "ከሰራዊት ለተቀነሰው ትንሽም ቢሆን ማቋቋሚያ ካገኘ ሕይወቱም የሚያስተካክልበት፣ ሞራሉም የማይነካበት ነገር ቢመቻች መልካም ነው። ትንሽ ድጋፍ ካገኘን ሰርተን ሰላማዊ ሕይወት የምንመራ ነን። ምንም ካላገኘን ግን የአእምሮም ቀውስ ነው የሚፈጥረው" ሲል አክሏል።

የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር የቀድሞ ተዋጊዎች በማቋቋም ተግባር ላይ የፋይናንስ ችግር መፈጠሩ ሲገልፅ ቆይቷል። ባለፈው ሐምሌ ከሰራዊቱ ከተሰናበቱ ውጭ ከ200 ሺህ በላይ ሌሎች የቀድሞ ተዋጊዎች አሁንም በትግራይ የተለያዩ ቦታዎች መኖራቸው ግዚያዊ አስተዳደሩ ይገልፃል።

ሚሊዮን ኃይለስላሴ

ነጋሽ መሐመድ

እሸቴ በቀለ