1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቀይመስቀል የስልክ አገልግሎት ለትግራይ

ዓርብ፣ የካቲት 11 2014

በመቐለ እንደታዘብነው፥ በከተማዋ የሚገኙ አንዳንድ ዓለምአቀፍ ድርጅቶች እና የትግራይ ክልል መንግስት ከኢትዮ ቴሌኮም ውጭ የሆነ የቪሳት ኢንተርኔት አቅርቦት አላቸው። ከዚህ አገልግሎት ለማግኘት በሚል ተስፋ በርካታ ህዝብ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በራፍ ደጅ ሲጠና ይውላል።

https://p.dw.com/p/47EwB
Äthiopien Rotes Kreuz in Tigray
ምስል Million H.Silase/DW

የዓለም ቀይ መስቀል ከ100ሺ በላይ ሰዎች በስልክ አገናኝቷል

የዓለም ቀይ መስቀል ኮሚቴ ትግራይ ዉስጥ በተደረገዉ ጦርነት አንዳቸዉ ከሌላቸዉ የተለያዩ ቤተሰቦችን በስልክ ማገናኘቱን አስታወቀ።ካለፈዉ ሰኔ ማብቂያ ጀምሮ ትግራይ ዉስጥ የስልክ፣የኢንተርኔትና የፖስታ አገልግሎቶች እንደተቋረጡ ነዉ።የመገናኛ አገልግሎት ባለመኖሩ የሕዝቡ መደበኛ እንቅስቃሴ ክፉኛ ተቃዉሷል።በተለይ በጦርነቱ ሰበብ አንዳቸዉ ከሌላቸዉ የተለያዩ የቤተ-ሰብ አባላት፤ ዘመድና አዝማዶች መቸገራቸዉን እየገለፁ ነዉ።የዓለም ቀይ መስቀል ኮሚቴ ግን በቅርቡ 115 ሺሕ የተለያዩ ቤተ-ሰብ አባላትን በስልክ ማገናኘቱን አስታዉቋል።

 የትግራይ ሐይሎች መቐለ ከተቆጣጠሩበት ሰኔ 21 ቀን 2013 ዓመተምህረት በኃላ በትግራይ በተወሰነ ደረጃ የነበረው በመንግስታዊው ተቋም ኢትዮ ቴሌኮም የሚቀርብ ሁሉም የቴሌኮም አገልግሎት ሙሉ በሙሉ እንደተቋረጠ ይገኛል።
በትግራይ የመደበኛ እና ሞባይል ስልክ፣ ኢንተርኔት እና ሌላ የግንኙነት መስመር በመቋረጡ ህዝቡ ለማሕበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግር መጋለጡ ይገለፃል። በትግራይ ያሉ ዜጎች ከትግራይ ውጭ ካሉ ቤተሰቦቻቸውና ወዳጆቻቸው ለረዥም ግዜ ተለያይተው ያለ ሲሆን፥ ከዚህ በተጨማሪ በውጭ ሀገር የትምህርት ዕድል አግኝተው ሂደት ላይ የነበሩ፣ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ይሰሩ የነበሩ፣ ከኢንተርኔት ጋር በተገናኘ ስራ ይተዳደሩ የነበሩ እና ሌሎች ከስራ ውጭ ከሆኑ፣ ያገኙት የትምህርት እና ስራ ዕድል ከተደናቀፈ ወራት አልፈዋል።

Äthiopien Rotes Kreuz in Tigray
ምስል Million H.Silase/DW

በመቐለ እንደታዘብነው፥ በከተማዋ የሚገኙ አንዳንድ ዓለምአቀፍ ድርጅቶች እና የትግራይ ክልል መንግስት ከኢትዮ ቴሌኮም ውጭ የሆነ የቪሳት ኢንተርኔት አቅርቦት አላቸው። ከዚህ አገልግሎት ለማግኘት በሚል ተስፋ በርካታ ህዝብ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በራፍ ደጅ ሲጠና ይውላል። እጅግ በጣም የተወሰኑ የተሳካላቸው ከትግራይ ውጭ የሚኖሩ ቤተሰባቸው በዋትሳፕ፣ ቴሌግራይ አልያም ሌላ መተግበርያ አማካኝነት ያገኛሉ።

ከዚህ ውጭ አለምአቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ በመቐለ ጨምሮ በተለያዩ በትግራይ ባሉ ማእከላቱ የተጠፋፉ ቤተሰቦች በሳተላይት ስልክ አማካኝነት የማገናኘት አገልግሎት ይሰጣል። በዓለምአቀፉ ቀይመስቀል ኮሚቴ የትግራይ መስክ ልዑክ ቭላዲስላቭ ፖዶሊያኑክ ለዶቼቬለ እንደገለፁት ቀይመስቀል እስካሁን በትግራይ ለ115 ሺህ ሰዎች ነፃ ስልክ የማስደወል አገልግሎት ሰጥቷል። ቭላዲስላቭ ፖዶሊያኑክ እንደሚሉት የቀይመስቀል ነፃ የስልክ ማስደወል አገልግሎቱ ቤተሰቦቻቸው የት፣ ምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ ለማያውቁ ሰዎች መልካም አጋጣሚ የፈጠረ ነው ሲሉ ይገልፃሉ። ዓለምአቀፉ ቀይመስቀል ማሕበር ተመሳሳይ የተጠፋፉ ቤተሰቦች የማገናኘት ስራ በተለያየ መንገድ ላለፉት በርካታ ዓመታት በመላው ዓለም መከወኑ የቀይመስቀል ልዑኩ ተናግረዋል። 

Äthiopien Rotes Kreuz in Tigray
ምስል Million H.Silase/DW

የትግራይ ክልላዊ መንግስት የሞባይል ስልክ አገልግሎት በትግራይ ውስጥ ለማስጀመር ሞክሮ የነበረ ቢሆንም በቴክኒካዊ ችግሮች ምክንያት እንዳልተሳካ ከወራት በፊት ገልፆ ነበር። ከዚህ ውጭ ብዙ ተገልጋይ የሌለው የመደበኛ ስልክ አገልግሎት ግን ወደ ስራ ማስገባቱ የክልሉ መንግስት ይገልጻል።

ሚሊዮን ኃይለስላሴ

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሰ