1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፍራይታል ነዋሪዎች ስጋት  

ሐሙስ፣ ጳጉሜን 5 2012

ስለ ስደተኞች የተሳሳተ መረጃ የሚነዙ  ዜጎች የሚገኙባቸው የተለያዩ ስብስቦች ተመሰረቱ።በኢንተርኔት የስደተኞችን ስም የሚያጠፉ ዘረኛ መልዕክቶችን መለዋወጥና ማሠራጨት ያዙ።ዘመቻው እንደ ብራህቴል ባሉ ለስደተኞች ደጋፍ በሚሰጡትም ጭምር ላይ ነበር።ከስብስቦቹ አንዱ አንድ ደረጃ ወደፊት ተሻግሮ ራሱን የፍራይታል ቡድን በማለት ሽብር ለማካሄድ ተነሳ።

https://p.dw.com/p/3iAzL
Rechte Proteste gegen das Flüchtlingslager in Freital
ምስል picture-alliance/AP Photo/J. Meyer

የፍራይታል ነዋሪዎች ስጋት

ፍራይታል ምሥራቅ ጀርመን በሚገኘው የዛክሰን ፌደራዊ ክፍለሃገር ዋና ከተማ ድሬስደን አቅራቢያ የምትገኝ አነስተኛ ከተማ ናት። 40 ሺህ ነዋሪዎች ያሏትን ይህችን ከተማ ቫይስሪትዝ የተባለ ወንዝ ያቋርጣታል።ይህች ከተማ ከዛሬ አምስት ዓመት ወዲህ በፖለቲከኞችና በስደተኞች ላይ የፈንጂ አደጋ ጨምሮ የተለያዩ የሽብር ጥቃቶችን  ያደርስ በነበረ «የፍራይታል ቡድን» በተባለ የቀኝ ጽንፈኞች ቡድን ትታወቃለች።የቀኝ ጽንፈኞች ዋና ምሽጋቸው በሆነው በዛክሰን ፌደራዊ ክፍለ ሃገር ፣ከአንድ ሚሊዮን በላይ ተገን ጠያቂዎች ጀርመን እንዲገቡ ያስቻለው የጀርመን መራሄ መንግሥት አንጌላ ሜርክል የስደተኞች ፖሊሲ ጠንካራ ተቃውሞ ይቀርብበታል።በወቅቱ ሜርክል ለስደተኞች ከለላ መስጠታቸው ከሃገር ውስጥም ከውጭም ሰፊ የፖለቲካ ድጋፍ ቢያስገኝላቸውም በአንጻሩ ግን  አጋጣሚው ቀኝ ጽንፈኞች ደጋፊዎቻቸውን ይበልጥ ጽንፈኛ ለማድረግ ተጠቅመውበታል።    
መቀመጫው በሆነችው በፍራይታል የተሰየመው ቡድን ስደተኞች ወደ ጀርመን በብዛት በገቡበት በጎርጎሮሳዊው በ2015 በከተማይቱ የፍርሃት ድባብ ማስፈን ዓላማው እንደነበር ክሳቸው በመታየት ላይ ያለው የቡድኑ አባላት ለድሬስደን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ትናንት ተናግረዋል።የቡድኑ አባላት በዓመቱ በአንድ የምክር ቤት አባል መኪና ላይ እንዲሁም በስደተኞች መጠለያ ላይ ጥቃት ፈጽመዋል። ሁለቱ የ27 ዓመትና የ53 ዓመት እድሜ ያላቸው ወንዶች የቡድኑ አባል በመሆናቸው የተከሰሱ ሲሆን የተቀሩት ሁለቱ የ31 ዓመት እድሜ ያላቸው ወንድና ሴት ደግሞ ቡድኑ ወንጀሎቹን ሲፈጽም እገዛ ማድረግን ጨምሮ በሌሎች ወንጀሎች ነው የተከሰሱት።ይኽው ፍርድ ቤት ከሁለት ዓመት በፊት በአሸባሪነትና በግድያ ሙከራ የተከሰሱ 8 የፍራይታል ቡድን አባላት ላይ ረዘም ያለ እሥራት ፈርዷል። የሦስት ወንድና የአንዲት ሴት ተጠርጣሪዎች የክስ ሂደት በሚቀጥለው ዓመት ከፍጻሜ ይደርሳል ተብሎ ይገመታል።
የቡድኑ አባላት በከተማይቱ የፈጸሙት የሽብር ጥቃት ነዋሪዎችዋን እስካሁን ለስጋት እንደዳረገ ነው።ከመካከላቸው አንዷ ሽቴፊ ብራህቴል ናቸው። ብራህቴል የዛሬ አምስት ዓመት ከሌሎች ጋር ወደ ከተማይቱ የመጡ ስደተኞችን ለመርዳት ከመሰሎቻቸው ጋር በህብረት መስራት ከጀመሩ በኋላ ሕይወታቸው ተመሰቃቀለ።ስደተኞቹን መጥላት የተጀመረው ገና ከተማዋ ከመግባታቸው በፊት አንስቶ ነበር።ስደተኞች በከተማይቱ በሚገኝ የቀድሞ ሆቴል እንደሚያርፉ ከተሰማ በኋላ በመቶዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎች  በተደጋጋሚ ሰልፍ ይወጡ ነበር።  በወቅቱ ከአስከፊው የሶሪያ ጦርነት ሰለባ የሆኑ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ወንዶች ሴቶች እና ህጻናት ሕይወታቸውን ለማትረፍ በእግርና በጀልባ  ወደ አውሮጳ  መጉረፍ ጀመሩ።በመካከሉም በርካቶች በጉዞ ላይ እየሰጠሙ የባህር ሲሳይ ሆኑ።በግሪክ የባህር ዳርቻዎች ከወላጆቹ ተነጥሎ በውሐ የተበላ ህጻን አስከሬን በመገናኛ ብዙሀን በተሠራጨበት በዚህ ወቅት ላይ ነበር ፍራይታልን በመሳሰሉ ከተሞች ዜጎች የተነፈጉትን ገንዘብ መንግሥት ለስደተኞች እየሰጠ ነው የሚሉ የተቆጡ ቀኝ ጽንፈኞች በአደባባይ ጩኽታቸውን ያሰሙት። ቁጣው በተቃውሞ ብቻ አላበቃም ከተማዋን እንጠብቃለን የሚሉና ስለ ስደተኞች የተሳሳተ መረጃ የሚነዙ  ዜጎች የሚገኙባቸው የተለያዩ ስብስቦች ተመሰረቱ።በኢንተርኔት የስደተኞችን ስም የሚያጠፉ ዘረኛ መልዕክቶችን መለዋወጥና ማሠራጨት ያዙ።ዘመቻው እንደ ብራህቴል ባሉ ለስደተኞች ደጋፍ በሚሰጡትም ጭምር ላይ ነበር።ከስብስቦቹ አንዱ አንድ ደረጃ ወደፊት ተሻግሮ ራሱን የፍራይታል ቡድን በማለት በከተማይቱ ሽብር ለማካሄድ ተነሳ።ብራህቴል 
«በኢንተርኔት ዘለፋዎችን በማሰራጨት ተጀመረ። ከዚያም ጥቃት እንደተፈጸመብኝ ተሰማኝ።በነሐሴ 2015 የፖስታ ሳጥኔ በፈንጂ ተበታተነ፤ድርጊቱ የተፈጸመው በፍራይታል ቡድን መሆኑ ተረጋግጧል።ልጄ በመጀመሪያ የፍርድ ሂደት ውስጥ ክስ ከተመሰረተባቸው ሰዎች በአንዱ ጥቃት ተፈጸመበት።»
ፍራይታል ለተወለዱትና ላደጉት ለብራህቴል ይህ አስከፊ ነበር።8 የፍራይታል ቡድን አባላትና ደጋፊዎች አሸባሪ ቡድን በመመስረትና የስደተኞች መጠለያዎችን የተቃዋሚዎቻቸውን የመኖሪያ ህንጻዎች፣ ቢሮዎችንና መኪናዎችን በፈንጂ ጥቃት ዒላማ በማድረጋቸው ለረዥም ጊዜ እስር ተዳርገዋል።የጥቃት ፈጻሚዎቹ ዓላማ የፍርሃት እና የጭቆና ድባብ ማስፈን ነበር። አዎ በዚህ የተነሳ የብራህቴል ጭንቀት አሁንም አላበቃም።የታሰሩት 8 አሸባሪዎች ደጋፊዎች እንዳሏቸው የሚያውቁት  ብራህቴል ጀምበር ከተዘቀዘቀች ከቤታቸው መውጣት አቁመዋል።።
«ያኔ አቅም የሌለህ ደካማ እንደሆንክ ነው የሚሰማህ። እስከዚያን ጊዜ ድረስ ሕይወቴ በራስ መተማመን የተሞላ ነበር።ከዚያ በኃላ ግን ዛቻው ወደኔ እየቀረበ  መጣ።በኢንተርኔት የቤተሰቦችህን መረጃ የያዘ ዘለፋ ይበተናል።ፍርሃት ያድርብሃል፤ በእንቅስቃሴህ ሁሉ ከመጠን ያለፈ ስጋት እንዲያድርብህ  ሁሌም ቀጥሎ ምን ይመጣ ይሆን የሚል ስሜት እንዲኖርህ ያደርጋል።ስለ ወላጆችህ ስለ ጓደኞችህ እና ቤተሰቦችህ ትጨነቃለህ።» 
ትናንት በነዚህ ድርጊቶች ክስ የተመሰረተባቸው የአራት ተጨማሪ የፍራይታል ቡድን አባላት ሁለተኛው ችሎት ተካሂዷል።ከመካከላቸው አንዱ ከዚህ ቀደም የከተማዋ ምክር ቤት አባል እንደነበረ ተዘግቧል።ሚካኤል ሪሽተር  በጎርጎሮሳዊው 2015 የፍራይታል ከተማ ምክር ቤት አባል ነበሩ። ያኔ የግራዎቹን ፓርቲ ወክለው በምክር ቤቱ መቀመጫ የነበራቸው ሪሽተር ከብራህቴል ጋር ስደተኞችን ይረዱ ነበር።በዚህ በጎ አድራጎታቸው የጽንፈኛው «የፍራይታል ቡድን ሰለባ ሆኑ።ቀኝ ጽንፈኞቹ መኪናቸውን አቃጠሉባቸው።ርሳቸውንም ከመኪናቸው ጋር ለማቃጠል ሞክረው ነበር።
«የፍርድ ቤቱን ሰነዶች ማንበብ ችያለሁ።ሰዎቹ ስለ እንቅስቃሴ ሁሉንም ያውቁ ነበር።በመኪናዬ ላይ የቦምብ ጥቃት ካደረሱ በኋላ አዲሱን መኪናዬንም ከኔ ጋር ሊያደነዷት ሞክረው ነበር።ሁሉንም ያውቁ ነበር።»
ሪሽተር ከሁለት ዓመት በኋላ ፍራይታልን ለቀው ሄዱ። 
«በጎርጎሮሳዊው 2017 ፍራይታልን ለመልቀቅ ወሰንኩ።እዚህ ውሳኔ ላይ የደረስኩት ሰነዶቹን  ካነበብኩ በኋላ ነው።ፍጹም የሚመች አልነበረም።እጅግ አደገኛ ነበር።ከጥቃት ፈጻሚዎቹ አንዱ እኔ ከነበርኩበት ህንጻ ጎረቤት ካለ መኖሪያ ህንጻ ውስጥ ነው የሚኖረው።መኪናዬ መጀመሪያ የቦምብ ጥቃት ከደረሰበት በኋላ የያዝኳትን አዲስ መኪና ወዲያውኑ ፎቶ አንስቶ ለፍራይታል ቡድን የላከላቸው እርሱ ነበር።»  
ሪሽተር በጥቃቱ ሰበብ ለ9 ወራት የሀኪም ፈቃድ ላይ ከቆዩ በኋላ ወደ ደቡብ ጀርመንዋ ባቫርያ ግዛት ሄዱ።እዚያም ፖለቲካውን ትተው በእርሻ ሥራ የተሰማሩት ሪሽተር አሁን ነጻነት ይሰማኛል የፈለግኩትንም መናገር ችላለሁ ብለዋል።ብራህቴል ግን አሁንም ይሰጋሉ ።
«የተፈጸመው የቀኝ ጽንፈኞች አሸባሪነት ነው።እንደዚህ ተብሎ መጠራት አለበት። የፖስታ ሳጥኔ የፈነዳው  በሪችት ሳይሆን በፈንጂ ነው።እንደሚመስለኝ ይህ እንደገና ሊደርስ ይችላል።አሁን ክስ የተመሰረተባቸው ከፊት ያሉት ብቻ ናቸው።በዚህች ከተማ በርካታ የዚህ ድርጊት ደጋፊዎች ወይም አጨብጫቢዎች ናቸው።አዎ አደጋው አሁንም አለ።» 
ጥቃቱ ከተፈጸመ ከአምስት ዓመት በኋላ ቀኝ ጽንፈኛውና ፀረ ስደተኞች አቋም ያለው «አማራጭ ለጀርመን በጀርመንኛው ምህጻር AFD የተባለው ፓርቲ በከተማዋ ምክር ቤት ውስጥ አሁን ጠንካራ ይዞታ ያለው ፓርቲ ሆኗል።በምክር ቤቱ የAFD ተወካይ ሬኔ ዛይፍሪድ በፍራይታል ቡድን የኢንተርኔት የሃሳብ መለዋወጫ መድረክ ለስደተኞች በተዘጋጀው ቤት ውጭ ተቃውሞ እንዲካሄድ ግፊት ሲያደርጉ ነበር።«ሁሉንም አድናቸዋል »ሲሉም ጽፈዋል።የቀድሞ ሠራተኛቸው ደግሞ ክስ ከተመሰረተባቸው መካከል አንዱ ነው ተብሏል።የከተማዋ  ከንቲባና ሌሎች የከተማዋ ባለሥልጣናት በፍራይታል የሚካሄደውን አመጽ በማለዘብ ከተማዋን ከአሉታዊ ዘገባዎች ለመታደግ  ችለዋል።ዶቼቬለ አስተያየቱን የጠየቀው የከተማው ከንቲባ ጽህፈት ቤት በጽሁፍ በሰጠው መልስ  አብዛኛዎቹ ነዋሪዎች ሰላም ወዳድ መሆናቸውንና በፍራይታልም ለጽንፈኞች ቦታ እንደሌለ ተናግረዋል።

Deutschland Mutmaßlicher Anschlag auf Auto von Politiker Michael Richter aus dem Freitaler Stadtrat
ምስል picture-alliance/dpa/A. Burgi
Dresden - Urteile im Prozess gegen «Gruppe Freital»
ምስል picture-alliance/dpa/S. Kahnert
Deutschland Die Flüchtlingshelferin Steffi Brachtel in Freital
ምስል picture-alliance/dpa/S. Kahnert
Rechte Proteste gegen das Flüchtlingslager in Freital
ምስል picture-alliance/AP Photo/J. Meyer

ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ