1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ» አስፈላጊነትና አተገባበሩ

ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 26 2015

ፍትሕ ሚኒስቴር በቅርቡ ይወጣል ባለው የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ካስቀመጣቸው የማስፈፀሚያ ስልቶች ቀዳሚው ክስ ነው። የወንጀል ምርመራውን፣ክስ የመመስረቱን እና የፍርድ ሂደትን ማን ያከናውነው የሚለው ለውይይት ቀርቧል። ሌላኛው የፖሊሲው ማስፈፀሚያ ስልት እውነትን ማፈላለግ፣ እና ይፋ ማድረግ ሲሆን እርቅ ፣ ምህረት፣ የገንዘብ ወይም ሌላ ካሳን ያካትታል።

https://p.dw.com/p/4Lj9a
Symbolbild | Justiz
ምስል fikmik/YAY Images/IMAGO

"የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ"

ፍትሕ ሚኒስቴርበኢትዮጵያ ውስጥ የሽግግር ፍትሕ በምን ሁኔታ ሊመራ እና ሊተገበር ይገባል የሚለውን ጥያቄ ይመልሳል በሚል ያዘጋጀውን የጥናት ሰነድ ሕዝብ እንዲወያይና ሀሳብ እንዲሰጥበት ይፋ አደረገ። ፍትሕ ሚኒስቴር ለውይይት ክፍት ያደረገው ሰነድ በኢትዮጵያ ሊዘጋጅ ለታሰበው "የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ" የባለሙያዎችን እና የሕዝብን ሀሳብ ለማካተት የታለመለት ነው ተብሏል። ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት በሽግግር ሁኔታ ውስጥ ብታልፍም የሽግግር ፍትሕ በተሟላ ደረጃ ተግባራዊ ሆኖ አያውቅም ሲል ያስታወቀው ፍትሕ ሚኒስቴር "ከዚህ በፊት የተተገበሩት የሽግግር ፍትሕ ስልቶች በእርቅ እና ሀገራዊ መግባባት ላይ ያተኮሩ ባለመሆናቸው ውጤታማ አልነበሩም" በማለት አሁን ጉዳዩ አስፈላጊ የሆነበትን ምክንያት ገልጿል። 
ፍትሕ ሚኒስቴር የሽግግር ፍትሕ የፖሊሲ አቅጣጫ አማራጮች በሚል ርእስ ባወጣው ባለ 37 ገጽ በጥናት የተዘጋጀ የተባለ ሰነድ ላይ " ከእርስ በርስ ጦርነት ፣ ግጭት እና ጭቆና በመውጣት - በፖለቲካ እና በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ውጤታማ ሽግግር ለማድረግ በሞከሩ ሀገራት የሽግግር ፍትሕ ሂደቶች ተግባራዊ ተደርገዋል" ይላል።የሽግግር ፍትሕ ሥርዓት መዘርጋት ዘላቂ ሰላም ፣ እርቅ እና ፍትሕ በማስገኘት ረገድ ውጤታማ መሆኑንም ይሄው ሰነድ ይገልፃል። የሽግግር ፍትሕ በግጭት፣ በጦርነት ወይም ሌላ ምክንያት ለተፈፀመ ጥቃት ፣ መጠነ ሰፊ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች እና በደሎች የተሟላ መፍትሔ መስጠት መሆኑን የገለፀው ሚኒስቴሩ ውጤቱ ዘላቂ ሰላም ፣ እርቅ፣ መረጋጋት እና የሕግ የበላይነት የሰፈነበት ሥርዓት መፍጠር መሆኑንም አብራርቷል።
በሌሎች ሀገራት ክስ እና ቅጣት ዋነኛ የሽግግር ፍትሕ ማስተግበሪያ ስልቶች ሆነው መታየታቸውንም ፍትሕ ሚኒስቴር ያወጣው ሰነድ ያሳያል። ኢትዮጵያ ልታዘጋጀው በሂደት ላይ ያለው ይህንን የተመለከተው ፖሊሲ ከክስ እና ቅጣት ባለፈ "እውነት እየተጣራ ይፋ የሚሆንበት ፣ እርቅ የሚሰፍንበት፣ የማካካሻ እርምጃ እና የተቋማት ለውጥ የሚካሄድበት ይሆናል" ተብሏል። በጉዳዩ ዙሪያ ተጨማሪ ማብራሪያ ከፍትሕ ሚኒስቴር ለማግኘት ጥረት ባደርግም ለጊዜው አልተሳካም።
ኢትዮጵያዊ ተነሳሽነት ለሰብዓዊ መብቶች የተባለ ሀገር በቀል ድርጅት ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ዮሃንስ ሰለሞን "የሽግግር ፍትሕ እጅግ አስፈላጊ ነው" ይላሉ።ፍትሕ ሚኒስቴር የሽግግር ፍትሕ በአራት ዋና ዋና ምክንያቶች አስፈላጊ መሆኑን አስታውቋል። ኢትዮጵያ የምትገኝበት ሀገራዊ አውድ ያንን መተግበር በማስገደዱ ማለትም የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ፣ አለመረጋጋት፣ ግጭትና የእርስ በርስ ጦርነት በመቀጠሉ ዜጎች ለሞት፣ ለመፈናቀል አደጋ እየተጋለጡ በመሆኑና ለነዚህ ችግሮች ከዚህ በፊት የተሰጡ ምላሾች ሙሉ አለመሆባቸው የአጥፊዎችና የተጎጅዎችን ቁጥር ማብዛቱ ፣ የበደሎች መደራረብ እና የጥፋቶች ማህበረሰባዊ ቅርጽ መያዝ በመደበኛው የፍትሕ ሥርዓት እና አካሄድ ፍትሕ መስጠትንም ሆነ ይቅርታ እና እርቅን ማከናወን አላስችል በማለቱ አንድ ፣ የተሳካ የሽግግር ፍትሕ ለሀገረ - መንግሥት ግንባታ ወሳኝ በመሆኑ ማለትም ባለፉ በደሎች ይቅር ለመባባልና እርቅ ለማውረድ ብሎም የተከፋፈለ ያለውን ሕዝብ ለማቀራረብ ግንኙነትን ለመጠገን ፣ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ እና እርቅን ለመስጠት ለዚህም የሰውን ክብር ለመምለስ፣ ላለፈ ቁስል እውቅና ለመስጠት እንዲሁም ለጋራ ዳግም ውህደት ሁለት፣
የተሳካ የሽግግር ፍትሕ ሂደት ሳይተገበር የዴሞክራሲ ሽግግርም ሆነ ዘላቂ ሰላም ማስፈን ስለማይቻል ሦስት እንዲሁም ሰብዓዊ መብቶችን ለማስከበር እና የሕግ የበላይነትን ለማስፈን የሚሉት ናቸው። የሕገ መንግሥት ጉዳዮች የሕግ ባለሙያ አቶ አሮን ደጎል በበኩላቸው "ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለማስፈን የሚውል" ስልት ነው ብለዋል።በጉዳዩ ላይ አስተያየት የሰጡት አቶ ዮሃንስ የሽግግር ፍትሕ ሲታሰብ "ገለልተኛ ወገን" ሊሳተፍበት የተገባ ነው ብለዋል። አቶ አሮን የሽግግር ፍትሕ ከተሳካላቸው ሀገሮች ደቡብ አፍሪካ አንዱ መሆኑን በመጥቀስ "ኢትዮጵያ ውስጥ ይህንን ለማድረግ በቅድሚያ ብሔራዊ መግባባት ያስፈልጋል" ብለዋል።
ፍትሕ ሚኒስቴር በቅርቡ ይወጣል ባለው የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ውስጥ የማስፈፀሚያ ስልቶችን ሲዘረዝር ቀዳሚው ክስ መሆኑ ሰፍራል። የወንጀል ምርመራውን ፣ ክስ የመመስረቱን እና የፍርድ ሂደትን ማን ያከናውነው የሚለው ለውይይት ቀርባል። ሌላኛው የፖሊሲው ማስፈፀሚያ ስልት እውነትን ማፈላለግ፣ እና ይፋ ማድረግ ሲሆን እርቅ ፣ ምህረት፣ ማካካሻ ማለትም ለደረሱ የመብት ጥሰቶች ወይም የሀብት ውድመቶች ውጤታማና ተመጣጣኝ የገንዘብ ወይም ሌላ ካሳ ፣ መጠገኛ ፣ ማደሻን ማገዝን ያካትታል። ተቋማዊ ለውጥ ማድረግ እና ይህ ሀገራዊ ጉዳይ መቼ ይጀመር የሚለው ውሳኔ የሚጠይቁ ጉዳዮች መሆናቸው በዝርዝር ቀርበዋል።

Symbolbild Justitia Rechtsstaat
የፍትሕ ምልክትምስል Damien Meyer/AFP/Getty Images

ሰሎሞን ሙጬ

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ