1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሽግግር ተግዳሮቶች ወይስ የአስተዳደር ድክመቶች?

ሰኞ፣ ጥቅምት 5 2011

በኢትዮጵያ በቅርብ ጊዜ እየታዩ ያሉ አብዛኞቹ ክስተቶች በሽግግር ላይ ባለ ስርዓት የሚከሰቱ እንደሆነ እና በጊዜ ሂደት እየተፈቱ እንደሚመጡ የሚከራከሩ አሉ። ከእነዚህ ሁነቶች የተወሰኑቱ በሽግግር ላይ ባሉ ሀገሮች የሚከሰቱ እንደሆኑ የሚገልጹ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራን በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መንግስት ድክመትም የመጡ አሉ ይላሉ።

https://p.dw.com/p/36alj
Äthiopien Kundgebung Premierminister Abiy Ahmed in Addis Ababa | Explosion
ምስል Oromo Media Network

የሽግግር ተግዳሮቶች ወይስ የአስተዳደር ድክመቶች?

ኢትዮጵያ ያልተጠበቁ፣ አስደማሚ፣ አሳዛኝ አንዳንዴም አስፈሪ ሁነቶችን በየሳምንቱ ማስተናገድ ከጀመረች መንፈቅ አለፈ። ይህን የኢትዮጵያን ሁኔታ የታዘቡቱ እየሆነ ያለውን ለመግለጽ ደጋግመው የሚጠቅሱት ታዋቂው የሩሲያ ፖለቲከኛ ቭላዲሚር ሌኒንን ጽፎታል የሚባለውን አባባል ነው። አባባሉ «ምንም የማይከሰትባቸው አስርት ዓመታት እንዳሉ ሁሉ የአስርት ዓመታት ሁነቶች የሚግተለተሉባቸው ሳምንታት ደግሞ አሉ» የሚል ነው። 

“የኢትዮጵያ ተከታታይ ሁነቶች በአስርት ዓመታት ከሚደረጉትም በላይ ናቸው” የሚሉቱ ወቅቱ ሀገሪቱ ከመበታተን ወጥታ ወደ እውነተኛ ዲሞክራሲ ለመሻገር የምትፍጨረጨርበት እንደሆነ አጽንዖት ይሰጣሉ። ሌሎች ደግሞ የለውጥ ጭላንጭል ቢኖርም ሀገሪቱ አሁንም በመስቀለኛ መንገድ ላይ እንዳለች መረሳት እንደሌለበት ያስገነዝባሉ።

Äthiopien Vereidigung Premierminister Abiy Ahmed
ምስል picture-alliance/AA/M. W. Hailu

በኢትዮጵያ ከኅዳር 2008 ዓ. ም. ጀምሮ የነበረውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን መምጣታቸው ለውጦች ማምጣቱን ብዙዎች ይስማሙበታል። ሆኖም እዚህም እዚያም የሚታዩ ግጭቶች፣ ብሔር ተኮር ጥቃቶች፣ መፈናቀሎች፣ ስርዓት አልበኝነቶች፣ የደቦ ፍርዶች፣ የሥራ ማቆም አድማዎች እና ሰላማዊ ሰልፎች የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ መንግሥት የአስተዳደር ጥንካሬ ላይ ጥያቄዎች እንዲነሱ ምክንያት ሆነዋል።

በኢትዮጵያ በቅርብ ጊዜ እየታዩ ያሉ አብዛኞቹ ክስተቶች በሽግግር ላይ ባለ ስርዓት የሚከሰቱ እንደሆነ እና በጊዜ ሂደት እየተፈቱ እንደሚመጡ የሚከራከሩ አሉ። በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካል ሳይንስና የዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር አቶ ዮናስ አሽኔ ለችግሮቹ ትንታኔ ከመስጠታቸው በፊት በኢትዮጵያ የመጣው ለውጥ «ሽግግር ነው ወይስ አይደለም» የሚለውን አስቀድመው መመልከት ይመርጣሉ። ጉዳዩን «በጣም አከራካሪ ነው» ሲሉ የሚገልጹት መምህሩ የኢትዮጵያ የአሁን የፖለቲካ ሁኔታ በተለያዩ ምልከታዎች እንዴት እንደሚገለጽ ጠቅለል ባለ መልኩ ያስረዳሉ።    

“በአጠቃላይ የተለያዩ ጽንሰ ሀሳቦችን በመጠቀም ለመግለጽ ይሞከራል። ግን አንድ የማክደው ትልቁ ሀሳብ ለምሳሌ ሽግሽግ፣ ሽግግር፣ ለውጥ ነው ወይ? የሚለውን ነገር ሊገልጽልን የሚችለው አፍጥጦ የወጣ ነገር ለውጥ አለ። ይሄ ለውጥ  እንዴት እንግለጸው የሚለው ወሳኝ ይመስለኛል። እና ደግሞ በታሪክ ሂደት ውስጥ ሆነን እያሰብን ስለሚሆን ምንድነው እየተካሄደ ያለው የሚለውን የሚይዝልን ቃል እና ጽንሰ ሀሳብ ማግኘት ሊከብደን ይችላል። ሰዎች የተለያየ ሀሳብ ይሰጣሉ። እና ሀሳቡንም በተለያየ መንገድ ይደግፋሉ አንዳንዴ በጣም ተቀባይነት ይኖረዋል።

ለምሳሌ ሽግሽግ የሚሉት ሰዎች እነ ዶ/ር መረራ [ጉዲናም] ጭምር በፖርቲው ውስጥ የተካሄደውን ለውጥ፣ የስልጣን መቀባበል ለመግለጽ ነው የተቀጠቀሙበት። ስለዚህ ሽግሽግ የሚለው ነገር በጣም ገላጭ ይመስላል። ግን ይሄ ሽግሽግ የተካሄደው ደግሞ እንደገና ያመጣው ሰፊ የሆነ፣ እየተካሄደ ያለ፣ እንደገና ወደፊት በደንብ ልናወራው የምንችለው ሽግግር ውስጥ ነን ብዬ አስባለሁ። ይሄም በፓርቲው ግፊት የመጣ ሳይሆን በህዝባዊ ፖለቲካ የመጣ [ነው]። ትልቅ ጥያቄ አለ። ያንን ለመጠየቅ ነው ፓርቲው ሽግግር ያደረገው። ስለዚህ ሰፊው ነገር ህዝቡ ራሱን ወደ ሽግግር ውስጥ ከትቷል” ይላሉ አቶ ዮናስ። 

የጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህሩ አቶ ሙሳ አደም በኢትዮጵያ የተካሄደው የፖለቲካ ለውጥ «ሽግግር» በሚለው ቃል ሊገለጽ ይችላል ይላሉ። «ከአንድ መንግሥት ወደ ሌላ መንግሥት፣ ከአንድ ፓርቲ ወደ ሌላ ፓርቲ አሊያም ከአንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ወደ ሌላ ጠቅላይ ሚኒስትር» የሚደረግ ለውጥ «ሽግግር» እንደሆነ ያስረዳሉ። የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው አቶ ዮናስ በበኩላቸው «ብዙ ሰዎችን ያገልል የነበረን የፖለቲካ መድረክ ብዙ ቡድኖች እንዲሳተፉበት ሲደረግ የዲሞክራሲ ሽግግር ዘመን ሊባል ይችላል» ይላሉ። በኢትዮጵያ ከታዩ ሁነቶች የተወሰኑቱ በሽግግር ላይ ባሉ ሀገሮች የሚከሰቱ እንደሆኑም ያብራራሉ።  

Äthiopien Ministerpräsident Abiy Ahmed wandte sich an einige Mitglieder der äthiopischen Streitkräfte
ምስል Fitsum Arega/Chief of Staff/Prime Minister's Office of Ethiopia

“በኢትዮጵያ  አሁን እየሆነ ያለው ታፍኖ፣ ተዘግቶ የነበረ በር ሲከፈት የሚመጣ የድርድር ፖለቲካ አሊያም የፖለቲካ እንቅስቃሴ የሚያመጣው ነው” ይላሉ አቶ ዩናስ። የጅግጅጋ ዩኒቨርስቲው አቶ ሙሳም በዚህ ይስማማሉ። የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲው መምህር በገዢው ፓርቲ የ27 ዓመታት የስልጣን ዘመን የተቋማት መዳከም ብሎም መፈራረስ አሁን በኢትዮጵያ ለታዩ ችግሮች መባባስ በተጨማሪ ምክንያትነት ይጠቅሳሉ። ኢህአዴግ የሚከተለው ስርዓት በማንነት እና ብሔር ፖለቲካ ላይ መንጠላጠሉ ሌላው የችግሮች መንስኤ እንደሆኑ ይገልጻሉ። በኢትዮጵያ የመጣው ለውጥ የተከተለው አካሄድ “ከውስጥ ወደ ውጭ” መሆኑን የሚያስምሩበት የጅግጅጋ ዩኒቨርስቲው አቶ ሙሳ አንዳንዶቹ ክስተቶች በፖለቲካ መዋቅር ውስጥ ባሉ ግለሰቦች አማካኝነት የሚመጡ እንደሆኑ ይተንትናሉ።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲው አቶ ዮናስ ደግሞ በኢትዮጵያ ባለፉት ወራት የተደጋገሙ እንደ ስራ ማቆም አድማ አይነት ክስተቶች እና በተለያዩ ጉዳዮች የሚታዩ የተጋጋሉ ክርክሮች የቀውስ ምልክቶች ተደርገው መወሰድ የለባቸውም ይላሉ። በኢትዮጵያ በሽግግር ወቅት የሚጠበቁ ምልክቶች ቢታዩም በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ መንግስት ድክመት የተከሰቱም እንዳሉ የጅግጅጋ ዩኒቨርስቲው መምህር ይናገራሉ። ለዚህም በገዢው ፓርቲ አጋር ድርጅቶች የሚመሩ ክልሎችን በምሳሌነት ያነሳሉ። 

ሁለቱም የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራን አሁን የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት በመንግስት በኩል በአፋጣኝ መሰራት ያለባቸው ጉዳዮች እንዳሉ ያምናሉ። አቶ ዮናስ አሁን በኢትዮጵያ ያለውን ለውጥ መሸከም የሚችሉ ተቋማት መመስረት በአጭር ጊዜ ሊከናወን ይገባል ይላሉ። ህዝባዊ ፖለቲካን ወደ ተቋማዊ ፖለቲካ መለወጥ እንደሚገባም ይመክራሉ። “ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለውጥ ፈልጎ ከስር ያለው ስርዓት ለውጥ የማይፈልግ ወደ ኋላ መጎተት አይቀሬ መሆኑን አቶ ሙሳ ይናገራሉ። ለዚህ መፍትሄው በፖለቲካ መዋቅሩ ውስጥ “የማጥራት ስራ” ማከናወን እና “አዳዲስ ፊቶችን” ወደፊት ማምጣት መሆኑን ያስገነዝባሉ።

የፖለቲካ ምሁራኑን ትንታኔ ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ። 

ተስፋለም ወልደየስ 

ሸዋዬ ለገሠ