1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ፖለቲካእስያ

የስድስት ዓመታቱ የየመን ጦርነት መቋጫ ያገኝ ይሆን?

ዓርብ፣ መጋቢት 17 2013

ላለፉት ስድስት ዓመታት በየመን በርካቶችን ለሞት ለረሀብና ለበሽታ የዳረገ አስከፊ ጦርነት ተካሂዷል። ከተፋላሚ ሀይሎቹ አንዷ የሆነችው ሳውዲ አረቢያ  የሰላም እቅድ አቅርባለች።ተንታኖች  ግን የሰላም ስምምነት ማለት ጦርነቱ ያበቃል ማለት አይደለም ይላሉ።

https://p.dw.com/p/3rEHU
Jemen Marib | Soldaten auf Truck
ምስል Ali Owidha/REUTERS

የመኑ የስድስት ዓመታት ጦርነት ትልቁ ምስል

ላለፉት ስድስት ዓመታት በየመን በርካቶችን ለሞት ለረሀብና ለበሽታ የዳረገ አስከፊ ጦርነት ተካሂዷል። ከተፋላሚ ሀይሎቹ አንዷ የሆነችው ሳውዲ አረቢያ  የሰላም እቅድ አቅርባለች።ተንታኖች  ግን የሰላም ስምምነት ማለት ጦርነቱ ያበቃል ማለት አይደለም ይላሉ።

የየመን መንግስት በኢራን ከሚደገፉት ሺአ ሀውቲ አማፅያን ጋር  በሚያደርገው ጦርነት የጠላቴ ጠላት በሚል ሳውዲ አረቢያ  ለፕሬዚዳንት አብድ ራቦ ማንሱር ሀዲ ወታደሮች ላለፉት  6 ዓመታት ድጋፍ አድርጋለች። የሳዑዲው አልጋ ወራሽ ልዑል መሐመድ ቢን ሳልማን ከዛሬ ስድስት አመት በፊት በየመኑ የርስበርስ ጦርነት ዘው ብለው ሲገቡ በሁቲ አማጽያን ላይ ፈጣን ድል ይገኛል ብለው ተስፋ ያደርጉ ነበር። በጎርጎሪያኑ መጋቢት 26 ቀን 2015 ዓ/ም የተጀመረው ጦርነት ግን ሁቲዎች በሂደት እየተጠናከሩ በመምጣታቸው የሳውዲ አረቢያ ጦርነቱን የማሸነፍ ነገር የሚሳካ አልሆነም።ከዚያ ይልቅ  ጦርነቱ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት መረጃ መሠረት ከ 230,000 በላይ ሰዎችን ለሞት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ደግሞ ለስደት፣ለረሃብና ለበሽታ ዳርጓል።ሳዑዲ አረቢያ አሁን በየመን ያለውን ጦርነት ለማቆም ሀሳብ አቅርባለች። የሳውዲ መንግሥት ባለፈው ዓመትም ተመሳሳይ ሀሳብ አቅርቦ ነበር ። የሳዑዲው  ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ልዑል ፈይሰል ቢን ፋርሃን አል ሳዑድ ሰሞኑን እንዳስታወቁት በተባበሩት መንግስታት ቁጥጥር  በመላ ሀገሪቱ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ ሀገራቸው ዕቅድ አላት። በአሁኑ ወቅት የሪያድ  ገዥዎች ራሳቸውን ከጦርነት ለማላቀቅ አጥብቀው ይፈልጋሉ። ምክንያቱም ሁቲዎች ዋና ከተማዋን ሰናዓ እና ሰፊውን የየመን ሰሜን ምዕራብ ክፍል ተቆጣጥረዋል። ሰሞኑንም በነዳጅ ዘይት በበለፀገችው በማሪብ ከተማ ላይ የማጥቃት ዘመቻ ጀምረዋል። በሳውዲ የሚመራው ወታደራዊ ጥምረት  ለዓመታት በሰንዓ የአየር ድብደባ ሲያካሂድና የሃውቲዎች አቅርቦት ለማቋረጥ አየር ማረፊያዎች እና ወደቦችን ዘግተው ቆይተዋል። ይሁን እንጅ የሰላም ዕቅዱን ተከትሎ የሀገሪቱን አቅርቦት ለማሻሻል የዋና ከተማዋ የሰንዓን አውሮፕላን  ማረፊያና የሁዲዳን የባህር ወደብ እንደገና ለመከፈት  ወስነዋል።አማጽያኑ  በሳውዲ የቀረበው ሀሳብ  አዲስ ነገር እንደሌለው በመግለጽ መጀመሪያ ላይ ውድቅ አድርገውት የነበረ ቢሆንም፤ የአማጽያኑ ዋና ተደራዳሪ መሀመድ አብዱልሰላም ከሪያድ ፣ ከዋሽንግተን እና ከኦማን መንግስታት ጋር ለቀጣይ ውይይት ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀዋል። የወደቦች እና አውሮፕላን ማረፊያዎች መከፈት ግን የሀገሪቱ የሕልውና መብት በመሆኑ ለስምምነት እንደ ቅድመ ሁኔታ መቀመጥ የለበትም ሲሉ የሳውዲን ሀሳብ አጣጥለዋል። ይህንን የሳውዲ ርምጃ ተንታኞች ከአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆባይደን ርምጃ ጋር ያይዙታል። የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ቢደን ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ በሪያድ ንጉሣዊቤተሰብ ጫናው የጨመረ ሲሆን፤ባይደን በየመን የሚደረገውን ጦርነት  እንደማይደግፉ አስታውቀዋል።ያ በመሆኑ ለሳዑዲ አረቢያ ወታደራዊ ጥምረት ከአሜሪካ ይደረግ የነበረው  የቁሳቁስ፣ የደህንነትና የስለላ ድጋፍ ተቋርጧል።በዚህ የተነሳ የመካከለኛው ምስራቅ ተመራማሪ ጊዶ ስቲንበርግ  ሳዑዲ አረቢያ በየመን ጦርነት ተሸንፋለች ባይ ናቸው።ምክንያቱም ይህ የባይደን እርምጃ  ለሳውዲያዋ ተቀናቃኝ ለኢራንና ለምትደግፋቸው የሃውቲ አማፅያን የልብልብ የሰጣቸው በመሆኑ በጦርነቱ አሸናፊ ሊሆኑ ይችላሉ።ያ በመሆኑ  ሪያድ የሰላም ዕቅድ ማቅረቧ  ተገቢ ነው ይላሉ።ስቲፍበርግ እንደሚሉት ያ ማለት ግን በየመን የርስበርስ ጦርነት ያበቃል ማለት አይደለም።ከጎርጎሪያኑ 1990 ዓ/ም ከየመን ውህደት በፊት የነበረውን የደቡብ የመን ነፃ መንግሥት እንደገና ለመመስረት ለአስርተ ዓመታት ሲታገሉ የቆዩ ሀይሎች ሊያንሰራሩ ይችላሉ።ስለሆነም በሰሜን  የሀውቲ አማፅያን በአንድ በኩል  የደቡብ  ተገንጣይ ኃይሎች እና አጋሮቻቸው በሌላ በኩል ግጭት ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ።ከዚህ በተጨማሪም ቀድሞውንም ደካማ የጤና ስርዓት ለነበራት የመን  ረሀብ፣በሽታና የኮሮና ወረርሽኝም ሌላው ጦርነት ነው።

ፀሀይ ጫኔ

ታምራት ዲንሳ

ነጋሽ መሐመድ