1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስደተኞች ፍሰትና የአውሮጳ ስጋት

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 6 2011

ሀገራቸው ላይ የሥራ ዕድል እንዲያገኙ አስፈላጊውን እርዳታ ለስደተኛ ምንጭ ለሆኑ ሃገራት ማድረግ ሕገወጡን ፍልሰት ለመግታት አንደ አንድ አማራጭ ተወስዷል። ለዚህ ታዲያ ሃገራቱ የገንዘብ እርዳታው ከፍ እንዲል ወስነዋል።

https://p.dw.com/p/36eIb

የስደተኞች ፍሰትና የአውሮጳ ስጋት

በሰሜን አፍሪቃ ሃገራት በኩል ያላባራው ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር እና የባህር ላይ ሞት ለመከላከል፤ ጥብቅ ቁጥጥር ለማድረግ የአውሮጳ ሃገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ሉክሰምበርግ ላይ ተነጋግረዋል። ወደ ሀገራቸው የሚተመውን ሕገወጥ ስደተኛ ለማገድ በሚልም በዘላቂ መፍትሄ ችግሩን ለመፍታት ማለማቸውም ነው የተነገረው። ለዚህም የሰሜን አፍሪቃ ሃገራት የበለጠ ሊረዱ የሚችሉበትን መንገድ መሻት እንዳለባቸው፤ የብዙ ስደተኞች መሸጋገሪያ የሆነችው እና የፖለቲካ ብጥብጥ አመፁ ለራሷም ችግር የሆነባት አገር ሊቢያም፤ በባህር ዳርቻዎቿ አካባቢ ጥበቃዋን እንድታጠናክር የሚሉ ሃሳቦች ተነስተዋል። የፍልሰቱን ችግር ከስር መሠረቱ እንዴት እንፍታው? የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ ትኩረት ያደረጉበት ነበር።
ኅብረቱ ለችግሩ መፍትሄ በስብሰባው ከደረሰባቸው ውሳኔዎችም፤ የአውሮጳ አገሮች የባህር ሀይል ቡድን በሊቢያ ዳርቻ የስደተኞች ላይ ቁጥጥር እንዲያደርግ እና ለሊቢያ ባህር ጠባቂዎችም ስልጠና እንዲሰጣቸው የሚሉት ይገኙበታል። 
ወደ አውሮጳውያን ሃገራት የሚገቡ ጥገኝነት ጠያቂዎች ከመካከለኛው ምሥራቅ ሃገራትና ከአፍሪቃ እንደሚሰደዱ ይታወቃል። UNHCR እንዳለው በዚህ አመት ስፔይን 9,500፣ ግሪክ 12,000 እና ጣሊያን 15,300 ከተጠቀሱት አካባቢዎች የመፈለሱ ተሰዳጆችን ተቀብለው አስተናግደዋል። ከአልጀሪያ፣ ሊቢያና ግብጽ በዚህ አመት እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር 37,034 ተሰዳጆች ናቸው ባህር አቋርጠው ወደ አውሮጳ የገቡት። አብዛኞቹም ከሰሀራ በስተ ደቡብ ከሚገኘው የአፍሪቃ ሃገራት የሚፈልሱ ናቸው።
ከአውሮጳውያኑ 2014 እስከ 2017ዓ,ም 1.8 ሚሊዮን ስደተኞች የአውሮጳን ምድር ረግጠዋል። በ2015 ብቻ 1 ሚሊዮን ስደተኞች መግባታቸውም ተመዝግቧል።
በዚያም ላይ በሰሜን አፍሪቃ ሃገራት በኩል በሕገወጥ መንገድ ድንበር ሲያቋርጡ በረሃ ላይ የሚሞቱት ሰዎች ቁጥር ቀላል የሚባል አይደለም። በዚህ አመት እንኳን ሜድትራንያን ባህር ላይ ከ1,700 በላይ ስደተኞች ሕይወታቸው አልፏል። 
ጦርነት፣ የፖለቲካ አመለካከት ወይም በእምነት ሰበብ መታሰርና መገደል ሰዎች ያለፍላጎታቸው እንዲሰደዱ ምክንያት ከሚሆኗቸው መንስኤዎች ውስጥ ይጠቀሳሉ።
ከዚህ በተቃራኒ ደግሞ ወደ አውሮጳ ለሚደረገው ስደት የተሻለ ሕይወትና ኑሮ ፍለጋም አንዱ ምክንያት ነው። ከማዕከላዊ እስከ ከፍተኛ ገቢ ያላቸው ሰዎች የተሻለ ሕይወት እንኖራለን በሚል ተስፋ ወደ አውሮጳ እንደሚሰደዱ ታውቃል። የቤተሰብና የዕድሜ አቻዎች ግፊት አብዛኞቹንም በሕገወጥ ደላሎች እጅ ይጥላቸውና በሰሜን አፍሪካዊቷ ሊቢያ እንደተመኙት አቋርጠው አውሮጳ ሳይደርሱ ባህር ውስጥ ሰጥመው የዓሣ ራት ሆነው የሚቀሩትንም ቤቱ ይቁጥራቸው። በረሀውን አቋርጠው አስገድዶ መደፈሩና ግድያውን እና ሌሎች በጉዟቸው ላይ የሚያጋጥሟቸውን አደጋዎች ተቋቁመው የሚያልፉና አውሮጳ የሚደርሱ ጥቂቶች ናቸው። 
በሰቆቃው ጉዞ የሚደርስባቸውን ማናቸውንም ኢሰብአዊ ድርጊት ተቋቁመው ወደአውሮጳ ቢገቡም የሰሙት እና በገሀድ የሚገጥማቸው ባለመጣጣሙ ከፀፀት አልፎ ለበሽታ የሚዳረጉትም ብዙዎች መናቸው የሚታይ ነው። ይህም ሆኖ የሰሃራ በረሃ እና የሜዲትራኒያን ውቅያኖስ የፈጁት የሰው ሕይወት ያልበቃ ይመስል ዛሬም የተሰዳጆች ቁጥር አልቀነሰም። 
ይህ ያሰጋቸው የስደተኞቹ መዳረሻ የሆኑት የአውሮጳ ሕብረት ሃገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ባካሄዱት ስብሰባ ከመነጋገሪያ አጀንዳቸው መካከል የስደት እና ስደተኞች ጉዳይ አንዱ ነበር። በብራስልስ የDW ዘጋቢ ገበያው ንጉሤ ካለፉት ተመሳሳይ ስብሰባዎች የተለየ ነገር የለም ይላል። 
ሀገራቸው ላይ የሥራ ዕድል እንዲያገኙ ሥራ እንዲፈጠር አስፈላጊውን እርዳታ ለስደተኛ ምንጭ ለሆኑ ሃገራት ማድረግ ሕገወጡን ፍልሰት ለመግታት አንደ አንድ አማራጭ ተወስዷል። ለዚህ ታዲያ ሃገራቱ የገንዘብ እርዳታው ከፍ እንዲል ወስነዋል። በተጨማሪም ስደተኞች ከሚመጡባቸው አገሮች ጋር በአስፈላጊ ነጥቦች ላይ በመነጋገር እና መደራደር ተሰዳጆች እንዳይመጡ ማድረግ ሌላው መፍትሄ እንደሚሆንም ታስቧል።  
በሌላ በኩል ግን ስደተኞችን እንዴት እናስተናግድ በሚለው ላይ አሁንም የሕብረቱ ሃገራት ሊስማሙ አልቻሉም። 
ቀሪውን ዘገባ በድምጽ እንድትከታተሉት እንጋብዛለን 

Italien, Salerno: Rettungsschiff Aquarius
ምስል picture-alliance/R. Basile

ነጃት ኢብራሒም 
ሸዋዬ ለገሰ