1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስደተኞች አስተዋጽኦ

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 9 2011

ከ3 ዓመት በፊት በርካታ ስደተኞች ጀርመን እንዲገቡ ሲፈቀድ፣መጤ ጠሎች እርምጃውን በመቃወም ለሀገሪቱ ሸክም ከመሆን ውጭ የሚያስገኙት ጥቅም አይኖርም ብለው ሲሞግቱ ነበር። ይሁን እና እዳ ይሆናሉ ከተባሉት ስደተኞች አብዛኛዎቹ የተለያዩ የሙያ ስልጠናዎች እየወሰዱ በፍጥነት  ሥራ ማግኘት መቻላቸው እና ከህብረተሰቡም ጋር መዋሃዳቸው አስገርሟል።

https://p.dw.com/p/3AL5b
Bildergalerie Deutschland drei Syrische Flüchtlinge finden neues Zuhause in Berlin
ምስል Reuters/A. Cocca

የስደተኞች ስኬት በጀርመን

ጀርመን የዛሬ ሦስት ዓመት ባልተለመደ ሁኔታ ድንበርዋን ክፍት አድርጋ ቁጥራቸው አንድ ሚሊዮን እንደሚደርስ የተገመተ ስደተኞችን ማስገባትዋ በሀገር ውስጥ ብዙ አነጋግሯል አከራክሯል። ክርክሩ አሁንም በየአጋጣሚው መነሳቱ አልቀረም። ስደተኞች ያኔ በብዛት እንዲገቡ መፈቀዱ ብቻ ሳይሆን  ማንነታቸውም አልተጣራም መባሉም ብዙ ሲያጨቃጭቅ ነበር። ከህብረተሰቡ ጋር ተዋህደው መኖር መቻላቸውም እንዲሁ ከአነጋጋሪዎቹ ጉዳዮች መካከል ይጠቀሳል። ያኔ፣ስደተኞች በዙ፣ ሀገሪቱን ለተጨማሪ ወጪ ይዳርጋሉ የሚሉ እና የመሳሰሉ ክርክሮች በተስፋፉበት ወቅት መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል«አያቅተንም፣እንወጣዋለን» ሲሉ መልስ ሰጥተው ነበር። ያኔ ደጋፊዎቻቸው ቢያወድሷቸውም የእርምጃው ተቃዋሚዎች ቁጣ ግን ብሶ ነበር። እርምጃው ያለ እቅድ የተወሰደ መጨረሻውም የማያምር ነው የሚሆነው ሲሉ አጥብቀው ይተቹዋቸው ጥቂት አልነበሩም። የሜርክል እርምጃም እየዋለ ሲያድር እርሳቸውን እና ፓርቲያቸውን ዋጋ አስከፍሏቸዋል። የርሳቸውን ፓርቲ የክርስቲያን ዴሞክራት ህብረት መራጮችን ጨምሮ በርካታ ጀርመናውያን ለሜርክል ጀርባቸውን እንዲሰጡ አድርጓል። ይህም ስደተኞች ጀርመን መግባታቸውን የሚቃወመው ቀኝ ጽንፈኛው «አማራጭ ለጀርመን»የተባለው ፓርቲ ብዙ ድምጽ አግኝቶ የጀርመን ፌደራል ምክር ቤት እንዲገባ እገዛ አድርጓል። ከ3 ዓመት በኋላ አሁን ግን የሜርክል ውሳኔ የሚያስመሰግን  ውጤት ተገኝቷል እየተባለ ነው። የጀርመን አሠሪዎች ማህበር ፕሬዝዳንት ኢንጎ ክሬመር የዛሬ 3 ዓመት ጀርመን ከገቡት ከአንድ ሚሊዮን እንደሚበልጡ ከሚገመቱ ስደተኞች ቁጥራቸው 400 ሺህ የሚደርሰው የሙያ ስልጠና ወስደዋል አለያም ሥራ ይዘዋል ሲሉ ተናግረዋል። ይህ ብቻ አይደለም አብዛኛዎቹ ወጣት ስደተኞች ከአንድ ዓመት የጀርመንኛ ቋንቋ ትምህርት በኋላ ጥሩ ጀርመንኛ መናገር በመቻላቸው ሳይቸገሩ በሙያ ማሰልጠኛ ትምሕርት ቤቶች ትምሕርታቸውን መከታተል እንደቻሉም ገልጸዋል።  አብዛኛዎቹ ስደተኞች የጀርመን ምጣኔ ሀብት ምሶሶ እየሆኑ ነውም ብለዋል ካርመር ። ፔተር ቫይስ የክርስቲያን ዴሞክራት ህብረት ፓርቲ የሥራ እና የማህበራዊ ጉዳዮች ኮሚቴ ባልደረባ በጉዳዩ ላይ በሰጡት አስተያየት የስደተኞች መጥፎ እንጂ ጥሩ ጎናቸው ጎልቶ እንዲወጣ በማይደረግበት ሀገር አሁን የተገኘው ይህ ውጤት ትልቅ ስኬት መሆኑን ተናግረዋል። 
«እንዳለመታደል ሆኖ ህዝቡ የሚነገረው ስደተኞች ፈጠሩ የሚባለው ችግር፣እና እንዴት ከእነሱ እንገላገል የሚለው ነው። ስለ ስኬቶቻቸው ግን አይነገርም። ከትልቁ ስኬት አንዱ ወደ 400 ሺህ የሚሆኑ ስደተኞች ጀርመን ውስጥ ሥራ ማግኘት መቻላቸው ነው። ከመካከላቸው ቋንቋውን በቅጡ የማይችሉ በጀርመን የታወቀ የሙያ ሥልጠና የሌላቸውም ይገኙበታል። ይህ የሚያመለክተው የጀርመን የስራ ገበያም ሆነ የጀርመን ምጣኔ ሀብትም ምን ያህል በፋጣኝ ብዙ የሰው ኃይል እንደሚፈልግ ነው።»
"አብዲ አባጀበል በደቡብ ጀርመንዋ በባቫርያ ፌደራዊ ክፍለ ሀገር በሙኒክ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ለስደተኞች የምክር አገልግሎት የሚሰጥ ወጣት ነው። በግሉም ስደተኞችን በተለያየ መንገድ በበጎ ፈቃድ ይረዳል። አብዲ እንደሚለው የስኬቱ መነሻ መንግሥት ከከዚህ ቀደሙ በተለየ ለስደተኞች ጉዳይ ትኩረት መስጠቱ ነው። ከዚሁ ጋር በተለይ ከስደተኞቹ በእድሜ ወጣት የሆኑት ቋንቋውን ፈጥነው መልመድ መቻላቸው ከህብረተሰቡ ጋር ለመዋሀድ ረድቷቸዋል።   
ይሁን እና አቢዲ እንደሚለው ይህ ማለት ግን ያኔ ጀርመን የገቡት ስደተኞች በሙሉ ይህን እድል አግኝተዋል ማለት አይደለም። በተለይ እርሱ በሚገኝበት በባቫርያ ፌደራዊ ክፍለ ሀገር ባለው ጥብቅ አሰራር ከህብረተሰቡ ጋር ተዋህዶ የመኖር እድል ያገኙት ስደተኞች ጀርመን የመቆየት መብት የተሰጣቸው ብቻ ናቸው።
ለአሁኑ የጀርመን ፖለቲከኞች ትኩረት ስኬቱ ላይ ሆኗል። የሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ የሥራ እና የማህበራዊ ጉዳዮች ባለሞያ ካትያ ማስት ከስኬቱ አድናቂዎች አንዷ ናቸው። ሊረዱ የመጡ ሰዎች ራሳቸውን መቻላቸው ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ጉዳይ እና መልዕክትም ያለው መሆኑን በማስረዳት። «በመጀመሪያ እዚህ የሚኖሩ እና የሚሰሩ ሰዎች ሁሉ ለኛ ሀብት ናቸው።ምን ዓይነት የውጭ የዘር ሐረግ ይኑራቸው አይኑራቸው እርዳታ ፈልገው የመጡ ሰዎች ሥራ ሲያገኙ ይህ ትልቅ ነገር ነው። እንደሚመስለኝ ይህ በጣም ጠቃሚ መልዕክት ነው።»
በሌላ በኩል የዛሬ 3 ዓመት ስደተኞች በብዛት ጀርመን መግባታቸውን በግንባር ቀደምትነት ሲቃወም የነበረው «አማራጭ ለጀርመን» የተባለው ፓርቲ ስኬቱን ወደ ጎን በመተው ወቀሳ መሰንዘሩን ነው የመረጠው። በጀርመን ምክር ቤት የፓርቲው ተጠሪ አሌግዛንደር ጋውላንድ ስደተኞቹ በጀርመን የስራ ገበያ ተፈላጊ ስለመሆናቸው የጀርመን አሠሪዎች ማህበር ፕሬዝዳንት በአድናቆት የሰጡትን መግለጫ አጣጥለዋል።
«የጀርመን አሠሪዎች ማህበር ፕሬዝዳንት በየትኛው ዓለም እንደሚኖሩ ያስገርመኛል። እርሳቸው ምናልባት በስለት ስለሚፈጸሙ ጥቃቶች አላነበቡ ወይም  ደግሞ ተማሪ ልጃገረዶችን ስለሚደፍሩት አልሰሙ ይሆናል። ይህ ሁሉ እርሳቸው ጋ አልደረሰም። ምናልባትም ሁሉንም ነገር አይተው እንዳላዩ ሲያልፉ ብቻ እንደ የአሰሪዎች ማህበር ፕሬዝዳንት ማድረግ የሚቻለው፣ይህን መሰል ፣የማይታመን ውጤት ላይ ደረስን ማለት ነው።»  
በክርስቲያን ዴሞክራት ህብረት ፓርቲ የውስጥ ጉዳዮች አዋቂ ማቲያስ ሚድልበርግ ግን ከ3 ዓመት በፊት ጀርመን ከገቡ ስደተኞች አብዛኛዎቹ የሙያ ስልጠና መውሰዳቸው እና ሥራም ማግኘታቸው ሊወደስ የሚገባው ነው ብለዋል። ሆኖም ያለሥራ በመንግሥት ድጎማ የሚኖሩ በርካታ ዜጎች መኖራቸውም ሊረሳ አይገባም ሲሉ ያሳስባሉ።
« በርካታ ስደተኞች በዘላቂነት ሊጠቅማቸው የሚችል ስልጠና ወስደው  ሥራ ማግኘት የሚችሉበትን መንገድ ማግኘታቸው በጣም ያስደስታል። ይህ በጥሩ ሁኔታ እየተራመደ ነው። እውነቱን ለመናገር በሌላ በኩል ሥራ የሌላቸው መንግሥት ድጎማ የሚያደርግላቸው በርካታ ዜጎች አሉ። በዚህ ረገድም ይበልጥ መሥራት ይኖርብናል። ያም ሆኖ ጥሩ ውጤት ላይ ደርሰናል።»
አብዲም ስኬቱን ያደንቃል ሆኖም የተገን ጥያቄአቸው ተቀባይነት ያላገኘ ስደተኞች የዚህ እድል ተጠቃሚ ስላልሆኑ ከህብረተሰቡ ጋር መዋሀድ እንዳይችሉ እንቅፋት መሆኑን ሳያነሳ አላለፈም።

Bildergalerie Deutschland drei Syrische Flüchtlinge finden neues Zuhause in Berlin
ምስል Reuters/F. Bensch
Bildergalerie Deutschland drei Syrische Flüchtlinge finden neues Zuhause in Berlin
ምስል Reuters/H. Hanschke
Deutschland Integration - Afrikaner
ምስል Imago/photothek/M. Gottschalk

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ