1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሴቶች የአለም እግር ኳስ ዋንጫ

ዓርብ፣ ሰኔ 28 2011

ፈረንሳይ ውስጥ እየተካሄደ ያለው የሴቶች የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ በመጪው እሁድ ይጠናቀቃል። ለመሆኑ ምን ያህል ትኩረት አግኝቶ ከረመ? የኢትዮጵያኑስ የሴቶች ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድንስ በምን ሁኔታ ላይ ይገኛል?

https://p.dw.com/p/3LeYh
FIFA Frauen-WM 2019 | Deutschland v Nigeria
ምስል Reuters/E. Foudrot

የሴቶች የአለም እግር ኳስ ዋንጫ

በመገባደድ ላይ ያለው የሰኔ ወር በርካታ የእግር ኳስ ውድድሮች የተስተናገዱበት ነበር። ከመካከላቸው በተለይ በጀርመን ጎረቤት ፈረንሳይ እየተካሄደ ባለው የሴቶች የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ምርጥ የተባሉት ሴት እግር ኳስ ተጫዋቾች ችሎታቸውን አሳይተዋል። ከአፍሪቃ የተሳተፉት  የካሜሩን ኢንዶሚተብል ላዮነስስ ፣ለሩብ ፍፃሜ አልፎ የነበረው የናይጄሪያ ሱፐር ፋልኮንስ እና የደቡብ አፍሪቃው ባንያና ባንያና ግን ሶስቱም ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል። ለመሆኑ የአፍሪቃውያኑ ጨዋታ ምን ይመስል ነበር? የአፍሪቃ ሴት የእግር ኳስ ተጫዋቾችስ ምን አይነት ውጣ ውረዶች ይገጥማቸዋል? የናይጄሪያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ዲዜሬ ኤሊስ ወደ ሀገራቸው እንደተመለሱ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ተጫዋቾቹ ብዙ መጣራቸውን ተናግረዋል።« የሚገባንን ውጤት አላገኘንም። ነገር ግን ቡድኑ ምንም አይነት ቁርጠኝነት አላሳየም ወይም የሚገባውን ጥረት አላደረገም ማለት አንችልም። እስከ ፍፃሜው ድረስ ታግለው ነበር ይህ ሁሉም ተመልካች ያየው ነገር ነው።»

በመጪው እሁድ የሚጠናቀቀው የሴቶች የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ውድድር ሲጀመር 24 ቡድኖች ተካፍለውበታል። የናይጄሪያ ሱፐር ፋልኮንስ ቡድን በጀርመን ቡድን ሦስት ለባዶ ተሸንፎ ወደ ሀገሩ ከተመለሰ በኋላ የ DW ባልደረባ ክሬስ ሀሪንግተን ከስፍራው ሆኖ እንደዘገበው ተጨዋቾቹ ብዙ ችላ ተብለዋል። የብሔራዊ ቡድኑ ተጫዋች ቶቹኩዉ ኦሉሂ ታብራራለች « ሱፐር ፋልኮንስ በወንዶችም ይሁን በሴቶች ከአፍሪቃ ምርጥ የሚባል ነው። ሱፐር ፋልኮንስ ለሀገሪቱ ክብር ያስገኘም ነው።  ይሁንና ሴቶች ተጨዋቾች በአግባቡ አልተያዙም። አልፎ አልፎ ሴቶቹ ችላ ይባላሉ።»

Fußball WM 2019 Frauen Team Nigeria
ምስል Getty Images/M. Hitij

ካለፈው የአለም ዋንጫ በኋላ የናይጄሪያ ተጫዋቾች  ደሞዝ ስላልተከፈላቸው ለተቃውሞ አደባባይ ወጥተውም ነበር። የዩናይትድ ስቴትስ ሴት ተጫዋቾች እንደውም ከወንዶች ተጫዋቾች ጋር ሲነፃጸር የሚከፈላቸው እጅግ አናሳ ስለሆነ ጉዳዩ ፍርድ ቤት ደርሶ ነበር። ናይጄሪያዊቷ ተጫዋች ቶቹኩዉ ግን እኛ የምንለው እኩል ይከፈለን ሳይሆን ትንሽ ትኩረት ይሰጠን ነው ትላለች። «ብዙ ማበረታታት ብዙ ድጋፍ እንሻለን። ይህ ራሱ ሞራላችንን እንድናድስ ይረዳናል።አዎ ይቻላል ብለን እንድናስብ። እነዚህ ሰዎች ግን ሞተዋል። ሊረዱን አልቻሉም። »

የናይጄሪያዎቹ ሱፐር ፋልኮንስ የገጠማቸው የገንዘብ ችግር ብቻ አይደለም።አንዳንድ ተጫዋቾች እንደውም ተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪዎች ናቸው እየተባሉ ይተቻሉ። የሆነው ሆኖ ግን የሱፐር ፋልኮንስ ተጫዋች ቶቹኩዉ እንደምትለው አላማቸው አርዓያ መሆን ነው።« እኛን ብቻ ሳይሆን ወጣቶቹንም ያበረታታል። በዛ ላይ እኛ ነን ለወጣቶቹ መሰረተ ድንጋዩን የምንጥል»

ባለፉት 30 አመታት የናይጄሪያ እግር ኳስ ተጫዋቾች ከአፍሪቃ አህጉር በብቃታቸው በምሳሌነት የሚጠቀሱ ናቸው። ኢትዮጵያዊቷ ሎዛ አበራ የኢትዮጵያ ሴቶች እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን ምክትል ካፒቴን ናት።ለአዳማ ክለብም ተጫወታለች።« የናይጄሪያውያኑ የቻሉትን አድርገዋል ብዬ አስባለሁ።በአለም ዋንጫም መሳተፋቸው በአፍሪቃ ያለውን እግር ኳስ በተወሰነ መልኩ ምን አይነት እንደሆነ አሳይተዋል ብዬ አስባለሁ።»ታሪኳ በርግነህም የኢትዮጵያ የሴቶች ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን እና የባህዳር ከነማ ክለብ ተጫዋች ነች። በመብራት መቋረጥ ግጥሚያዎችን ለማየት እንዳልቻለች ነግራናለች። ከዚህም ባሻገር የሴቶች የአለም እግር ኳስ ዋንጫ ብዙ የሚዲያ ሽፋኝ  አላገኘም የምትለው ታሪኳ ከብራዚል ቡድን ቀጥላ የአፍሪቃ ሀገራትን ተካፋዮች በተለየ አይን እንደምታያቸው ለ DW ገልጿለች። «አገርሽም እዚህ ደረጃ ቢደርስ ብለሽ እንድታስቢ ያደርግሻል።»

FIFA Frauen-WM 2019 Halbfinale | Niederlande vs. Schweden
ምስል Reuters/B. Szabo

ከ 20 ዓመት በታች የሆኑ የሴቶች ብሔራዊ ቡድን የቀድሞ አሰልጣኝ  አስራት አባተ በአሁን ሰዓት የቢሾፍቱ የወንዶች እግር ኳስ ክለብ አሰልጣኝ ሆነው ይሰራሉ። እርሳቸው ያሰለጠኑት የሴቶች ብሔራዊ ቡድን በባለፈው የዓለም ዋንጫ የመጨረሻ ማጣሪያ ጨዋታ በጋና ቡድን ተሸንፎ ነው በአለም ዋንጫ ሳይሳተፍ የቀረው።በዘንድሮው የአለም ዋንጫ የተካፈሉትን  የደቡብ አፍሪቃ ፣ የናይጄሪያ እና የካሜሩንን ቡድኖች« ጠንካራ ብሔራዊ ቡድን ያላቸው ሀገራት ናቸው። በተደጋጋሚ ጊዜም በአፍሪቃ ጨዋታዎች ላይ ብዙ ተፎካካሪነታቸውን አሳይተዋል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ቴክኒካል ዳሬክተር አቶ መኮንን ኩሩ የሴቶች እግር ኳስ ትኩረት አላገኘም ሳይሆን ቅድሚያ አልተሰጠውም ብንል ይሻላል ይላሉ። አቶ መኮንንስ በአጠቃላይ የሴቶችን ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ብቃት ሲገመግሙ « የሴቶቻችን የእግር ኳስ እድገት በጣም ፈጣን ነው።ከወንዶቹ ጋር ሲተያይ የሴቶቹ በጣም የተሻለ ነው።»

የኢትዮጵያ የሴቶች ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ነሐሴ 26፣2011 ለኦሎምፒክ እግር ኳስ ጨዋታ ማጣሪያ ከካሜሮን ቡድን ጋር ግጥሚያ ይኖረዋል። ከጋምቢያ ቡድን ጋር የነበረው የወዳጅነት ግጥሚያ ግን በገንዘብ ምክንያት ተዘርዟል። አቶ መኮንን እንደሚሉት« ለትራንስፖርት ለአንድ ሰው ከ50 ሺ በላይ ነው የተጠየቅነው።ይህ ደግሞ ከ 1,5 ሚሊዮን ብር በላይ ነው።ይህ ደግሞ አትራፊ አያደርገንም። የወንዶችም ቡድን በእንደዚህም ቦታ ቢሆን ያን ያህል ገንዘብ አውጥተን ተጠቃሚ እንሆናለን ብለን አናስብም።» ፈረንሳይ ላይ በመካሄድ ላይ ወዳለው የሴቶች የዓለም ዋንጫ ስንመለስ ጋናዊው የ DW ጋዜጠኛ ማይክል ኦቲ የእግር ኳስ ግጥሚያዎቹ በሌሎች የአፍሪቃ ሀገራትም ትኩረት እንዳያገኝ ያደረገበትን ምክንያት ያስረዳል። « ለምን እንደሆነ አላውቅም የሴቶች የዓለም ዋንጫ እየተካሄደ ያለው የአፍሪቃ ዋንጫ በሚካሄድበት ወቅት ነው። ሴቶች አፍሪቃውያን በአለም ዋንጫ ውድድር ሲጫወቱ እና ወንዶቹ በአፍሪቃ ዋንጫ ሲጫወቱ ትኩረት የሚሰጠው ለማን እንደሆነ መገመት ይቻላል። ተመልካቹ፣ስፖንሰር አድራጊው፣ በአጠቃላይ ተከታታዮቹ። ይሄን ጉዳይ FIFA ወደፊት ትኩረት ሰጥቶት መከታተል ያለበት ነገር ይመስለኛል።

Afrika-Cup 2019 | Benin vs  Kamerun
ምስል picture-alliance/dpa/G. Hamdy

ልደት አበበ

ሂሩት መለሰ