1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሴቶች መብት ይከበር

ሐሙስ፣ ኅዳር 18 2012

በኢትዮጵያ ፖለቲካ የሴቶች ተሳትፎ ምን ያህል ነዉ? የሚመሩት የፖለቲካ ፓርቲ አልያም የሴቶችን ሃሳብ የሚያካትት የፖለቲካ ፓርቲስ አለን? የሃገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ያየን እንደነ ፤ ሞትን ጥቃትን ፤ መገለንን የመሳሰሉ ጥቃቶች በመጀመርያ ደረጃ ሴቶች ተጠቂዎች መሆናቸዉ እሙን ነዉ።

https://p.dw.com/p/3Tsa7
Pakistan Marsch der Frauen beim Internationalen Frauenstag
ምስል picture-alliance/AP Photo/B.K. Bangash

አስገድዶ መድፈር ያሳፍራል

«በአሁኑ ወቅት በተለይ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚዉ ከበዛ እና በዓለም ማኅበረሰብ ዘንድ ታዋቂ ከሆነ በኋላ፤ የብዙ የሃገራችንን ሰዎች ባህሪን ስናይ ለሴቶች የሚሰጡት አስተያየትና ፤ ሴት ልጅ ስለምትሰራዉ ስራም ሆነ ምንም አስተያየት መስጠት አለመቻልዋን ፤ ስለ ፖለቲካም ሆነ በማኅበራዊ ጉዳዮች የሴት ልጅ ኃሳብን የማይቀበሉ ሰዎች የበዙበት መድረክ መሆኑን አይተናል። በሌላ በኩል ምንም እዉቀት የሌላቸዉ ከእዉቀት ነጻ የሆኑ ወንዶች ሲናገሩ መደመጥን በአንጻሩ እዉቀት ያላት ሴት ስትናገር ያለማዳመጥ ችግር ያለበት ማኅበረሰብ ዉስጥ እንዳለን የሚታይም ሆንዋል። የትም ሃገር ዉስጥ ስንኖር በኛዉ ማኅበረሰብ ዉስጥ እስካለን ድረስ ሃገራችን ዉስጥ እንዳለዉ እንደማኅበረሰባች ነዉ የምናስበዉ። ይህን በአሁኑ ሰዓት አጉልቶ ያሳየዉ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች መኖር ፤ የፖለቲካ አክቶቪስቶች መብዛት ጉዳዩን በቅርበት እንድናየዉ አድርጎአል። ይህን ችግር ለመቅረፍም ሊሰራበት የተሞከረ ነገርም ያለ አይመስልም። » ለሴቶች ፍትህ የምትለን ረዘም ላሉ ዓመታት በሰሜን አሜሪካ ነዋሪ የሆነችዉ እና በዋሽንግተን በሚገኝ የዲያስፖራ ቢሮ የምክር ስራ አገልግሎት በመስጠትዋ የምትታወቀዉ የዲያስፖራ ሬድዮ ጋዜጠኛ ቅድስት አቤኔዘር የሰጠችዉ አስተያየት ነዉ።   

Äthiopien  Addis Abeba die Gelbe Bewegung
ምስል Mehret Equbai Berhe

ሴቶችን ማጥቃት፤ መድፈር መናቅ አሳንሶ ማየት አይነት ድርጊት ይቁም ሲሉ በሳምንቱ መጨረሻ በፈረንሳይ እና በኢጣልያ በአስር ሽዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰልፈኞች አደባባይ ወጥተዉ ጥሪያቸዉን አሰምተዋል።  ቅዳሜ ኅዳር 14፤ 2012 ዓ,ም  በፓሪስ ብቻ ከ100 ሺህ በላይ ሰላማዊ ሰልፈኞች በሴቶች ላይ የሚካሄድ ጥቃት፤ ሴትን ማንቋሸሽና አሳንሶ ማየት ይቁም ሲሉ ጉዳዩ በዓለም የፖለቲካ ትኩረት እንዲሰጠዉ ጥሪ አቅርበዋል።  በዚሁ እለት የፈረንሳይ የፍትሕ ሚኒስቴር ባወጣዉ መረጃ፤ በያዝነዉ የጎርጎረሳዉያኑ  ዓመት 2019 ብቻ 116 ሴቶች በባሎቻቸዉ አልያም በፈትዋቸዉ የቅድሞ ባሎቻቸዉ ወይም ደግሞ በፍቅረኞቻቸዉ ተገድለዋል። ስለዚህም ለሴቶች ልዩ ጥበቃ እንዲደረግ ጥሪ ቀርቦአል። በፈረንሳይ ፓሪስ እና በተለያዩ የፈረንሳይ ከተሞች የሴቶች መብት እንዲጠበቅ የሚጠይቀዉ በመቶ ሺዎች የወጡበት ሰላማዊ ሰልፍ፤ በፈረንሳይ ታሪክ የመጀመርያዉ ነዉ ተብሎአል።  በዚህ በሰለጠነዉ ዓለም ሴቶችን ከመድፈርና ከማንቋሸሽ በዘለለ፤ ለሴቶች የሚሰጠዉ የደምወዝ ልክ እንደ ትምህርት ደረጃቸዉ እና ስራቸዉ ፤ የተመጣጠነ እንዲሆን የተለያዩ ተቋማት በየጊዜዉ ትግል ያደርጋሉ። በያዝነዉ ሳምንት መጀመርያ  በሴቶች ላይ ጥቃት፤ ይቁም በሚል በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታሰብበት እለት በተለያዩ ዓለም ሃገራት በተለያየ ዝግጅት ታስቦ ዉሎአል።  በሴቶች ላይ ጥቃት ይቁም በሚል በኢትዮጵያም የተለያዩ ወጣት ሴቶች እንቅስቃሴን እያደረጉ ነዉ። እለቱንም በተለያዩ ዝግጅቶች አስበዉ ዉለዋል። ከነዚህ መካከል ቢጫ ንቅናቄ አልያም በእንጊሊዘኛዉ « Yellow Movement»  በሚል ወጣት ሴቶች የተሰባሰቡበት ንቅናቄ ይገኛል።  ንቅናቄዉ የፆታ ጥቃትን ለማስቆም ንቃትን ለመስጠትና እና የሴቶች እኩልነትን ለማምጣት የተመሰረተ ነዉ ። ከንቅናቄዉ መስራች አንዷ እና የንቅናቄ አስተባባሪ ወጣት አክሊል ሰለሞን  ዘንድሮዉ  ሰኞ ኅዳር 15 ንቅናቄመጀመሩን፤ በተለይ ደግሞ የዘንድሮ ዓመት መርህ ሴቶችን አስገድዶ መድፈር ይቁም የሚል መሆኑን ገልፃለች። 

Brasilien Proteste in Brasilia nach Gruppenvergewaltigung
ምስል Reuters/U. Marcelino

« ኅዳር 15  ፆታ መሰረትን ያደረገ ጥቃትን የመቃወም ቀን ነዉ። ኅዳር 30 ደግሞ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ቀን ነዉ። እና በሁለቱም ቀናት መካከል ያሉትን ቀናት፤ ፆታን መሰረተ ያደረገ ጥቃትን በመቃወም ዘመቻ ይካሄዳል ፤ እኛም በማኅበራዊ መገናኛ ግንዛቤ እየሰጠን ዘመቻ ጀምረናል። በዚህ ዓመት የያዝነዉ ዋና ርዕስ አስገድዶ መድፈር ይቁም የሚል ነዉ። «በእኩልነት የሚያምን ትዉልድ አስገድዶ መድፈርን ይጠየፋል» በምናካሂደዉ ዘመቻ አስገድዶ መድፈር ምን ማለት ነዉ? ከኃይል ዉጭ ያለፈቃድ የሚደረግ ግንኙነትም አስገድዶ መድፈር ነዉ፤ በሚል ማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ላይ ዘመቻን እያካሄድን ነዉ። በሌላ በኩል አብዛኛዉን ጊዜ ሴቶች ሲደፈሩ መልሰዉ ሴቶቹን ራሳቸዉን የመዉቀስ ባህሪ አለ፤ ይህንንም በመቃወም ነዉ ይህ የአስራ ስድስቱ ቀናት ዘመቻችን ። በዚህ ርዕስ ላይ ግንዛቤን እንሰጣለን። ሌላዉ የሴቶችን ኩልነት ለማምጣት በተለያዩ ቦታዎች እየዞርን የዚህ ትዉልድ ምኞቶች ምን ይመስላል ስንል መዘርዝር ጥያቄዎችን አዘጋጅተን እና መልሶችን ሰብስበን በዘመቻ መጠናቀቅያ እለት፤ በመጨረሻዉ ቀን  መልሱን በዓዉደ ርዕይነት እናቀርባለን። ይህ ንቅናቄ ማለት ቢጫ ንቅናቄ ወይም ደግሞ « Yellow Movement»  ስትሉ መቼ ነዉ የጀመራችሁት?   

Tansania Proteste gegen Genitalverstümmelung von Mädchen und Frauen
ምስል DW/V. Natalis

« ቢጫ ንቅናቄ ወይም ደግሞ « Yellow Movement»  የተሰኘዉ የወጣቶች ከጀመረ አንድ ሰባት ዓመት ይሆነዋል። የተጀመረዉ በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ በሕግ ተቋም ዉስጥ ነዉ። የስርዓተ ፆታን እኩልነት ለማምጣት የሚደረግ እንቅስቃሴ ነዉ። ንቅናቄዉ በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ይጀመር እንጂ በመቀጠል በመቀሌ ዩንቨርስቲ ከባለፈዉ ዓመት ጀምሮ ደግሞ በአዋሳ ዩንቨርስቲ ይገኛል። በዋናነት እግን ንቅናቄዉ መቀመጫዉን ያደረገዉ አዲስ አበባ ዉስጥ ነዉ በዋናነት በማኅበራዊ መገናኛ የፆታ እኩልነትን ግንዛቤ በመስጠት ንቅናቄ እና ንቃትን በመፍጠር ላይ ይሰራል። ንቅናቄዉ በፆታዊ እኩልነት ላይ በወጣቶች የሚመራ ለዉጥንም ይደግፋል። »  

ወጣት አክሊል ሰለሞን እንዳለችዉ ቢጫ ንቅናቄ በሚል የሴቶችን መብት ለማስከበር የሚንቀሳቀሰዉ ንቅናቄ ዘንድሮ በዩንቨርስቲዎች ያለዉን ነባራዊ ሁኔታ ተከትሎ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ብቻ ዘመቻዉን እያካሄደ መሆኑን ገልፃለች።

በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የቢጫ ንቅናቄን የተቀላቀሉት መቅደስ አስራት የተባሉ ተከታታይ፤ በዚሁ የሴቶችን መብት በተመለከተ ያስቀመጡትን አስተያየት እንዲህ ይነበባል «አስገድዶ መድፈር በህክምና ቦታዎች ለምርመራ የሄደችን ሴት እንዲሁም በህዝብ መጓጓዣዎች ላይ ባልተገባ ሁኔታ ሴቶችን መነካካት መጋፋትና መለፋደድን ይጨምራል! አንዳንዶች በከተማ ባሶች ላይ ሴቶችን በአደባባይ ህዝብ መሃል ሊደርፉሩ ምንም አይቀራቸውም! ያንን ያልተገባ ምግባር አለመገሰጽና ሴት ልጆች ጎን አለመቆምም ከደፋሪዎች ጋር እንደመተባበር ይቆጠራል! መርፌ ለመወጋት ሄጀ ታምሜ እያቃሰትኩ የማይሆን ቦታ ሊነካካኝ የሞከረ የጤና ባለሞያ ጥፊ አልሼ አውቃለሁ እና ምን ለማለት ነው ሴቶችን እናክብር ከእንስሳት የተሻለ ማሰብ የሚችል፤ የሴቶችን በአጠቃላይ የሰዎችን ሁሉ መብት ማክበር የሚችል ትውልድ እናፍራ! እንከባበር! የበለጠ መዋደድ የሚመጣው በመከባበር ውስጥ ብቻ ነው!» ይላል

Äthiopien  Addis Abeba die Gelbe Bewegung
ምስል Mehret Equbai Berhe

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ሴቶች ምን ያህል ተሳታፊ ናቸዉ? በተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዉስጥስ የሴቶች ተሳትፎ ምን ያህል ነዉ? የሚመሩት የፖለቲካ ፓርቲ አልያም የሴቶችን ሃሳብ የሚያካትት የፖለቲካ ፓርቲስ አለን? የሃገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ያየን እንደነ ፤ ሞትን ጥቃትን ፤ መገለንን የመሳሰሉ ጥቃቶች የሚደርስባቸዉ ግን በመጀመርያ ደረጃ ሴቶች መሆናቸዉ እሙን ነዉ። የሴቶች ጥቃት ሲዘረዘር፤ ልጆቻቸዉ ፤ ባሎቻቸዉ አባቶቻቸዉ ሲገደሉባቸዉ ሰቆቃዉ ዘጠኝ ወር በማሕፀንዋ የተሸቀመች እናት ሰቆቃ በመሆኑ ነዉ። በዚህም የሴት ልጅን ጥቃት ማየት ያለብን፤ በወለድነዉ ልጁ በእህት በእናት በሴት አያታ እና አክስታች መጠን መሆን አለበት። ፖለቲካችንስ ሴቶችን ይበልጥ አሳታፊ ቢያደርግ ፤ የሴቶችን ሃሳብና መፍትሄ ቢያዳምጥ በርግጥም መፍትሄዉ አመርቂ መሆኑ ለሁሉም ግልፅ አይደለም ይላሉ?  

Demo gegen Gewalt gegen Frauen in Nairobi 17.11.2014
ምስል AFP/Getty Images/S, Maina

በፆታ እኩልነት እና ለሴቶች ግንዛቤ መስጠትን በተመለከተ የዲያስፖራ ሬድዮ ጋዜጠኛ ቅድስት አቤኔዘር፤ እንዲሁም የሴቶችን ጥቃት ለመከላከል በመንቀሳቀስ ላይ ያላችዉ የቢጫ ዘመቻ አባል፤ አክሊል ሰለሞን፤ ለሰጡን ቃለ ምልልስ እያመሰገንን ሙሉ መሰናዶዉን እንዲያደምዱ ምጡ እንጋብዛለን።

አዜብ ታደሰ

ተስፋለም ወልደየስ