1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አሳሳቢው የሴቶች ልጆች ግርዛት

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 13 2013

«እዚህ ያደጉ ወይም የተወለዱ ሴቶች ለግርዛት ወይም ለመዋለጃ አካላት ትልተላ የተጋለጡ መሆናቸውን እናውቃለን።እኛ እስከምናውቀው ድረስ አብዛኛዎቹ ወደ ሌሎች ሃገራት ተወስደው ነው ይህ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት የሚፈጸምባቸው። ወደ ሌሎች የአውሮጳ ሃገራት ለምሳሌ ብሪታንያ ወይም ኔዘርላንድ ወይም ደግሞ ወደ አረብ ሃገራት እንደሚወስዷቸው እናውቃለን።»

https://p.dw.com/p/3n718
Deutschland Berlin | Kundgebung | Genitalverstümmelung
ምስል Imago Images/C. Ditsch

የሴቶች ልጆች ግርዛት ስጋት በጀርመን

ጎጂው ልማድ ፣የሴቶች ግርዛት ወይም የሴቶች የመዋለጃ አካላት ትልተላ በበርካታ ሃገራት የተከለከለ እና የሚያስቀጣ ድርጊት ነው። ችግሩ በተስፋፋባቸው በአፍሪቃና በሌሎችም የሦስተኛው ዓለም ሃገራት ሴቶች ልጆችን ለከባድ ቋሚ የጤና ችግሮች የሚዳርገውን ይህን ጎጂ ልማድ ለመከላከል ጥብቅ ሕጎችን ወጥተዋል፤ ህብረተሰቡንም የማስተማር ዘመቻዎችም ይካሄዳሉ።ይሁንና አሁንም ይህ ጎጂ ልምድ በድብቅም ሆነ በይፋ መካሄዱ ሙሉ በሙሉ አልቆመም። ልምዱ በማይታወቅባቸው ጀርመንን በመሳሰሉ የአውሮጳ ሃገራትም የችግሩ ሰለባዎች ቁጥር ከፍ ማለት ጎጂውን ልማድ የመካለከል ዓላማ ያላቸው ማኅበራት እንዲቋቋሙ ምክንያት ሆኗል።ከመካከላቸውከአስር ዓመት በፊት በጀርመን የተቋቋመው «የሴቶች የመዋላጀ አካላት ትልተላ መከላከያ መርኃ ግብር የተሰኘው ድርጅት አንዱ ነው።የድርጅቱ ሃላፊና መሥራች ኢነስ ላውፈር ለዶቼቬለ በሰጡት ቃለ ምልልስ እንደተናገሩት ድርጅቱን የመሰረቱት በጀርመን ሴቶች ልጆችን ከዚህ ጥቃት እንዲጠበቁ ለማድረግነው።
«ምክንያቱ በጣም ቀላል ነው እኔ በዚህ ዘርፍ መሥራት የጀመርኩት ከ25 ዓመት በፊት ነው። ከ15 ዓመት በኋላ በመስኩ ምንም እንዳልተሰራ ስገነዘብ ሴቶች ልጆችም ጀርመን ውስጥ ከዚህ ጎጂ ልማድ የሚፈለገውን ያህል ጥበቃ አለማግኘታቸውን ሳውቅ በትክክል ጥበቃ እንደማይደረግላቸው ስገነዘብ ነው ድርጅቱን በጀርመን ለማቋቋም የወሰንኩት።»
ላውፈር የቋቋሙትና የሚመሩት ይህ ድርጅት የጀርመን ፖለቲከኞችና መገናኛ ብዙሀን ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጡ የሚያደርጉ ጽሁፎችንና ጥናቶችና ያቀርባል።እነዚህ ጥናቶችም ይህ ጎጂ ልማድ የተፈጸመባቸው መሠረታቸው የሴቶች ግርዛት ከሚዘወተርባቸው ሃገራት የሆነ በርካታ የውጭ ዜጎችና ልጆቻቸው ጀርመን ውስጥ እንደሚገኙ አሳይተዋል። በድርጅቱ እምነት ጀርመን የተወለዱ ወይም ያደጉ የውጭ ዜጎች ልጆች ለዚህ ችግር ተጋላጭ ናቸው።
«በበኩላችን እዚህ ያደጉ ወይም የተወለዱ ሴቶች ለግርዛት ወይም ለመዋለጃ አካላት ትልተላ የተጋለጡ መሆናቸውን እናውቃለን።እኛ እስከምናውቀው ድረስ ፣ከጥናታችን በተረዳነው መሠረት አብዛኛዎቹ ወደ ሌሎች ሃገራት ተወስደው ነው ይህ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት የሚፈጸምባቸው። ወደ ሌሎች የአውሮጳ ሃገራት ለምሳሌ ብሪታንያ ወይም ኔዘርላንድ ወይም ደግሞ ወደ አረብ ሃገራት እንደሚወስዷቸው እናውቃለን። ለምሳሌ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ይህን የሚሰሩ ክሊኒኮች አሉ።ወደ አፍሪቃ እየተወሰዱም ይህ ተግባር እንደሚፈጸምባቸው መረጃዎች አሉን።»
የላውፈር ድርጅት ምናልባት ጀርመን ውስጥም የሴቶች ልጆች ግርዛት ወይም የሴቶች የመዋለጃ አካላት ትልተላ በድብቅ ሳይካሄድ አይቀርም የሚል ጥርጣሬ አለው።ሆኖም ይህን እስካሁን በተጨባጭ ማረጋገጥ አለመቻሉን ነው ላውፈር ያስረዱት ።
«ይህን ልናረጋግጥ አልቻልንም።ግን ይፈጸማልብለን ግን እንገምታለን።።እዚህ ሃገር ይህን ለማድረግ ዝግጁ የሆኑ ሐኪሞች እንዳሉ እናውቃለን። ሆኖም እስካሁን ማረጋገጫ አላገኘንም።እዚህ ጎጆው ልማድ በምን ደረጃ እንደሚከናወን መናገር አንችልም።»
ድርጅታቸው በቅርቡ ባካሄደው የዳሰሰ ጥናት ፣የጀርመን የቤተሰብ ሚኒስቴር በጀርመን የችግሩ ሰለባ ናቸው ብሎ አስቀድሞ ካወጣው አሃዝ በላይ የሆኑ የውጭ ዜጎች መኖራቸውን አረጋግጦ ቁጥሩ እንዲስተካከል መደረጉን ላውፈር ተናግረዋል።የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጀርመን ያሉ በችግሩ የተጠቁት ቁጥር  66 ሺህ አዋቂ ሴቶችና ሴት ህጻናት  ናቸው ነበር ያለው።የላውፈር ድርጅት የዳሰሳ ጥናት ግን ይህ አሃዝ ወደ 330ሺህ እንደሚጠጋ ነው የሚያሳየው።በዳሰሳው ጥናት መሠረት ከመካከላቸው  ከ20 በላይ የሚሆኑት ሴት ታዳጊ ህጻናት ናቸው።እነዚህ ሴቶችና ህጻናት የመዋለጃ አካላት ትልተላ እንደተፈጸመባቸው የተረጋገጠው ለሕክምና በሄዱባቸው አጋጣሚዎች መሆኑን ጥናቱ ያስረዳል።ላውፈር ሌሎች አሳሳቢ የሚባሉ የጥናቱን ውጤቶችም ተገኝተዋል።
«በጎርጎሮሳዊው 2019 በተካሄደው የዳሰሳ ቅኝት ብቻ ከ20 ሺህ በላይ አዋቂ ሴቶችና ሴት ህጻናት ግርዛቱ ባስከተለባቸው የጤና ችግር ምክንያት ሕክምና ተደርጎላቸዋል።አሳሳቢው ጉዳይ ደግሞ ከመካከላቸው 200 ያህል የሚሆኑ እድሜያቸው ከ12 ዓመት በታች የሆኑ ህጻናት ይገኙበታል።ከነዚህ ውስጥ ከፊሉ ከ5 ዓመት በታች ናቸው።ይህ በጣም አሳሳቢው ጉዳይ ነው።በርግጥም የመዋለጃ አካል ትልተላ የተፈጸመባቸው ሴት ልጆች እዚህ ሃገር ይገኛሉ።ከ2016 ዓመተ ምኅረት አንስቶ የችግሩ ሰለባ የሆኑ በአጠቃላይ ከ500 በላይ ከ12 ዓመት በታች ህጻናት በግርዛት ሰበብ በደረሰባቸው የጤና ችግር ሕክምና ተደርጎላቸዋል።»
ላውፈር እንዳሉት ይህ አሃዝ ተመላላሽ ታካሚዎችን እንጂ በየሆስፒታሉ ተኝተው የታከሙትን ወይም ደግሞ የግል ሐኪሞቻቸው ጋ የሄዱትን አይጨምርም።በዚህ የተነሳም በሆስፒታል ተመሳሳይ ሕክምና ያገኙ ሴቶች ቁጥር ከዚህም የበለጠ ሊሆን ይችላል።ምንም እንኳን በዳሰሳው ጥናት እነዚህ ውጤቶች ቢገኙም ለዚህ ድርጊት ተጠያቂ የሚባሉትን ድርጊቱን የፈጸሙ ያስፈጸሙ እና ያበረታቱ ሰዎች ላይ ምንም ዓይነት ምርመራም ሆነ ክትትል አለመደረጉ የሴቶች ግርዛትን ለመከላከል ለተቋቋመው የላውፈር ድርጅት አሳሳቢ ነው።በተለይ በዚህ ጉዳይ ፖሊስና አቃቤ ሕግንን ጉዳዩን ችላ በማለታቸው ላውፈር ወቅሰዋቸዋል።
«በዚህ ጉዳይ ማለትም በልጆቹ ላይ ለተፈጸመው ዋነኛዎቹ ተጠያቂዎች ወላጆች ናቸው።የአበረታቾችም ጉዳይ ሊጣራ ይገባል።ምክንያቱም ልጆቹ ጉዳቱ እንዳይደርስባቸው መከላከል የነርሱ ሃላፊነት ነው።እነዚህ ልጆች የተገረዙት ምናልባትም ጀርመን ከመምጣታቸው በፊት በአፍሪቃ ሃገራት ሊሆን ይችላል።ሆኖም ፖሊስና አቃቤ ሕግ ምርመራ ማድረግ አለባቸው።ይህ ባለመደረጉ የድርጊቱ ፈጻሚዎች በዚህ ሃገር ውስጥ ምን ይደርስብናል ብለው የሚፈሩት ነገር የለም። በዚህ ሃገር የሴቶች የመዋለጃ አካላት ትልተላን በግልጽ የሚከለክል ሕግ አለን።ሕጉ ግን  በተግባር አልተተረጎመም።»   
ሕጉ በ2013 ዓም መውጣቱን ያስታወሱት ላውፈር በአካል ላይ የሚፈጸም ጉዳትን የሚመለከተው በሕጉ የተቀመጠው አንቀፅ ድርጊቱ እንደሚያስከስስ ቢገልጽም ቅጣቱ ግን አነስተኛ መሆኑን አስረድተዋል።እርሳቸው እንዳሉት በድርጊቱ የተከሰሰ ቢያንስ አንድ ዓመት ተኩል ይታሰራል።ቅጣቱ ድርጊቱን ያበረታቱ የቤተሰብ አካላትንም ይጨምራል።ሆኖም እርሳቸው እንደሚሉት ሕጉ ወጣ እንጂ ተግባራዊ አልሆነም።በርካታ ህጻናት የችግሩ ሰለባ ሆነው ማንም አለመከሰሱን ስህተት ብለውታል።እናም ድርጅታቸው ችግሩን በዘላቂነት መከላከያ የሚላቸውን መፍትሄዎችንም ጠቁመዋል።ላውፈር ለመገረዝ አደጋ ለተጋለጡ ሴቶች መፍትሄ የሚሉት  ፖለቲካዊ ውሳኔ ነው።  
«ለሴቶች ልጆች ሊደረግ የሚገባው ጥበቃ ፖለቲካዊ ነው ስንል የመንግሥት ሃላፊነት ነው ማለታችን ነው።ምክንያቱምለመዋለጃ አካል ትልተላ የሚጋለጡ ሴቶች ልጆች መንግሥት ሊያረጋግጥላቸው የሚገባ መሠረታዊ ሰብዓዊ መብታቸውን ነው የተነፈጉት ። የመኖር መብት ፣የሰውነትና አካል ደህንነትን የማስጠበቅ መብት ሰው የመሆን ክብርና የመሳሰሉትን መብቶች የማስጠበቅ ሃላፊነት የመንግሥት ብቻ ነው።ይህ በብዙዎች አስተሳሰብ የሲቪል ማኅበራት ሃላፊነት ተደርገው ይወሰዳሉ።ሆኖም ሴቶች ልጆችን ጨምሮ ዜጎች ከዚህ ሆነ ተብሎ ከሚፈጸም ጥቃት ጥበቃ ማድረግ የመንግሥት  ሃላፊነት ነው።ይህ ማለት በዚህ ጉዳይ ላይ ዋነኛ ተዋናይ ሆኖ ተገቢውን እርምጃ መውሰድ ያለበት መንግሥት ነው።»
ላውፈር ከዚሁ ጋር ሊወሰዱ ይገባል ያሏቸውን እርምጃዎችም ዘርዝረዋል።
«መጀመሪያ ለአደጋ የተጋለጡትን ሴቶች ልጆች መለየት።ይህም በጣም ቀላል ነው ምክንያቱም ለዚህ አደጋ የሚጋለጡት ከየትኛው ሃገር እና ከየትኛe ጎሳ የመጡ መሆናቸው ይታወቃል። እነዚህን ልጆች በግልጽ ተለይተው መታወቅ አለባቸው።ከዚያ በኋላ ደግሞ መደበኛ የሕክምና ቁጥጥርና ክትትል ማድረግ ይገባል።የcgeሩ ሰለባ መሆናቸው ከታወቀ ደግሞ ለፖሊስ ወይም ለአቃቡ ሔግ ማመልከት ግዴታ ሊሆን ይገባል።ይህ ግን አሁን ተግባራዊ እየሆነ አይደለም።ይህም ሰዎች ለምን እንደማይከሰሱ የሚያሳይ ቁልፍ ጉዳይ ነው።ሐኪሞች ለፖሊስ ወይም ለአቃቤ ሕግ ማሳወቅ አይችሉም።»
ባላውፈር እምነት እነዚህ ተግባራዊ ከሆኑ ችግሩ መፍትሄ ያገኛል።በተለይ ግርዛት መፈጸሙን የሚያውቀው ሐኪም ጉዳዩ ለሚመለከታቸው አካላት ቢያሳውቅና ጉዳዩ ይፋ የሚደረግ ከሆነ ጎጂውን ልማድ ማስቀተረት ይቻላል ይላሉ ላውፈር።ምክንያቱም  ድርጊቱ ለእስር ስለሚዳርግ በመፍራት ሰዎች ይህን ከማድረግ ይቆጠባሉ ብለው ያምናሉ።
በጀርመን የሴቶች ግርዛት ስጋት ምክንያቱና መፍትሄው ላይ ያተኮረው የዛሬው አውሮጳና ጀርመን ዝግጅታችን በዚሁ አብቅቷል።

Weibliche Genitalverstümmelung in Deutschland - Untersuchungsstuhl
ምስል picture alliance/dpa/W. Kastl
Weibliche Genitalverstümmelung in Deutschland - Straßentheater-Aktion
ምስል picture alliance / Jörg Carstensen/dpa
Infografik Genitalverstümmelung in Deutschland EN

ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ