1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስኢትዮጵያ

የሳይንስ ካፌዎች ለኢትዮጵያ ምን ይዘው መጡ?

ረቡዕ፣ መስከረም 25 2015

የኢትዮጵያ መንግሥት ሐዋሳን ጨምሮ በክልሎች ዋና ዋና ከተሞች የኢንተርኔት አገልግሎት እና ዲጂታል ቤተ-መጻህፍት ጭምር ያሏቸው የሳይንስ ካፌዎች በከፍተኛ ወጪ በመገንባት እያስፋፋ ነው። በኢትዮጵያ ከተገነቡ አምስት መሰል ተቋማት አራቱ ሥራ ላይ እንደሚገኙ የኢኖቬሽን እና ቴክሎጂ ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ዓለምነው ተናግረዋል።

https://p.dw.com/p/4HlRP
Äthiopien | Hawassa Wissenschaftscafé mit Service
ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

የሳይንስ ካፌዎች ለኢትዮጵያ ምን ይዘው መጡ?

በኢትዮጵያ የቡና እንጂ ‹‹ የሳይንስ ካፌ ›› የሚል ሥያሜን መስማት ብዙም የተለመደ አይደለም፡፡ በሀዋሳ ከተማ በ2ሺህ 500 ካሬ ሜትር ላይ የተገነባው የሳይንስ ካፌ አገልግሎቱን የጀመረው የዛሬ ሁለት ወር ገደማ ነበር፡፡ የሳይንስ ካፌ በአገራችን የተለመደ አይደለም የሚሉት የሀዋሳ ሳይንስ ካፌ ሥራ አስኪያጅ አቶ ደረጀ ደቢሳ ካፌው እንደአገር ከጥቂቶች አንዱ እንደ ሲዳማ ክልል ደግሞ የመጀመሪያው ተቋም መሆኑን ይናገራሉ፡፡

ለመሆኑ የሳይንስ ካፌ ምንድ ነው በሚል ዶቼ ቬለ DW ለአቶ ደረጀ ላቀረበላቸው  ጥያቄ ሲመልሱም ‹‹  ሳይንስ ካፌ በአጭሩ የማህበረሰቡን ሳይንሳዊ ነክ ዕውቀቶች ለማጎልበት የሚያስችል ተቋም ነው ›› ብለዋል ፡፡ ለዚህም የተሟላ አገልግሎት ለመስጠት የሚረዱ የመረጃ አቅርቦትና የሥልጠና ማዕከላት ሊኖሩት እንደሚገባም አቶ ደረጀ ገልጸዋል፡፡

የሐዋሳ ሳይንስ ካፌ
የሐዋሳ ሳይንስ ካፌምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

የሀዋሳው ሳይንስ ካፌ ምን ይዟል?

በሀዋሳ ከተማ ፉራ ቀበሌ በተንጣለለ ቅጥር ግቢ ውስጥ የተገነባው የሳይንስ ካፌ በውስጡ በኮምፒዩተር የታገዙ የዲጂታልና የሕትመት ቤተ መጽሐፍቶች ፣ የሥልጠና ማዕከላት ፣የሻይ ቡና አገልግሎት መስጫ ሥፍራዎች እና መናፈሻዎችን የያዘ ነው ፡፡ በ5 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባው ይሄው የሳይንስ ካፌ ከባለፈው የሐምሌ ወር  ጀምሮ አገልግሎት አየሰጠ እንደሚገኝ የሚናገሩት የካፌው ሥራአስኪያጅ አቶ ደረጀ ‹‹ በእርግጥ ጅምር አካባቢ የተገልጋዩ ቁጥር አነስተኛ ነበር ፡፡ በሂደት ግን ወደ ካፌው የሚመጡ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ይገኛል  ›› ብለዋል ፡፡

የ12ኛ ክፍል ተማሪ የሆኑት ፍቅር ቴዎድሮስና አቤኒዘር አየለ በሳይንስ ካፌው ከሚጠቀሙት ተገልጋዮች መካከል ናቸው፡፡ ፍቅርና አቤነዘር የሳይንስ ካፌው በመከፈቱ ተጠቃሚ ሆነናል ይላሉ፡፡ በተለይም  ካፌው በአቅራቢያቸው በመከፈቱ ቀደም ሲል ለትምህርታቸው አጋዥ የሆኑ መረጃዎችን ለማግኘት ይገጥማቸው የነበረውን ድካምና እንግልት እንዳስቀረላቸው ይናገራሉ፡፡

የሳይንስ ካፌ እንደአገር

የሐዋሳ ሳይንስ ካፌ ሥራ አስኪያጅ አቶ ደረጀ ደቢሳ
የሐዋሳ ሳይንስ ካፌ ሥራ አስኪያጅ አቶ ደረጀ ደቢሳ ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

አቶ ተስፋዬ ዓለምነው በኢኖቪሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር ናቸው፡፡ አቶ ተስፋዬ እንደሚሉት የሳይንስ ካፌ እንደአገር የሳይንስ ባህልን ለማጎልበት ታስቦ ከአምስት ዓመት በፊት የተጀመረ ኘሮጀክት ነው፡፡ አሁን ላይ በሀዋሳ ፣ በአዳማ ፣ በባህርዳር እና በአዲስ አበባ ከተሞች የተገነቡ ካፌዎች ወደ አገልግሎት እየገቡ እንደሚገኙ የሚናገሩት የሕዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ ‹‹  ካፌዎቹ የሳይንስ መረጃዎችን እንደተገልጋዩ ምርጫ በዲጂታልና በህትመት አደራጅተው የያዙ ናቸው ፡፡ በተጨማሪም የፈጠራ ዝንባሌ ያላቸው ሰዎች ተገናኝተው የሳይንስ አውደ ርዕዮችን የሚያቀርቡበት ምቹ ሁኔታን እየፈጠሩ ይገኛሉ ፡፡ ለአብነትም እስከአሁን ሁለት ትላልቅ የሳይንስና ቴክኖሎጂ አውደርዕዮች በአዲስ አበባና በአዳማ ካፌዎች ተዘጋጀተዋል ፡፡ ይህ በቀጣይ በሌሎች ካፌዎችም የሚቀጥል ይሆናል ›› ብለዋል፡፡

 የሐዋሳ የሳይንስ ካፌ ደንበኛ ፍቅር ቴዎድሮስ
የሐዋሳ የሳይንስ ካፌ ደንበኛ ፍቅር ቴዎድሮስምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

የተደራሽነት ፈተና  

በሀዋሳ የሳይንስ ካፌ ተገልጋይ የሆኑት ፍቅር ቴዎድሮስና አቤነዘር አየለ አሁን ላይ በሳይንስ ካፌው  አልግሎት ማግኘታቸው ለመጪው አገር አቀፍ ፈተና ለመዘጋጀት እንዳስቻላቸው ይናገራሉ፡፡ ይሁን እንጂ ከከተሞች ርቀው በገጠር አካባቢ ለሚገኙ ወጣቶች ተመሳሳይ የመረጃ አቅርቦቶች ተደራሽ ሊሆኑላቸው  ይገባል ይላሉ፡፡

በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ አቶ ተስፋዬ ዓለምነው ግን የሳይንስ ካፌዎችን ተደራሽነት ለማረጋገጥ በአንድ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት አቅም ብቻ የሚቻል አይደለም ይላሉ ፡፡ አሁን ላይ ወደ አገልግሎት የገቡት ካፌዎች በሞዴል ደረጃ በማሳያነት የተገነቡ መሆናቸው የጠቀሱት አቶ ተስፋዬ በቀጣይ የማስፋፋት ሥራው በከተሞችና በክልል መስተዳድሮች አቅም እንዲካሄድ በፖሊሲ ደረጃ መታቀዱን ተናግረዋል፡፡

የሐዋሳ የሳይንስ ካፌ ደንበኛ አቤነዘር አየለ
የሐዋሳ የሳይንስ ካፌ ደንበኛ አቤነዘር አየለምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

አሁን ላይ በሞዴልነት ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ ከሚኙት መካከል አንዱ የሆነው የሀዋሳ ሳይንስ ካፌ ሥራ አስኪያጅ አቶ ደረጀ ዴቢሳ በበኩላቸው ካፌው በቀጣይ አልግሎት አሰጣጡን የማስፋፋት እቅድ እንዳለው ይናገራሉ፡፡ በተለይም ከተማሪዎች በተጨማሪ የመንግሥት ሠራተኞችና አካል ጉዳተኞችን ያማከለ አገልግሎት ለማቅረብ መታቀዱን አቶ ደረጀ ገልፀዋል፡፡

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

እሸቴ በቀለ