1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሲዳማ ሕዝበ ዉሳኔ የመራጮች ምዝገባ ተጠናቀቀ 

ሰኞ፣ ኅዳር 8 2012

የሲዳማ ሕዝበ -ውሳኔ የመራጮች ምዝገባ በሰላም መጠናቀቁን ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዛሬ አስታወቀ። የቦርዱ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ከጥቅምት 27 እስከ እስከ ህዳር 6 ቀን 2012 ዓ.ም የተከናወነዉ የመራጮች ምዝገባ በሰላም ተጠናቅቋል።

https://p.dw.com/p/3TEdw
Äthiopien PK Sidama Referendum
ምስል DW/S. Muchie

ከ2.3 ሚሊዮን በላይ የመራጮች ተመዝግበዋል

የሲዳማ ህዝበ ውሳኔ የመራጮች ምዝገባ በሰላም መጠናቀቁን ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ዛሬ ሃዋሳ ላይ በሰጠው መግለጫ አስታወቀ። የድምጽ ሰጪዎች ምዝገባ ከጥቅምት 27 እስከ እስከ ህዳር 6 ቀን 2012 ዓ.ም መከናወኑን የጠቀሰው ቦርዱ እስካሁን ባለው ከ2.3 ሚሊዮን በላይ ሰዎች መመዝገባቸውን አመልክቷል። በምዝገባ ሂደቱ ከ 6 ሽህ በላይ የምርጫ አስፈጻሚዎች በ1ሽህ 692 የምርጫ ጣቢያዎች መሰማራታቸውን ገልጿል። 

የቦርዱ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ በመግለጫቸው እንዳሉት በደረሳቸው ሪፖርት እና በመስክ ጉብኝታቸው በምርጫ ጣቢያዎች የተከለከሉ ምልክቶች እና በ200 ሜትር ርቀት ውስጥ መገኘት የማይገባቸው ሰዎች መታየታቸውን እንደ ችግኝ ጠቅሰዋል። የመራጮችን ካርድ ወደ ቤት በመውሰድ ከፍተኛ ጥፋት የተገኘባቸው አንድ አስፈጻሚ ከስራ መሰናበታቸውን፣ የመራጮች መዝገብን ይዘው ከአካባቢው ለመሰወር የሞከሩ ሌላ አስፈጻሚ በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑንም አመልክተዋል። 

Soliyana Shimelis Äthiopien
ምስል DW/S.Wegayehu

ከዚህ በተጨማሪም የታዛቢዎችን እንቅስቃሴ ሲያውኩ የተገኙ አንድ ግለሰብ የምርጫ ሂደትን በማስተጓጎል ጥፋት በፌደራል የወንጀል ምርመራ እንዲደረግባቸው ተደርጓል ብለዋል። ከአስተዳደር ወሰን ጋር በተያያዘ ቀድሞ ግጭት በነበረባቸው የተወሰኑ ቀበሌዎች ከማህበረሰብ መሪዎች እና ከመስተዳድር አካላት ጋር በመነጋገር የምርጫ ጣቢያዎች የተቋቋሙባቸውን ቦታዎች በመለወጥ የምዝገባ ሂደቱ ሳይስተጓጎል እንዲከናወን ተደርጓል ብለዋል።

ታዛቢዎችን በተመለከተ የተጠየቁት ወይዘሪት ብርቱካን ትናንት እና ዛሬ ስልጠና እየተሰጣቸው መሆኑንና ተጨማሪ 160 ታዛቢዎች እንደሚመደቡ ተናግረዋል። በእያንዳንዱ የምርጫ ጣቢያዎችም የሲዳማ ታዛቢዎች የቀረቡ ሲሆን የደቡብ ክልል የሂደቱን ሚዛናዊነት ለመጠበቅና ስራው በትክክል መፈጸሙንም ለማረጋገጥ ወኪል ማስቀመጥ እንዳለባቸው ተነግሯቸው እንደነበር ገልጸዋል።

በየጣቢያዎቹ ሻፌታን ብቻ የሚወክል ወኪል እንደሚገኝ የገለጹት ሰብሳቢዋ ይህ እንዳይሆን ቦርዱ ጥረት ቢያደርግም ሊሟላ ግን አልቻለም ብለዋል። ህዝበ ውሳኔው ከመከናወኑ በፊት እና የምርጫው እለት ብሎም ውጤት ይፋ ከተደረገ በኋላ ሊገጥም የሚችል ስጋት ስለመኖሩም ተጠይቀው እስካሁን ባለን አካሄድ ምንም አይነት ችግር ይገጥመናል ብለን አናምንም ብለዋል።

ሰለሞን ሙጬ 

አዜብ ታደሰ 
ማንተጋፍቶት ስለሺ