1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የምርጫ ተሳትፎ ዝግጅት

ሐሙስ፣ ሚያዝያ 21 2013

በምስራቅ ሀገሪቱ የሚገኙ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ የኅብረተሰቡን ተሳትፎ ለማሳደግ እና ምርጫውን ለመታዘብ እየሰሩ መሆናቸውን ዐስታወቁ። 

https://p.dw.com/p/3slSk
Stadt Dire Dawa in Äthiopien
ምስል Hailegzi Mehari

ድሬዳዋ፦ ቅድመ ምርጫ ዝግጅት

በምስራቅ ሀገሪቱ የሚገኙ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ የኅብረተሰቡን ተሳትፎ ለማሳደግ እና ምርጫውን ለመታዘብ እየሰሩ መሆናቸውን ዐስታወቁ። 

የምሥራቅ ኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባዔ ተወካይ አቶ ታሪኩ ተክሉ ድርጅታቸው ኅብረተሰቡ በምርጫው እንዲሳተፍ ከማስተማር በተጨማሪ እስከ ምርጫው ፍፃሜ ሂደቱን የመታዘብ ሥራ እንደሚሰራ ገልፀው ለዚህም ሰዎች መመደባቸውን ተናግረዋል፡፡ በድሬደዋ የሚንቀሳቀሰው የድሬደዋ ሲቪል ሶሳይቲ ኔትወርክ ዳይሬክተር አቶ ተፈሪ አበራ በምርጫው የራሳቸውን አስተዋፅኦ ለማበርከት እየጣሩ መሆኑን በመጥቀስ በመስተዳድሩ ያለውን የመራጮች ምዝገባ ለማጠናከር እየሰሩ እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡ 17 አባል ድርጅቶችን ያቀፈው የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ሕብረት ዳይሬክተር አቶ መሱድ ገበየሁ መጪውን 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ የመታዘብ እና በሰብዓዊ መብት ጥሰት ተጠያቂነት በኩል ፓርቲዎቹ ባላቸው የተጨበጠ ፖሊሲ እና ስትራቴጂ ላይ ያተኮረ የምርጫ ክርክር መድረክ እንደሚያዘጋጁ አስታውቀዋል፡፡ 

ከምርጫ ጋር የተያያዘ ስራ ለሚሰሩ  ከሶማሌ ፣ ሀረሪ ፣ አፋር ክልሎች እና ከድሬደዋ አስተዳደር ለተውጣጡ  ድርጅቶች በመራጮች ትምህርት እና በምርጫ መታዘብ ዙርያ ስልጠና ተሰቷል፡፡

በሀገሪቱ በሰብአዊ መብት ጉዳዮች ላይ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ተሳትፎን ገድቦ የነበረው አዋጅ በቅርቡ መሻሻሉን ተከትሎ የተለያዩ ድርጅቶች ወደ ሥራ እየገቡ መሆናቸው ታውቋል፡፡  
መሳይ ተክሉ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ነጋሽ መሐመድ