1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሱዳን ጦር ጥቃት በአርማጭሆ

ረቡዕ፣ ሰኔ 22 2014

በምዕራብ ጎንደር ዞን ምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ የሱዳን ሠራዊት አሁንም ከርቀት መድፍ እየተኮሰ እንደሆነ የወረዳው የሰላምና ደህንነት ኃላፊ አቶ አብራራው ተስፋ ተናግረዋል፡፡ አንድ የአካባቢው ነዋሪም የሱዳን ጦር ትንኮሳውን በአካባቢው ትናንት ማምሻውን ቀጥሎ እንደነበር አስረድተዋል፡፡

https://p.dw.com/p/4DQY2
Äthiopien  West Gondar und Metema
ምስል DW/Alemenew Mekonnen

የሱዳን ጦር ጥቃት በአርማጭሆ

ሱዳን ትሪቢዩን የተባለው የሱዳን የግል ጋዜጣ ሱዳንና ኢትዮጵያ የይገባኛል ጥያቄ በሚያነሱበት የድንበር አካባቢ አልፋሽጋ አካባቢ የሱዳን ጦር በኢትዮጵያውያን ላይ ጥቃት በማድረስ በርካታ የጦር መሳሪዎችን አቃጥሏል፣ ወታደሮችንም ማርኳል በሚል ያሰራጨውን ዘገባ ሀሰት ነው ሲል የኢትዮጵያ መንግስት አስታወቀ፡፡ በሌላ ዜና የሱዳን ጦር ሰራዊት አሁንም ከርቀት መድፍ መተኮሱን እንዳላቆመ የምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ ሰላምና ጸጥታ መስሪያ ቤት አስታውቋል።  ሱዳን ትሪቡን ዛሬ ባሰራጨው ዘገባ የሱዳን ጦር ሠራዊት ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ ኃይሎች ተወሰደብኝ ያለውን እርምጃ ለመበቀል ሁለቱ አገሮች የይገባኛል ጥያቄ በሚያነሱበት የአልፋሽጋ አካባቢ ቀደም ሲል በኢትዮጵያ ስር የነበሩ “ካላ ላባን”ና “በረከት” የተባሉ አካባቢዎችን ተቆጣጥሯል ብሏል፡፡ 
ሱዳን ትሪቢዩን በውጊያው በርካታ የኢትዮጵያ የጦር ተሸከርካሪዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው በምስል የተደገፈ መረጃ ቢሰጥም በሶስተኛ ወገን ማረጋገጥ አልተቻለም፡፡ 
የኢፌድሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስተር ዶ/ር ለገሰ ቱሉ በአጭር ፅሁፍ መልዕክት ለዶይቼ ቬሌ እንዳረጋገጡት ግን መረጃው ውሸት ነው፡፡ 
ይህ በእንዲህ እንዳለ በምዕራብ ጎንደር ዞን ምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ የሱዳን የጦር ሰራዊት አካባቢው እንዳይለማ አልሞ አሁንም ከእርቀት መድፍ እየተኮሰ እንደሆነ የወረዳው የሰላምና ደህንነት ኃላፊ አቶ አብራራው ተስፋ በስልክ ገልፀዋል፡፡ አንድ የአካባቢው ነዋሪም የሱዳን ጦር ትንኮሳውን በአካባቢው ትናንት ማምሻውን ቀጥሎ እንደነበር አስረድተዋል፡፡ መድፍ ከእርቀት ከመተኮስ ያለፈ ነገር እንደሌለ የሚናገሩት የወረዳው የሰላምና ደህንነት ኃላፊ፣ በእግረኛ የሚመጡ ከሆነ የአካባቢው ታጣቂ በተጠንቀቅ ቆሟል ነው ያሉት፡፡ ህብረተሰቡ በሚተኮሱ ከባድ መሳሪያዎች ከመደናገጥ ይልቅ ተደራጅቶ፣ ዘልቀው የሚመጡ ከሆነ እየጠበቀ እንደሆነ ነው ያስረዱት፡፡ ሱዳን ሰባት ወታደሮች ሰሞኑን በኢትዮጵያ ጦረ ተገድለውብኛል በማለት ስትከስ፣ ኢትዮጵያ በአንፃሩ ድንበር ተሸግረው ወደ ኢትዮጵያ የገቡ የሱዳን ወታደሮች የተገደሉት በአካባቢው ካለው ሚሊሺያ ጋር በተፈጠረ ግጭት ነው በማለት ክሱን አጣጥላዋለች፣ ሆኖም ለጠፋው የሰው ሕይወት ኢትዮጵያ ሀዘኗን ገልፃለች፡፡ 
የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ ኮሎኔል ጌትነት አዳነ ለመገናኛ ብዙሐን በሰጡት መግለጫ ኢትዮጵያ የሱዳንን ሉዓላነት እንደምታከብር አመልክተው፣ ግን የሱዳን ጦር ከጠብ ጫሪነቱ የማይታገስ ከሆነ ከመንግስት ትዕዛዝ ከተሰጠው ሠራዊቱ የአገሩን ሉዓላዊነት በግልፅ ያስጠብቃል ብለዋል፡፡ 
ዓለምነው መኮንን 
ኂሩት መለሰ
አዜብ ታደሰ
 

Grenze Äthiopien Sudan
ምስል Alemnew Mekonnen/DW