ጦሩ ተቃውሞውን ይቀላቀል ይኾን?
ረቡዕ፣ ሚያዝያ 2 2011ላለፉት አራት ወራት በሱዳን የተቀጣጠለው የመንግሥት ተቃውሞ እንደቀጠለ ነው። ማክሰኞ እለት ብቻ መዲናይቱ ካርቱም በሚገኘው የሀገሪቱ ጦር እዝ ማዕከል ፊት ለፊት በመቀመጥ ተቃውሞ ያደረጉ ሱዳናውያን ላይ ጦሩ ተኩስ ከፍቶ ሰባት ሰዎች መገደላቸው ተነግሯል። ካለፈው ሳምንት መጨረሻ አንስቶ የተገደሉት ሰዎች ቊጥር እስከ ማክሰኞ ድረስ 15 ተጠግቷል።
በአንድ ወገን ጦሩ ከተቃዋሚ ሰልፈኞች ጋር እንዳይጋፈጥ ትእዛዝ መተላለፉ ይሰማል። በሌላ ወገን ግድያው እንደቀጠለ ነው። ያም ኾኖ ጦሩ ከተቃዋሚዎች ጋር ኅብረት መፍጠር መጀመሩን የሚያመላክቱ ዘገባዎች በተለይ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተሰራጭተዋል። የምሥራቅ አፍሪቃ የፖለቲካ ተንታኙ፦ ቶቢያስ ሲሞንም ይኽንኑ ነው የሚናገሩት።
«ዘገባዎቹ እውን የሚኾኑ ከኾነ ሰልፈኛውን የሚደበድበው ጦር በእርግጥም ጨዋታ ቀያሪ ሊኾን ይችላል።»
ባለፈው እሁድ ሱዳናውያን በጦሩ እዝ ማዕከል ፊት ለፊት ተገኝተው ፕሬዚዳንት ዖማር ኧል በሽር ከሥልጣናቸው ይውረዱ ሲሉ ከጦሩ ግልጽ ድጋፍ መታየቱ ተዘግቧል። በተለይ የቅዳሜ እለቱ ተቃውሞ በሱዳን ታሪክ ልዩ ሥፍራ አለው። ከ34 ዓመታት በፊት ቅዳሜ፤ መጋቢት 28 ቀን የያኔው ፕሬዚደንት ጃፋር ኧል ኒሜሪ በሀገሪቱ ጦር ሊወገዱ ተቃውሞ የተቀጣጠለበት ወቅት ነበር። ከ16 ዓመታት በፊት እርሳቸውን በወታደራዊ መፈንቅለ-መንግሥት ሥልጣኑ ማማ ላይ ያወጣቸው ጦሩ ነበር አውርዶ የከሰከሳቸው። የሱዳን ጦር አንዴ ከመመንግሥት መልሶ ደግሞ ከሕዝቡ ጎን ሲቆም በታሪክ ተደጋግሞ ታይቷል። የምሥራቅ አፍሪቃ የፖለቲካ ተንታኙም በዚህ ይስማማሉ።
«ሱዳን ውስጥ በሕዝባዊ አመጽ ለኹለት ጊዜያት መንግሥት ተቀይሯል፤ በ1964 እና 1985። ያኔ ታዲያ በተለይ ተቃዋሚ ሰልፈኛውን ሲደበድቡ የነበሩ ወጣት መኮንኖች መንግሥት ወደ መቀየሩ ለመሸጋገር ቀናትም አልፈጀባቸውም ነበር። እናም አኹን የትኛው የጦሩ ክፍል ከሰልፈኛው ጎን እንደሚቆም ዐናውቅም።»
የሱዳን የፀጥታ ኃይላት ልባቸው ወደየት እንዳደላ በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም። ሰኞ እለት አደባባይ የወጡ ተቃዋሚዎችን ለመበተን የሀገሪቱ የደኅንነት አባላት እና ፖሊሶች አስለቃሽ ጢስ ተኩሰዋል። እንደ ዐይን እማኖች ከኾነ ደግሞ ከሰልፈኞቹ ፊት የነበሩ የጸጥታ አስከባሪዎች የማስጠንቀቂያ ተኩስ ከፍተዋል።
እድሜያቸው በ20 እና በ30ዎቹ መካከል የሚገኙ የሱዳን ወታደሮች ከአንድ ሰው ውጪ ሌላ ይኼ ነው የሚባል ፖለቲከኛ በሥልጣኑ ማማ ላይ ዐይተው አያውቁም። ያ ሰው ሱዳንን ከሦስት ዐሥርተ-ዓመት በላይ የመሩት ፕሬዚዳንት ዖማር ኧል በሽር ናቸው።
ምዕራቡ ዓለም የሱዳን ባለሥልጣናት «ለፖለቲካ ሽግግር ግልጽ እቅዳቸውን ያስቀምጡ» ሲሉ አሳስበዋል። በሱዳን ጸረ-መንግሥት ተቃውሞ በተጠናከረበት በአኹኑ ወቅት ዩናይትድ ስቴትስ፤ ብሪታንያ እና ኖርዌይ «ለሕዝባዊው ጥያቄ የሱዳን መንግሥት ባለሥልጣናት አኹኑኑ መልስ ሊሰጡ ይገባል» ሲሉ አሳስበዋል።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ነጋሽ መሐመድ