1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሱዳን ገዢ ስንብት አንደኛ ዓመት

ሰኞ፣ ሚያዝያ 5 2012

አልበሽር በሳቸዉ ፍቃድ፣ይሁንታና ስምምነት ደቡብ ሱዳን በመገንጠሏ ምክንያት ሕዝባቸዉ ለገጠመዉ ሥነልቦናዊ፣ ፖለቲካዊና ምጣኔ ሐብታዊ ሥብራት መፍትሔ ከመፈለግ ይልቅ፣ የሊቢያን ጠንካራ ገዢ ለማስወገድ በሚደረገዉ ጥልፍልፍ የጦርና የስልላ ረጅም እጃቸዉን  ቤንጊዚ ዉስጥ ነክረዉ ሲቦጫረቁ ነበር።

https://p.dw.com/p/3aoa1
Unruhen im Sudan | Demonstration
ምስል picture-alliance/Photoshot

ሱዳን የ30 ዓመት ገዢዋን ወሕኒ የዶለችበት 1ኛ ዓመት

ታሕሳስ 2010 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሪያዉያን አቆጣጠር ነዉ) ብዙም በማትታወቀዉ የማዕከላዊ ቱኒዚያ  መለስተኛ ከተማ ዚዲ ቡዚድ ላይ የተቀጣጠለዉ ሕዝባዊ አመፅ የቱኒስ፣የካይሮ፣የትሪፖሊ አብያተ መንግሥታትን የዘመናት ወሰክ ሲያፀዳ፣ ካርቱምን ዘሎ ደማስቆ መሰንቀሩ ብዙዎችን ብዙ እንዳነጋገረ ነበር።የካርቱም ገዢዎች «ሱዳን በ1964 የራስዋን ሕዝባዊ አመፅ አስተናግዳለች» በማለት የጥያቄ፤ ንግግሩን ትኩረት ለማስቀየስ መጣጣራቸዉ አልቀረም። አቅጣጫ ለማስቀየር ሲጣጣሩ አቅጣጫ የጠፋባቸዉ የካርቱሙ ጨቋኝ፤ጨካኝ፤ ግዙፍ ዋርካ ተገነደሰ።

አዲዮስ ዑመር ሐሰን አል በሽር።ሚያዚያ 11 2019።ቅዳሜ ዓመቱ።ላፍታ እንዘክረዉ።ፕሬዝደንት ዑመር ሐሰን አልበሽር ጥር 7 2012 ትሪፖሊን ሲጎበኙ፣ ላዳዲሶቹ የሊቢያ ገዢዎች ያሉትን ሲሉ የሊቢያን የብክነት፣ ጥፋት ጉዞን፣ያዳዲስ ገዢዎችዋን አቅምና አቋም አይደለም እስከዚያ ጊዜ ድረስ 23 ዓመት  የገዙትን ሕዝባቸዉን ብሶት፣ብልጭ ድርግም የሚለዉን ተቃዉሞ ጥልቀት፤ የሐገራቸዉን ምጣኔ ሐብታዊ ዉድቀት- የመንግስታቸዉን ፖለቲካዊ ክስረት እንኳን በቅጡ ያጤኑት አልመሰሉም  ነበር።

የሱዳኖች ብሶት፣ የምጣኔ ሐብቱ ድቀትና የፖለቲካዊዉ ኪሳራ ሰበብ ምክንያት ብዙ፣ዉስብስብ፣የኃያላን ክርን፣ የቱጃሮች መዳፍ የሚጫጨነዉ መሆኑ በርግጥ አያጠያይቅም።የጎላዉ ግን አል በሽር ሊቢያን ከመጎብኘታቸዉ ከ7 ዓመት በፊት ናይቫሺ ኬንያ ላይ የፈረሙት ሰነድ ነበር።አልበሺር ኋላ ደቡብ ሱዳንን የሚያስገነጥለዉን ያን ሰነድ በ2005 የፈረሙት ሕዝባቸዉን አሳምነዉ፣ የዘመናቱን ጦርነት ለማቆም መጥቀሙን አስረግጠዉ፤በሐገር ሕዝባቸዉ ላይ የሚመጣዉን ዉድቀት የሚያስቀርበትን ስልት ቀይሰዉ አልነበረም።እንደአብዛኛዉ አምባገነን ገዢ ሰላም በማስፈን ሰበብ የጠቀለሉት ሁለት አጫጭርና  ስልጣን ላይ የመቆያ ስልት ነበር።

Sudan Khartum | Ex-Präsident Umar al-Baschir vor Gericht
ምስል Getty Images/AFP/E. Hamid

የመጀመሪያዉ፣ ምዕራባዉያን በተለይም ዋሽግተኖች የሚፈልጉትን ስምምነት በመፈረም ከዋሽግተኖች የሚገኝ ፖለቲካዊና ምጣኔ ሐብታዊ ፍርፋሪ ካለ  መቃረም ነዉ። እርግጥ ነዉ የፕሬዝደንት ጆርጅ ዳብሊዉ  ቡሽ (ትንሹ) መስተዳድር በሚስጥር በገባዉ ቃል መሰረት አል በሽር  ዉሉን ከፈረሙ በመንግስታቸዉ ላይ የተጣለዉ ማዕቀብ፣ በአሸባሪነት የመፈረጁ ዉንጀላም ይነሳለታል።

ሁለተኛዉ፣ የአልበሽር መንግሥት ሙሉ ኃይሉን የዳርፉር ጠላቶቹን ለማጥፋት፣ በዉጤቱም የዳርፉር አማፂያንን የሚረዱትን ኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊን ማስወገድ ባይችል እንኳን ለማዳከም ሊጠቀምበት ።አስቦ ነበር።

የምዕራቦች ከደገፉት፣ የዳርፉር አማፂያን ከጠፉ፣ቃዛፊን መሰል ጠላቶች ከተደካሙ የእኒያን ጠንካራ ጄኔራል ጠንካራ ክንድ ማን ይዳፍራል-ነበር ድምር ስሌቱ።ግን  የዋሽግተኖች ቃል ገቢር የሚሆንበት ዋስትና አልነበረዉም።የዳርፉሩ ዉጊያም አልቆመም።እንዲያዉም የዳርፉር ጣጣ ያን ብዙ የተለፋለትን የአል በሽርን ስልጣን ሊያስጠብቅ ቀርቶ በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ከመከሰስ አንኳ አላዳናቸዉም። ተከሰሱ።መጋቢት 2009።አልበሽር በተገኙበት እንዲታሰሩ የዘ-ሔጉ ፍርድ ቤት ዋራንት በቆረጠባቸዉ በሁለተኛ ዓመቱ  ደቡብ ሱዳኖች  ነፃነታቸዉን አወጁ።ሐምሌ 2011።

Unruhen im Sudan | Demonstration
ምስል Getty Images/AFP/E. Hamid

የደቡብ ሱዳን ነፃ መዉጣት ጁባ ላይ ሲያስፈነድቅ ለካርቱሞች ሐዘን፣ሽንፈት፣ከሁሉም በላይ ወትሮም ከድሕነት ላልተላቀቀዉ ሕዝብ የከፋ ረሐብ ርዛት መርዶ  ነበር።በዘመናት ጦርነት የላሸቀዉ፣ በማዕቀብ፣ በመገለልና በሙስና የጫጫዉ ምጣኔ ሐብት የሚደጎመዉ በአብዛኛዉ ከዛሬዋ ደቡብ ሱዳን ከሚወጣዉ ነዳጅ  ነበር።ደቡብ ሱዳን የነዳጅ ጉርጓዶችዋን ይዛ ከሱዳን ስትገነጠል የሱዳን ምጣኔ ሐብት  «ሙገሌ» እንደተመታ በሬ ባጭር ጊዜ ተሽመደመደ።

አልበሽር በሳቸዉ ፍቃድ፣ይሁንታና ስምምነት ደቡብ ሱዳን በመገንጠሏ ምክንያት ሕዝባቸዉ ለገጠመዉ ሥነልቦናዊ፣ ፖለቲካዊና ምጣኔ ሐብታዊ ሥብራት መፍትሔ ከመፈለግ ይልቅ፣ የሊቢያን ጠንካራ ገዢ ለማስወገድ በሚደረገዉ ጥልፍልፍ የጦርና የስልላ ረጅም እጃቸዉን  ቤንጊዚ ዉስጥ ነክረዉ ሲቦጫረቁ ነበር።

ጥቅምት ላይ ኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊ ቆስለዉ፤ ከተማረኩ በኋላ ቴሌቪዥን ካሜራ ፊት የመገደላቸዉ ጭካኔ አነጋግሮ ሳበቃ ሕዳር አዲሱ የሊቢያ ገዢ ሙስጠፋ አብዱልጀሊል፣ አልበሽርን ለማመስገን ካርቱም መዉረዳቸዉ አልበሽር በሊቢያ ትርምስ መዘፈቃቸዉን የሚያረጋግጥ ነዉ።

ከስድት ሳምንት በኋላ ላፀፈ ጉብኝት ትሪፖሊ የሔዱት አል በሽር የኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊ መወገድ ለሱዳን ትልቅ «ስጦታ» ነዉ አሉ፣ በፓሪስ፣ለንደን ዋሽግተኖች ሙሉ ድጋፍ ከሐብታሚቱ ሐገር አናት ላይ ተቀምጠዉ ወደ እልቂት ፍጅት ለሚጋልቧት ለሙስጠፋ አብዱል ጀሊልና ለባልደረቦቻቸዉ።«የቀድሞ አማፂዎችን ከመደበኛዉ ፀጥታ አስከባሪ ጋር ለመቀየጥ እንረዳችኋለን» ቀጠሉ የካርቱሙ ጄኔራል ። «ጥሩ ልምድ አለን። መኮንኖቻችን ዝግጁ ናቸዉ።»  

Kombobild - Sudan | Machtabgabe Militär - Algerien | Freitagsdemo

አል በሽር ትሪፖሊ ላይ ያሉትን ከማለታቸዉ ከዘጠኝ ወራት በፊት የኑሮ ዉድነት የከበደዉ ሕዝባቸዉ የቀሰቀዉን አመፅ ለጊዜዉ ደፍልቀዉ ነበር።

ታሕሳስ 2018።የአል በሽር የርዳታ ተስፋ እንደ ፓሪስ፣ለንደን ዋሽግተን መሪዎች  ቃል ሁሉ ሸፍጥነቱ ገሐድ ከወጣ ከረመ።የነሙስጠፋ የመሪነት ብቃት ሐብታም፣ሰፊ፣ ስልታዊቱን ሊቢያን የአሸባሪዎች መፈልፈያ፣ የወሮበሎች መናሐሪያ፣ የጦር አበጋዞች መፈንጪያ በማድረጉ ጥፋት ከተረጋገጠ ዓምስት አለፈዉ።

የሊቢያ መረፈካከስ፣ የሶሪያ ዉድመት ይሁን የየመን ዉድቀት ሕዝብ ያምፅብናል ብለዉ ዕንቅልፍ አጥተዉ ለነበሩት ለካርቱምና  ለመሰሎቻቸዉ የአፍሪቃና የዓረብ  አምባገነኖች ሕዝባቸዉን ለማስፈራራት ጥሩ ምክንያት ነበር።

አምባገነኖቹ በ3ስቱ ሐገራት በደረሰዉ ጥፋት የሚያጣፍጡትን ፕሮፓጋንዳ ለየዝባቸዉ ማዓልት ወሌት በሚግቱበት በዚያ ታሕሳስ፣ ብዙ ጊዜ ዉስጥዉስጡን ሲንተከተክ የነበረዉ የሱዳኖች ተቃዉሞ አትባራ ላይ ምርጊቱን በርቅሶ ወጣ። ታሕሳስ 19 2018።አመፁ ትንሺቱ ከተማ በመጀመሩ፣ ምክንያቱም የዳቦ ዋጋ ንረት ስለነበረ የካርቱም ገዢዎችን ማዘናጋቱ አልቀረም። ብዙ ግን አልቆየም።ወር ባልሞላ ጊዜ ዉስጥ አመፁ ካርቱም ገባ።ጥር 24።ሰልፈኛዉም የዳቦ፣ፉል ዋጋ ንረትን ከመቃወም አልፎ ገዢዎቹን ያወግዝ፣ ነፃነቱን ይጠይቅ ገባ።የዑማ ፓርቲ መሪ ሳዲቅ አልመሕዲ ለሕዝባዊዉ አመፅ ወጥ ፖለቲካዊ ዓላማና ግብ አበጁለት።

«በጣም አስፈላጊዉ ጥያቄ ይሕ ስርዓት ተወግዶ በብሔራዊ የሽግግር  መንግስት መተካት አለበት።የሽግግር መንግሥቱ ኃላፊነትም ሰላም ማስፈን፤ ሰብአዊ መብት ማስከበርና ነፃነትን ማረጋገጥ መሆን አለበት።የሕዝቡን ችግር የሚያቃልል የምጣኔ ሐብት እና የለዉጥ መርሐ-ግብር መንደፍ፣ሕገ መንግሥት የሚያረቅ ብሔራዊ ጉባኤ መጥራት አለበት።»

አል በሽር አመፁን ለመደፍለቅ ሰልፈኞችን ያስገድሉ፣ ያስደበድቡ፣ ያሳስሩ ገቡ።የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደነገጉ፣ የሲቢልና የጦር ሹማምንቶቻቸዉን ቀያየሩ።ለዉጥ ያሉትን መርሕ አወጁ።የሰላሳ ዘመን ብሶት ያማረረዉን ሕዝብ አመፅ መግታት ግን አልቻሉም።የሕዝባዊዉ አመፅ መጠናከር ደራሹ ሕዝባዊ ጎርፍ ጠራርጎ  እንዳይወስዳቸዉ የፈሩትንም፣ የአልበሽርን መንበር ለመቀማት የሚያደቡትንም ወይም ለሕዝብ የወገኑትንም ጄኔራሎች ባንድ አቆማቸዉ።

አልበሽር የሱዳኖችን ተቃዉሞ ከመደፍለቅ አልፎ ሊቢያ  ያዘመቷቸዉ ወይም ሊያዘምቱ ያዘጋጇቸዉ  የጦር መኮንኖንኖች፣ የዓመታት ጠቅላይ አዛዣቸዉ ትሪፖሊ ላይ ያሉትን ባሉ በስደተኛ ዓመቱ ፣ እራሳቸዉ አልበሽር በ1989 ያደረጉትን አልበሽር ላይ አደረጉት።መፈንቅለ መንግሥት።

Unruhen im Sudan | Demonstration
ምስል Getty Images/AFP/A. Shazly

«እኔ አሁን፣ እንደ መከላከያ ሚንስትርና እንደ የፀጥታ ላዕላይ ምክር ቤት የበላይ ኃላፊ የማስታዉቀዉ ነገር፣ይሕን ስርዓት ከስልጣን ማስወገዳችንን ነዉ።የስርዓቱ የበላይ በአስተማማኝ ስፍራ በቁጥጥር ስር ዉሏል።»

ጄኔራል አዋድ መሐመድ አሕመድ አዉፍ፣ መከላከያ ሚንስትር።ሚያዚያ 11።2019።ካርቱም ፈነደቀች። ድፍን ሱዳን ቦረቀች።

                          

ደስታ ፌስታ፣ፈንጠዝያዉ ግን ከሰዓት በላይ አልዘለቀም።እርግጥ ነዉ የሱዳን ሕዝብ፣  ለአደባባይ ሰልፍ አመፅ እንግዳ አይደለም።በተለይ በ1964  ያደረገዉ «የጥቅምቱ አብዮት» በዘመኑ የነበሩ አምባገነን ገዢን አስወገዷል።

ይሁንና ከየስልጣናቸዉ የሚወገዱትን  አምባገነን ገዢዎች የሚተኩት አዳዲስ የጦር መሪዎች በመሆናቸዉ የአድማ አመፁ ዉጤት  ዉል እንደሳተ ነዉ።አምና ሚያዚያም አልበሽርን ከስልጣን ያስወገዱት የጦር ጄኔራሎች ሥልጣኑን «ጊዚያዊ» በሚል ሽፋን ለራሳቸዉ መያዛቸዉ፣ ታሪክ ራሱን የመደገሙ ማረጋገጪያ ነበር።

ሱዳኖች ግን ዳግም መታለል አልፈለገም።ጄኔራል አዋድ መሐመድ አሕመድ ኢብን አዉፍ የጊዚያዊ ወታደራዊ መንግሥት ርዕሠ-ብሔር ሆነዉ ቃለ-መሐላ ሲፈፅሙ ካደባባይ ወደ ቤቱ ያልገባዉ ሕዝብ ያፍታ ቡረቃዉን አቁሞ አመፁን ቀጠለ።

አመፅ፣አድማዉ ጠንከር፣ ጠጠር፣ አድመኞቹ በርከት፣ መፈክራቸዉ ደገምገም ሲል እኒያ   ቀጭን፣ጠይም፤ ሸበቶዉ ጄኔራል የርዕሠ-ብሔርነቱን ስልጣን ለቀቁ።በዕለታት ዕድሜ፣ የ30 ዓመቱ የኃይለኞች ኃያለኛ በተረኛ ኃይለኛ ከስልጣን ተወገዱ።ተረኛዉ ኃይለኛም ሥልጣን ለቀቁ።የሱዳኖች የነፃነት፣የሰላምና የፍትሕ፣ ጥያቄ ግን መልስ አላገኘም።አድማ፣ ሰልፉ ቀጠለ።

ጄኔራል አዉፍ የመሰረቱትን የጊዚያዊ ወታደራዊ ላዕላይ ምክር ቤት የሊቀመንበርነትን ሥልጣን የተረከቡት ጄኔራል አብዱል ፈታሕ አል ቡርሐን አዲሱን ስልጣናቸዉን ለማደላደል፣ ባንድ በኩል ከተቃዉሞ ሰልፈኛዉ መሪዎች ጋር መደራደር፤ በተቃራኒዉ ሰልፈኛዉን በሐይል እያስመቱ የሚደራደሯቸዉን መሪዎች ማዉገዝ እንደ ጥሩ መንታ ስልት ይከተሉ ገቡ።

ጄኔራሉ እንዳሰቡት የመንታዉ ስልት ጥቅል ዉጤት ሰልፈኛዉ ፈርቶ፣በጊዜ ሒደት ተሰላችቶ ወይም በመሪዎቹ ላይ እምነት አጥቶ ይበተናል ነበር።ድርድሩ እንደቀጠለ ፀጥታ አስከባሪዎች ካርቱም ከሚገኘዉ ከመከላከያ ሚንስቴር ዋና ማዘዢያ አጠገብ ለቁጭታ አድማ የተሰበሰበዉን ሕዝብ ለመበተን በዱላ ይቀጠቅጡት፣ በጥይት ይቆሉት ያዙ።ቁጥራቸዉ በዉል ያልተነገረ ሰዎች ሞቱ፣ በርካቶች ቆሰሉ።

ጄኔራል  አብዱል ፈታሕ ቡርሐን ያዘመቱት ጦር ሰላማዊ ሰዎችን ለመግደል ማቁሰሉ የሰልፈኛዉን መሪዎች ወነጀሉ።ድርድሩንም አቋረጡ።ግንቦት 16።2019።«ስለዚሕ በፈጣሪ ፊት፣በሕዝባችን፣ በጦራችንና በአብዮታችን ፊት የሚከተሉትን የመወሰን ኃላፊነት አለብን።ስምምነቱ እንዲቀጥል ተገቢዉን ድባብ ለመፍጠር ይቻል ዘንድ ድርዱን ለ72 ሰዓታት ማቋረጥ።የቁጭታ አድማ በሚደረግባቸዉ አካባቢዎች የቆሙ መከላከያ አጥሮችን በሙሉ ማስወገድ።በነዳጅ ዘይትና በሌሎች ሸቀጦች እጥረት ችግር ላጋጠማቸዉ ግዛቶች ሸቀጦቹ እንዲደርሱ የተዘጋዉን የባቡር መስመር መክፈት።»

ጄኔራሉ ጨከኑ።በተለይ የጊዚያዊ ወታደራዊዉ ላዕላይ ምክር ቤት ምክትል ሊቀመንበር ጄኔራል መሐመድ ሐምዳን ዳግሎ፣ ሐሚቲ (በቅፅል ስማቸዉ) የሚያዙት ፈጣን ድጋፍ ሰጪ ኃይል የተባለዉ ጨካኝ ጦር ይበልጥ ጨከነ።ሰልፈኛዉን፣ አደራጆቹን ሌላዉ ቀርቶ ሐኪሞችን ሳይቀር እያሳደደ ያስር፣ይደበድብ፣ያቆስል፣ሲከፋም ይደፍርና ይገድል ገባ።

ሕዝቡም አልተበገረም።ሙታኑን እየቀበረ፣ቁስለኞቹን እያከመ ተቃዉሞዉን ቀጠለ።ወንዶቹ ሲደክሙ፣ ሲወድቁ ወይም ሲቆስሉ ሴቶቹ የመሪነቱን ሥፍራ እየተረከቡ ሰልፈኛዉን «የደም ዋጋ ደም ነዉ»ን ያስፈክሩት ያዙ።

                                      

ሰኔ 3 2019 የሆነዉ ግን በሱዳን የተቃዉሞ ሰልፍ ታሪክ ብዙም የማይታወቅ ነዉ።የዳርፉር ደፈጣ ተዋጊዎችን ለመደምሰስ ከተመሠረተዉ የግመለኞች (ጃንጃዊድ) ሚሊሺያ ጦር የተመለመለዉ የፈጣን ድጋፍ ሰጪ ጦር፣ ሰልፈኛ-አድመኞቹን በመደዳ ረሸናቸዉ።ሴቶቹን እያሳደደ ደፈራቸዉ።ቀጠቀጣቸዉ።ካርቱም በደም ጨቀየች።

የመብት ተሟጋቾችና ተቃዋሚዎች እንደሚሉት «የካርቱም ጭፍጨፋ» በተባለዉ  በሰኔ 3ቱ የኃይል እርምጃ ሲያንስ 118፣ ሲበዛ 241  ሰላማዊ ሰዉ ተገድሏል።ብዙ መቶዎች ቆስለዋል።78 ሴቶች ተደፍረዋል።ወታደራዊዉ  ሁንታ የሰየመዉ አጣሪ ኮሚቴ  ግን የሟቾቹን ቁጥር 87 ብሎታል።

Sudan Khartum Machtabgabe Militär
ምስል Getty Images/AFP/A. Mustafa

የኢትዮጵያዉን ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ እና የአፍሪቃ ሕብረት መሪዎችን ከአዲስ አበባ አሩጦ ካርቱም የዶለዉ፣ የሰኔ 3 የካርቱም ጭፍጨፋ ነዉ።ግፉ የእዉነተኛ የድርድር በርም ከፈተ።

በገዳይ አስገዳይነት የሚወነጃጀሉትን፣ በጥርጣሬ የሚተያዩትን፣ የተከፋፈሉትን የጦርና የፖለቲካ መሪዎች ተጣማሪ የሽግግር መንግሥት እንዲመሠርቱ ለማግባባት የኢትዮጵያና የአፍሪቃ ሕብረት በሳል ዲፕሎማቶችን ብልሐት፣ክሒል፣ ትዕግሥትን፣ የአረብ ቱጃሮችንና የዓለም ኃያላንን ጫና ጠይቋል።

ግን ተሳካ።ሁለቱ ወገኖች የሽግግር መንግሥት ለመሰስረት ተስማሙ።ነሐሴ 17፣ 2019 ።ካርቱም የሰላሳ ዘመን ገዢዋን ባሰናበተች በ5ኛ ወሯ፣ የግፍ ስዉዖችዋን በቀበረች በሁለተኛ ወር-ከሁለተኛ ሳምንቷ ፈገገች።ፈነጠዘች።3 ዓመት ከ3 ወር የሚዘልቀዉን የሽግግር መንግስት በጠቅላይ ሚንስትርነት እንዲመሩ የተሰየሙት እዉቁ የምጣኔ ሐብት ባለሙያ አብደላ ሐምዶክ የሽግግር መንግሥቱ መርሕ የአብዮቱ ዓላማ እንደሚሆን ቃል ገቡ።

«የሽግግር መንግስቱን መርሐ-ግብር የሚመሰረተዉ የአብዮቱ መሰረታዊ ዓላማ በሆኑት ነፃነት፣ሰላምና ፍትሕ (ማስፈን) ላይ ነዉ።ማዕከላዊዉን ጥያቄ ከግብ እንዳደርስ ፍቀደሉኝ።ቁጥር አንድ ቅድሚያ የሚሰጠዉ ጦርነቱን ማቆምና ዘላቂ ሰላም ማስረፅ ነዉ።»

ጦርነቱ በርግጥት ቆሟል።ዘላቂ ሰላም ተመስርቷል ማለት ግን ያጠራጥራል።ጠቅላይ ሚንስትሩ ራሳቸዉ ባለፈዉ መጋቢት ዘጠኝ ከግድያ ሙከራ ለጥቂት ነዉ ያመለጡት።የጦር ኃይሉና የሲቢል ፖለቲከኞቹ ሽኩቻም ሙሉ በሙሉ አልተወገደም።ከሁሉም በላይ ሕዝቡን ተቃዉሞ የጫረዉ የምጣኔ ሐብት ድቀት ዛሬም ያቺን ደሐ፣ሰፊ፣የየዋሆች ሐገር እየፈደፈዳት ነዉ።

ለወትሮዉ የሱዳንን ምጣኔ ሐብት ለመጠጋገን እጃቸዉን የሚዘረጉት የአረብ ቱጃሮች ኢራንን ለማሳጣት፣የመንን ለማጥፋት፣ ለዶሐ-ሪያዶች መበቃቀል ገንዘባቸዉን ስለሚረጩ ለአፍሪቃዊቱ አረባዊት ሱዳን የተፈለገዉን ያክል አልደረሱላትም።የሱዳን አብዮት ግን የሕዝብን ኃይል ኃይል አስመስክሯል።አልበሽርም ወሕኒ ቤት ናቸዉ።

ነጋሽ መሐመድ

ኂሩት መለሰ