1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሱዳን ከድርድር ማፈንገጥ፤የአልነጃሽ መስጊድ ጉዳትና የኢትዮጵያዊቷ ግድያ በጣሊያን

ዓርብ፣ ታኅሣሥ 30 2013

የሱዳን ከህዳሴዉ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር ማፈንገጥ፣የጥንታዊዉ የአልነጃሽ መስጊድ ጉዳት እንዲሁም በጣልያን የኢትዮያዊቷ አጊቱ ጉደታ የግፍ ግድያና እሱን ተከትሎ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አበቤ አስከሬኗ ወደ አዲስ አበባ እንዲመጣ መጠየቃቸው ሲያነጋግር ነበር የሰነበተው።

https://p.dw.com/p/3nfx8
Symbolbild I BigTech I Social Media
ምስል Ozan Kose/AFP/Getty Images

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች

የሱዳን ከድርድር ማፈንገጥ፤የአልነጃሽ መስጊድ ጉዳትና የኢትዮጵያዊቷ ግድያ በጣሊያን

አንዳች መነጋገሪያ የማያጡት የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በዚህ ሳምንትም የሱዳን ከህዳሴዉ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር ማፈንገጥ፣የጥንታዊዉ የአልነጃሽ መስጊድ ጉዳት እንዲሁም በጣልያን የኢትዮያዊቷ አጊቱ ጉደታ የግፍ ግድያና እሱን ተከትሎ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አበቤ አስከሬኗ ወደ አዲስ አበባ እንዲመጣ መጠየቃቸው ሲያነጋግር ነበር የሰነበተው። 

Äthiopien Addis Abeba | Diskussion Blue Nile & Renaissance-Damm | Flaggen
ምስል DW/G. Tedla

ታላቁ የህዳሴ ግድብን በተመለከተ የኢትዮጵያ፣ የግብጽ እና የሱዳን የውሃ ጉዳይ ሚኒስትሮች በበይነ-መረብ ሊያካሂዱት ታስቦ የነበረው ስብሰባ ሱዳን ባለመገኘቷ ሳቢያ ሳይካሄድ መቅረቱን የኢትዮጵያ የውሃ፣ የመስኖና የኢነርጅ ምንስቴር በሳምንቱ መጀመሪያ አስታውቋል። በሶስትዮሽ ምክክሩ የዕለቱ ሰብሳቢ የነበረችው ኢትዮጵያ ባስተላለፈችው ጥሪ መሰረት የግብጽ ልዑክ እንዲሁም የአፍሪካ ህብረት ባለሙያዎች እና ታዛቢዎች በዕለቱ ቢገኙም ሱዳን ግን የውሃ ሽታ መሆኗን ነበር ምንስቴር መስሪያ ቤቱ የገለፀው። የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በማግስቱ ባወጣው መግለጫ ደግሞ የግብጽና የሱዳን ፍላጎት ግድቡን ማስቆም፤ ካልተቻለ የግንባታውን ሂደት ማስተጓጎል ነው። ብሏል።

ይህንን ተከትሎም ጉዳዩ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚዎች ዘንድ  መነጋገገሪያ ሆኖ ነበር የሰነበተው። መኩሪያ አባይ«የግድቡ ስራ አይቋረጥ እንጂ እነሱ ተገኙ አልተገኙ ችግር የለውም።» ሲሉ፤ ሃዉስ ኦፍ ፌዝ በሚል የፌስቡክ ስም የሰፈረው አስተያየት ደግሞ «ሰዳን ምነው ያዙኝ ልቀቁኝ አበዛች። ወዲህ ቢሉ ድንበር መድፈር ወዲያ ቢሉ ከድርድር መውጣት።ባለቤቱን ካልናቁ አጥሩን አይነቀንቁ ነው ነገሩ።ያም ሆነ ይህ የኛ ስራ ግድቡን እንደጀመርነው በመተባበር መጨረስ ነው። የነሱ መምጣት መሄድ አጀንዳችን ሊሆን አይገባም።»ብለዋል።

 ሀይሉ ዶሪ በበኩላቸው «የግብፅ እና የሱዳንን ሴራ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሊከሽፈው እና በንቃት ሊታገለው እንዲሁም  ከመቼውም ጊዜ በላይ በአንድ ላይ ሊቆም ይገባል።»የሚል አስተያየት ሰንዝረዋል።ጎሳዬ አባይነህ ደግሞ «ትላንት የተስማማችበትን ትታ ዛሬ መቅረት ትክክለኛ አቋም እንደሌላት ያሳያል።እየታዬ ያለው የሴራ ፖለቲካ ከባድ ነው።የኢትዮጵያን ትንሳኤ ለማፋጠን በእኛ በኩል የራሳችንን የቤት ሥራ በጥንቃቄና በፍጥነት መሥራት ነው።»ብለዋል።

ዓለም መላኩ የተባሉ አስተያየት ሰጪ« ጉዳዩ የሱዳን ብቻ አይመስለኝም።ግብፅና ሱዳን የህዳሴ ግድብን አጀንዳ ከአፍሪካ ኅብረት ለማውጣት የፈጠሩት ዘዴ ነው።»ሲሉ ገልፀዋል።

ሃና በቀለ በበኩላቸው« እርስ በርሳችን ተከፋፍለን ስንናቆር በራችን ለውጭ ጠላት ተከፈተ።በዚህ ከቀጠልን እንደሀገር መቀጠላችንም እንጃ።» በማለት ስጋታቸውን አስፍረዋል።

«ዶሮ ሳይጮህ ሶስት ጊዜ የካደው ጴጥሮስ ትውልዱ ሱዳን ይሆን እንዴ?»በማለት ጉዳዩን ወደ ቀልድ የወሰዱት ደግሞ ዮሀንስ አድነው ጆቴ ናቸው።ማሞ ታዳ በበኩላቸው«እኛ ለማሸነፍ የመጀመሪያ እርምጃ አንድታችን ነው ።ከተባበርን ማንም አያሸንፈንም ። እየጎዳን ያለው የእርስ በርስ መጠላላትና መገዳደል ነው።እርስ በራሳችን ሳንከባበር ማን ሊያከብረን ይችላል።»በማለት አስተያየታቸውን ቋጭተዋል።

Äthiopien Grand-Ethiopian-Renaissance-Talsperre
ምስል AFP/Maxar Tech

ሌላው በዚህ ሳምንት የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚዎችን ያነጋገረው ጉዳይ በትግራይ ክልል ውቅሮ ከተማ አቅራቢያ የሚገኘው ጥንታዊዉ የአልነጃሽ መስጊድ በቅርቡ በህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይና በፌደራል መንግስቱ መካከል በተካሄደው ጦርነት ሳቢያ ጉዳት እንደደረሰበት መታወቁ ነበር።ይህንን ተከትሎም በአል-ነጃሺ መስጊድና መካነ ቅርስ ላይ ጉዳት ያደረሱ አካላት ተይዘው ለሕግ እንዲቀርቡ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ጠይቋል።

አየልኝ አንጋው የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይ«ቅርሡ የሁሉም ሀብት በመሆኑ የጥፋቱን ባለቤቶች ፈጣሪ እንደሥራቸው ይመልከታቸው።የስራቸውንም ይስጣቸው።» ሲሉ፤

ላያስችል አይስጥ. በሚል የፌስ ቡክ ስም የሰፈረው አስተያየት ደግሞ «በጣም የዘቀጠ አስተሳሰብ ማለት የ እምነት ቦታዎችን በማፍረስ በማቃጠል ለሺ አመታት ተዋልዶ፣ ተዋዶና ተከባብሮ የሚኖረውን ህዝብ ለግል ጥቅም ሲሉ ለማጋጨት መሞከር ነው።»ሲሉ፤ሀይሌ ቦላ የተባሉ አስተያየት ሰጪ በበኩላቸው «ቤተክርስቲያናትን ያቃጠሉ ፣አንገት የቀሉና የንፁሀንን ደም ያፈሰሱም በህግ ይጠየቁልን።»የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።

ሰኢድ ደመቀ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ «ቅርሶች ጉዳት ሲደርስባቸው ሌላ ታሪክ ይደርቡና ይበልጥ ያብባሉ እንጅ አይደበዝዙም !»በሚል ርዕስ ከኑረዲን ኢሳ ገፅ ተጋርተው በረጅሙ ካሰፈሩት ፅሁፍ ለንባብ በሚስማማ መልኩ በጥቂቱ እንዲህ ይቀርባል።

«እንደ ኢትዮዽያዊ በጋራ የምንኮራበት የነጃሺ መስጊድ ላይ ጉዳት በመድረሱ ብዙዎች ሲያዝኑ ውለዋል :: እኔም አዝኛለሁ። ይሁን እንጅ በመስጊዱ ላይ የደረሰው ጉዳት ለመስጊዱ ተጨማሪ ታሪክ ፈጥሮ ታሪካዊነቱን ያጎላው እንደሆነ እንጅ አያደበዝዘውም። ይሄ ባይሆን መልካም ነበር። ሲሆን ግን የከፋ ውድመት ባለመድረሱ ተፅናንቻለሁ። ስለዚህ እንደ ሙስሊምም እንደኢትዮጵያዊም የከፋ ውድመት ባለመድረሱ አልሃምዱሊላህ።ነጃሽ ግን ሌላ የሃያንደኛው ክፍለዘመን አዲስ የጥፋት ታሪክ ደርቦ ይቀጥላል።ቁምነገሩ ወዲህ ነው።መንግስት በዚህ የጋራ ታሪካዊ ቅርሳችን ላይ የደረሰውን የጉዳት መጠን አጥንቶ ወደቀድሞው ይዞታው የሚመለስበትን ሁኔታ ያመቻቻል ወይ ......?ነው።እንጅ ነጃሺማ ሌላ አዲስ ምዕራፍ ፈጥሮ ከነከራማው ይቀጥላል።አልሃምዱሊላህ!»

ከድር ሙሀመድ «ነጃሺ በካባድ መሳሪያ የተደበደበውና የወደመው ጦርነቱ አልቋል ተብሎ ከታወጀ ከ 20 ቀን በኃላ ነው።ይህ ነገር በደንብ መጣራት አለበት።»ሲሉ፤

እውነት ይቀድማል በሚል ስም የሰፈረው አስተያየት ደግሞ«ምንም ቅርስ ስይነካ መቐሌ ገባን ብላችሁ አልነበር። ይህንን ነገርስ ከስትዌሽን ሩም አልተመለከታችሁትም?»ብለዋል።

ዛሬ ነገ በሚል የፌስ ቡክ ስም የሰፈረው አስተያየት ደግሞ «ከህንጻ ሰው ይቀድማል ጦርነትን አውግዙ።» ሲሉ፤ «መስጂዱ የኔም ነው።ጉዳዩ ተጣርቶ እርምጃ ሊወሰድ ይገባል። ግን ደግሞ ጦርነት በሌለበት አካባቢ ስለፈራረሱ የሰው ልጆች ዝም  ያለ የሃይማኖት መሪና ፖለቲከኛ አሁን ሲንጫጫ ሳይ የጎደለ ነገር እንዳለ ይሰማኛል።»ያሉት ደግሞ ነፃነት ይልቃል ናቸው።

Äthiopien Al-Nejashi Moschee in Tigray
ምስል Mohamed Ali/DW


በጣሊያን ሀገር ትኖር የነበረችው ኢትዮጵያዊቷ አጊቱ ጉደታ በምትኖርበት አካባቢ በሰው ዕጅ በግፍ መገደሏ በርካታ ኢትዮጵያዉያንን  ያሳዘነ ጉዳይ ነበር።አጊቱ በምትኖርበት ጣሊያን ሀገር በእንስሳት እርባታ የተሳካላት የንግድ ሰው የነበች ሲሆን፤ ለስደተኖች መብት በመሟገትም የምትታወቅ ኢትዮጵያዊት እንደነበረች በርካታ የውጭ ሀገር የመገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።ይህንን ተከትሎ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲቫ  አዳነች አበቤ የአጊቱ አስከሬን ወደ ትውልድ ቦታዋ ወደ አዲስ አበባ ከተማ እንዲመጣ በውጭ ጉዳይ በኩል ጥያቄ ማቅረባቸው ተሰምቷል።ይህም በርካታ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚዎችን አነጋግሯል።

ፍፁም መንግስቴ የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይ «ሞት ያለጊዜው ሲሆን በጣም ያሳዝናል። ጭካኔ ሲጨመርበት ደግሞ ያማል።የኔ እህት ነብስሽን ይማረው።»ሲሉ፤

ዓለም በሀይሉ«አጊቱ ጉደታ ነፍስሽ በሰላም ትረፍ! አስክሬንሽም በሰላም ወደ ሀገሩ ይመለስ! የሚገርመው ግን እኛ እዚህ ያለነው ተቀባዮችሽ በዘር ተከፋፍለን እየተገዳደልን በእስካቫተር ነው ምንቀበረው! » ብለዋል።ሃና ሙለታ«ለቤተሰባቿ እግዚአብሔር መፅናናቱን ይስጣቸው። ነብሷንም ይማር።»ሲሉ፤ያሬድ መሰረት ደግሞ «ከሰው ይልቅ አስክሬን ትወዳላችሁ።እሷ በህይወት እያለች ለሰው ልጆች ማድረግ ያለባትን ያደረገች ጀግና ነች።እናንተ የምታደረጉት ግን ያጎድፋታል ተዋት በያንዳንዱ ነገር ፖለቲካ መስራት አይሰለቻችሁም።»በማለት ተችተዋል።

Äthiopien Einkommensministerium | Pressekonferenz Adanech Abebe
ምስል DW/S. Muchie

«መንግስት በነካ እጁ በጅምላ በእስካቫተር የተቀበሩትን ምስኪኖችም በክብር ያሳርፍልን።»ያሉት ደግሞ ዳናዊት የተባሉ አስተያየት ሰጪ ናቸው።

ሶሎሞን  ወልደማርያም «ወይ ሀገሬ ስው መሞት የለበትም።ገዳዮቹ ለፍርድ ይቅረቡ ብሎ መታገልና ድምፅ እንዳማሰማት በሙታን ላይ መጣላት።ለሞት የዘር.ምድብ መስጠት ምን የሚሉት ልክፍት ነው? »በማለት ፅፈዋል።ቱቱ አለማየሁ በበኩላቸው«የሀዘን ቀንስ አይታወጅም? መቼም ነገራችን ሁሉ እንዳይሆን እንዳይሆን ሆኗል ።»ብለዋል።

ደጀኔ ኦላና የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይ ደግሞ አስተያየታቸውን እንዲህ አስፍረዋል።

«ሀገሯ ላይ በነፃነት መኖር አቅቷት በስደት ተቀብላ እንደ ዕንቁ አክብራ ቦታ ሰጥታ በፍቅር ያኖቻ ሀገር፡ በህይወት ባትኖርም ታሪኳን አጣፍጠው ህያው እንድትሆን ለኛም ለዓለምም ያካፈለችው አገሯ ጣሊያን ብትቀበር ይሻላል። ባይሆን በሰላም በነፃነት ሀገር ሀውልቷን ሂደን እንጎበኛለን። ቤተሰቦቿም በቻሉ ጊዜ ይህንኑ ቢያደርጉ ይሻላል።ኢትዮጵያማ ለመኖሪያም ለመቀበሪያም የምትመች ሀገር አልሆነችም።»

አብዱል መነን ሰይፉ የተባሉ አስተያየት ሰጪ በበኩላቸው « ለማንኛውም ጉዳዩ ከዘረኝነትና ከተረኝነት ጋር ምንም ንክኪ የለውም።ልጅቱ ዓለም የዘገበላት ጀግኒት ነበረች። ጀግና ደሞ ሊዘከርም ሊከበርም ግድ ነው። ፈጣሪ  ነብስሽን በገነት ያኑርሽ ውድ እህቴ» ሲሉ፤ ኪሩቤል አስረስ ደግሞ «መርጠን እያዘንን መርጠን እየቀበርን እንዴት ሀገር እንሁን እንዲህ ተበታትነን» በማለት አስተያየታቸውን በግጥም አስፍረዋል።

 

ፀሐይ ጫኔ

ነጋሽ መሀመድ