1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሱዳን ኃይሎች ዘረፋ እየፈፀሙ ነዉ 

ዓርብ፣ ጥር 7 2013

የሱዳን ኃይሎች አሁንም የዘረፋ ተግባራቸውን መቀጠላቸውን በምዕራብ ጎንደር ዞን የምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ ነዋሪዎችና የአካባቢው ባለሥልጣናት አመለከቱ፣ በዚሁ ዞን መተማ ወረዳም ሱዳን ኃይሏን እያጠናከረች እንደሆነ ነዋሪዎች ተናግረዋል፤ ሱዳኖች አቁስለው ንብረታቸውን እንደዘረፉባቸው የአብደራፊ ከተማ ነዋሪዎች አመልክተዋል።

https://p.dw.com/p/3nyEz
Äthiopien Sudan Grenzgebiet Landwirtschaft
ምስል Alemnew Mekonnen/DW

የአካባቢው ነዋሪዎች ከፍተኛ ስጋት ፈጥሮብናል ይላሉ


የሱዳን ኃይሎች አሁንም የዘረፋ ተግባራቸውን መቀጠላቸውን በምዕራብ ጎንደር ዞን የምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ ነዋሪዎችና የአካባቢው ባለሥልጣናት አመለከቱ፣ በዚሁ ዞን መተማ ወረዳም ሱዳን ኃይሏን እያጠናከረች እንደሆነ ነዋሪዎች ተናግረዋል፤ ሱዳኖች አቁስለው ንብረታቸውን እንደዘረፉባቸው የአብደራፊ ከተማ ነዋሪዎች አመልክተዋል። ነዋሪዎቹ ሱዳን ከደንበር ጥያቄ ባለፈ ኢትዮጵያን የመውረር ህልም አላትም ብለዋል፡፡
አቶ ፋሲል አሻግሬ በምዕራብ ጎንደር ዞን ታች አርማጭሆ ላይ አቦቲር በተባለ አካባቢ በእርሻ ልማት የተሰማሩ ሲሆን የሱዳን ኃይሎች በፈጠሩት ጥቃት የሰሊጥና የማሽላ ሰብላቸው ተቃጥሎና ተዘርፎ ወደ አብደራፊ መምጣታቸውን ተናግረዋል፡፡ አቶ ፋሲል እንደሚሉት ሱዳን አሁን የምታካሂደዉ ትንኮሳ የደንበር ጥያቄ ሳይሆን ኢትዮጵያን ለመወረር የተዘጋጀች ይመስላል ብለዋል፡፡
አቶ ዳምጤ መውሻ የአብደራፊ ከተማ ነዋሪ ሲሆኑ ከከተማው 6 ኪሎ ሜትር በሚርቅ አካባቢ በጎችን ያረባሉ፣ ሁልጊዜም እንደሚያደርጉት ባለፈው ማክሰኞ በጎቻቸውን ለመጎብኜት ወደ አካባቢው ሲደርሱ የሱዳን ኃይሎች ከብበው እንደተኮሱባቸውና እንዳቆሰሏቸው 750 የሚሆኑ የእርሳቸውንና የጓደኛቸውን በጎች እንደዘረፉባቸው ገልፀዋል፡፡
በዚሁ ዞን መተማ ወረዳ የሽንፋ ከተማ ነዋሪው አቶ እያዩ ፈቃዱ እንዳሉት ደግሞ በቅርብ እርቀት ሰፊ ቁጥር ያለው የሱዳን ጦር እየተሰባሰበ መሆኑን አመልክተው በአብደራፊ እንዳለው ዓይነት ተኩስ በየቀኑ ባይኖርም አልፎ አልፎ እንደሚተኩሱ ተናግረዋል፡፡
የአካባቢው ነዋሪዎች ከፍተኛ ስጋት እየተፈጠረባቸው እንደሆነና አንዳንዶቹ ወደ መሀል አገር እየሄዱ እንደሆነ የአብደራፊ ከተማ ነዋሪው አቶ ፋሲል አስረድተዋል፡፡
የምድረ ገነት (አብደራፊ) ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አይሸሽም ጎንቼ በስልክ ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩት የሱዳን ኃይሎች አሁንም ትንኮሳቸውን አልተውም፤ ይተኩሳሉ፣ ይዘርፋሉ። ጉዳዩን አስመልክተው የምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሙሉዓለም ታደሰ እንዳሉት የሱዳን ጦር አሁንም በአካባቢው ችግር እየፈጠረ እንደሆነና ዘረፋ እየፈፀመ እንደሆነ አረጋግጠዋል፡፡ ሱዳንና ኢትዮጵያ 750 ኪሎሜትር የሚረዝም የጋራ ድንበር ይዋሰናሉ፡፡

Äthiopien Sudan Grenzgebiet Landwirtschaft
ምስል Alemnew Mekonnen/DW
Äthiopien Sudan Grenzgebiet Landwirtschaft
ምስል Alemnew Mekonnen/DW


ዓለምነው መኮንን
አዜብ ታደሰ 
ኂሩት መለሰ