1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሱዳን ሩሲያ ግንኙነት እና ቻድ ከዴቢ ሞት ከአንድ አመት በኋላ

ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 15 2014

ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ በወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ከስልጣን ከተወገዱ ከስድስት ወራት በኋላ ሱዳን እንደገና መንታ መንገድ ላይ ሆናለች። የሱዳን ወታደራዊ ሃይል በተባበሩት መንግስታት ድርጅት መሪነት ወደ ዲሞክራሲ ያመራል ተብሎ ሲጠበቅ በአሁኑ ወቅት  ለምዕራቡ ዓለም ባላንጣ  ወደ ሆነችው ሩሲያ ፊቱን ማዞሩ እያነጋገረ ነው።

https://p.dw.com/p/4AKkk
Sudan Proteste
ምስል AFP/Getty Images

ትኩረት በአፍሪቃ


በዛሬው የትኩረት በአፍሪቃ ዝግጅት  የሱዳን መንግስት እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እሰጣ እገባ እንዲሁም ምዕራብ አፍሪቃዊቷ ሀገር ቻድ ፕሬዚዳንቷን በሞት ካጣች ከአንድ አመት በኋላ  በሀገሪቱ ያለው የፖለቲካ ሁኔታ ምን ይመስላል የሚለውን ይዳስሳል ።
የሱዳን ወታደራዊ መንግስት በሀገሪቱ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተልዕኮ ላይ የሰነዘረውን ከባድ ትችት ተከትሎ።ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶካ በወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ከስልጣን ከተወገዱ  ከስድስት ወራት በኋላ ሱዳን እንደገና መንታ መንገድ ላይ ሆናለች።በተባበሩት መንግስታት ድርጅት መሪነት በሱዳን ህዝብ የታለመው የስቪል አስተዳደር ምስረታ እና ዲሞክራሲያዊ ሽግግር ስለመሳካቴ  ባለሙያዎች ከፍተኛ ጥርጣሬ ገብቷቸዋል። 
የሱዳኑ ወታደራዊ መሪ ጄኔራል አብደል ፋታህ ቡርሃን እና ሌሎች ወታደራዊ አባላት በቅርቡ በተልዕኮው መሪ ፎልከር ፔርቴስ ላይ  አመፅ እንዲደረግ ጥሪ ሲያሰሙ ቆይተው “ከአገሪቱ እናስወጣለን” ሲሉ ዝተዋል።የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ንግግሩን አውግዟል።ከዚህ በተጨማሪ  የሱዳን ጦር በተባበሩት መንግስታት ድርጅት መሪነት ወደ  ዲሞክራሲ ያመራል ተብሎ ሲጠበቅ በአሁኑ ወቅት  ለምዕራቡ ዓለም ባላንጣ  ወደ ሆነችው ሩሲያ ፊቱን ማዞሩ እያነጋገረ ነው።
ቴዎዶር መርፊ በአውሮፓ የውጭ ግንኙነት ምክር ቤት የአፍሪካ ዳይሬክተር ናቸው።እሳቸው እንደሚሉት የተባበሩት መንግስታት በሱዳን ችግር የገጠመው በአንድ ጊዜ ሁለት ግብ ለማሳካት በመሞከሩ ነው።
«በሱዳን የሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ተልዕኮ ችግር የገጠመው በአንድ ጊዜ ሁለት ተቃራኒ ግቦችን ለማሳካት በመሞከሩ ነው።ሲቪሎቹ እና ደጋፊዎቻቸው የተባበሩት መንግስታት ሽምግልና እንደ ጥብቅና እንዲሆን ይጠብቃሉ።በሠራዊቱ ላይ ጫና በማሳደር  እንዲቀበል ማስገደድ።ሌላው አላማ በተለመደው ሽምግልና በወታደሩና እና በስቪሉ ህዝብ  መካከል የሚደረግ የድርድር ሂደት ነው።ይህ ደግሞ በተለየ አመክንዮ የሚመራ ነው። አሸማጋዩ  በእያንዳንዱ ወገን ያለውን የሃይል ሚዛን በመለካት በመሃል መፍትሄ ለማምጣት የሚደረግ ሙከራ ነው።»
በጎርጎሪያኑ የካቲት 24 -ቀን 2022 ዓ/ም  ሩሲያ በዩክሬን ላይ ጥቃት የሰነዘረችበት ጊዜ - የፈጣን ድጋፍ ኃይሎች  ኃላፊ እና የሱዳን  ወታደራዊ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት መሐመድ ሃምዳን ዳጋሎ ወይም ሄሜቲ ፣በሞስኮ ከሩሲያ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ጋር ተወያይተዋል። ይህ የጀነራሉ ውይይት መርፊ እንደሚሉት ለሱዳን ሩሲያ ግንኙነት  ሰውየው ቁልፍ ተዋናይ መሆናቸውን ያሳያል።

Russland Mohamed Hamdan Dagalo und Sergey Lavrov in Moskau
ምስል Sudan's Presidential Palace/Handout/AA/picture alliance
Sudan Khartum | UN-Sondergesandter Volker Perthes
ምስል Ashraf Shazly/AFP/Getty Images

በጄኔራል ቡርሀን የሚመራው ወታደራዊ መንግስት ደግሞ ሄሜቲ በሩሲያ ድጋፍ ከስልጣን እንዳያወርደው ስጋት አለው ይላሉ።
«ሩሲያን በተመለከተ በሲቪሉ እና በጦር ኃይሉ መካከል የማይመሳሰል  የጋራ ጥቅም አለ ፣ እናም ሦስተኛው ተዋናይ ሄሜቲ (መሐመድ ሃምዳን ዳጋሎ ፣ እንዲሁም ሄሜቲ በመባልም ይታወቃል) ፣ የፈጣን ድጋፍ ኃይሎች መሪ ፣ ለሩሲያውያን ተመራጭ አጋር ናቸው ። እናም ሄሜቲ ነው  ሩሲያውያንን በጣም  አጥብቆ  ሲፈልግ  የነበረው። እነሱም ለዚህ ለፍላጎቱ   አዎንታዊ ምላሽ እየሰጡ ነው።ስለዚህ በወታደራዊው ሀይል በኩል ያለው ስጋት ሄሜቲ በሩሲያ ድጋፍ ሊያስወግደን ይችላል የሚል  ነው።ህዝቡም ያንን ስጋት ይጋራል።»
ነገር ግን ይህ የሱዳን ሩሲያ  ግንኙነት አዲስ አይደለም። ይላል  ለንደን የሚገኘው  ሱዳናዊው የማህበራዊ አንቂ መሐመድ ኢልናይም።መሀመድ እንደሚለው ግንኙነቱ  ከአልበሽር ዘመን ጀምሮ የነበረ ነው።
 «እውነታው ግን የ«ዋግነር ግሩፕ» ሱዳን ውስጥ ከኦማር አልበሽር ጊዜ ጀምሮ የነበረ ነው። በእርግጥም ከ2017 የሶቺ ጉባኤ በኋላ በሽር ሱዳን የሩስያ የአፍሪካ ቁልፍ እንደምትሆን  ተናግረዋል። ያኔ ነበር ለምሳሌ ቀይ ባህር ላይ የባህር ሃይል ለመመስረት ስምምነቶች የተደረጉት።በሱዳን የሚገኘው ወታደራዊ ተቋም ከአንድ ወር በፊት በነበረው ድርድር እና ውይይትም እንደገና እንደሚከፈት ፍንጭ ሰጥቷል።እውነታው ግን ሩሲያ ሱዳን ውስጥ ነበረች። የ«ዋግነር ግሩፕ»ም በሱዳን ለዓመታት ቆይቷል።»
የሱዳን  ህዝብ መፈክር «ወታደሮቹ ወደ ሰፈራቸው ይመለሱ» የሚል እንደነበር የሚገልፀው መሀመድ፤  ከመፈንቅለ መንግስቱ በኋላ ግን የሱዳን ህዝብ  በወታደራዊው ሀይል አማካኝት የዲሞክራሲያዊ ስርአት ሽግግር መንገድ የለም ብሎ ተቀብሏል። እንዲያውም ይላል መሀመድ አሁን ያጋጠመን  ትልቁ ችግር  ወደ ኋላ ተመልሰን ከጦር ኃይሉ ጋር በጠረጴዛ ዙሪያ ለድርድር እንድንቀመጥ እየተጠበቀ ነው።በመሆኑም የህዝቡን ትግል ወደ ኋላ ሊመልስ የሚችለውን ሁሉ ሩሲያንም ጭምር መታገል  አለብን በማለት ገልጿል።
በሌላ በኩል ሞስኮ የሱዳንን የወርቅ ማዕድን ሀብት እና ስልታዊ አቀማመጥ ላይ ከፍተኛ ፍላጎት ስላላት ትብብሩን ማሳደግ ትሻለች።ታዛቢዎች እንደሚሉት የሱዳን ወርቅ ሩሲያ በዩክሬን ጦርነት ምክንያት የተጣለባትን አለማቀፋዊ ማዕቀብ የሚያስከትለውን ጉዳት ለማቃለል ረድቷል ይላሉ።በተቃራኒው ካርቱም ወሳኝ የሆነውን የምዕራባውያን ድጋፍ አጥታለች።ከሩሲያ ጋር ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር መሞከሩም ካርቱም የሚገኘው የኤበርት ፋውንዴሽን ባልደረባ ክሪስቲን-ፌሊስ ሮህርስ እንደሚሉት ሀገሪቱ ከ1993 እስከ  2019 ዓ/ም በአልበሽር ዘመን  እንደነበረው ዓለም አቀፍ መገለል ውስጥ ልትገባ ትችላለች የሚል ፍራቻ አለ።
ቻድ ከዴቢ ሞት ከአንድ አመት በኋላ
ከአንድ ዓመት በፊት  የቻድ ፕሬዝደንት የነበሩት ኢድሪስ ዴቢ ኢቶ እራሱን የቻድ የለውጥ እና የአንድነት ግንባር  እያለ ከሚጠራው አማፂ ቡድን ጋር  በፋለም ላይ እያሉ ግንባር ላይ ነበር ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ። የእሳቸውን ሞት ተከትሎ የ38 አመቱ  ልጃቸው ጄኔራል ማሃማት ኢድሪስ ዴቢ ኢትኖ የአባታቸውን የ30 አመት  የስልጣን ውርስ ለማስቀጠል  በጦር ሀይል ታግዘው መንበረ መንግስቴን  ወዲያው ተቆጣጠሩ።ኢድሪስ ዴቢ ከመሞታቸው ጥቂት ቀደም ብሎ የስልጣን ቆይታቸውን ለማራዘም ሌላ ምርጫ አሸንፈው ነበር።ምዕራባውያን ዴቢን በሳህል ክልል የሚንቀሳቀሱትን አሸባሪዎች ለመዋጋት ጠንካራ  አጋር አድርገው ይመለከቷቸው ስለነበር የልጃቸውን ስልጣን መያዝ  ጦርነቱን ለማስቀጠል እንደ ማረጋገጫ ተወስዷል።በጄኔራል ዴቢ የሚመራው የዛሬው ወታደራዊ የሽግግር መንግስት  በ18 ወራት ውስጥ በሀገሪቱ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ እንደሚያካሂድ ባለፈው አመት ቃል ገብቷል። ያ ቀነ ገደብ አሁን  እየቀረበ ቢሆንም  ብዙ ተንታኞች ግን መሬቱ ገና ለምርጫ ለም ላይሆን ይችላል የሚል ስጋት አላቸው።
ጃቲካይ በተባለው የሰብዓዊ ደህንነት እና የሰላም ግንባታ ተቋም  የፀጥታ ባለሙያ የሆኑት አዲብ ሳኒ፤ ከጋና ዋና ከተማ አክራ በስልክ ለDW እንደተናገሩት ስልጣኑን ጄኔራል ዴቢ ከተቆጣጠሩ ወዲህ በሀገሪቱ ምንም አይነት ለውጥ አልመጣም።
«በቻድ ውስጥ ብዙም የተቀየረ ነገር የለም።አሁንም በወታዳራዊ ሀይል ችግሮችን  ለመፍታት ይሻሉ።የደህንነት ስጋት አሁንም በዚያ አካባቢ ትልቅ ችግር ነው። በተለይ ለእኔ የሚያሳስበኝ ሽብርተኝነትን ከቻድ  ወደ ጎረቤት አገሮች መስፋፋቱ ነው።ከዚያም አልፎ በምዕራብ አፍሪቃ ንኡስ ክልል የደህንነት ስጋት ሆኗል። ስለዚህ በኔ አስተያየት ብዙም የተቀየረ ነገር የለም።»
ጄኔራል ዴቢ የአባታቸውን ስልጣን ከወረሱ ወዲህ በጎርጎሪያኑ ሚያዝያ 2021 ዓ/ም 15 አባላት ባሉት ወታደራዊ ሀይል ሀገሪቱን የመግዛት እቅዳቸውን ሲያስተዋውቁ፣ ጉዳዩ ተቃውሞ ለማስነሳት ብዙም ጊዜ አልወሰደም።በዚህ የተነሳ በወቅቱ ወታደራዊውን አገዛዝን በመቃወም  በቻድ ዋና ከተማ  በርካታ ሰዎች ለተቃዉሞ ወደ ጎዳና ወጥተዋል። በሌላ በኩል ያለፈው መጋቢት ወታደራዊው አገዛዝ በኳታር ዶሃ ከአማፂያኑ ጋር የተደረገ ውይይትም ብዙ ፍሬ እያፈራ አይደለም።ምክንያቱም  የቻድ አማፂያን እና የወታደራዊ መንግስት መልዕክተኞች ፊትለፊት ተገናኝተው ለመደራደር ፈቃደኛ አልሆኑም።ከአንድ አመት በፊትም ወታደራዊው መንግስት ከአማፂያኑ ጋር ስምምነት ላይ ለመድረስ  በመዘግየቱ ለቀድሞው ፕሬዚዳንት ሞት ምክንያት ሆኗል።ይህ በእንዲህ እንዳለ ወታደራዊው አገዛዝ እስከ ግንቦት 10 ቀን ድረስ ሀገሪቱን ወደ ስቪል አስተዳደር ለመመለስ ሀገር አቀፍ መድረክ እንደሚዘጋጅ ገልጿል።ይህ "አካታች ሀገራዊ ውይይት" የተለያዩ ፓርቲዎችን እና የታጠቁ ቡድኖችን ለማሰባሰብ የታሰበ ቢሆንም፤  ዕቅዱ ስጋት ላይ መሆኑ እየተነገረ ነው።ምክንያቱም አማፅያኑ በገዥው ወታደራዊ ሀይል እምነት የላቸውም። ያ በመሆኑ የቻድን የተቃዋሚ  የፖለቲካ ፓርቲዎች  በመድረኩ እንደይሳተፉ አማፂያኑ በማስፈራራት ላይ ናቸው።ይህም ሀገሪቱን  ውጥረት ውስጥ ከቷታል።ሳኒ እንደሚሉት  ድርድር እስካልተካሄደ ድረስ በቻድ ለተፈጠረው ቀውስ ዘላቂ መፍትሄም ማምጣትም ሆነ  ሀገሪቱን ወደ ሲቪል አስተዳደር መመለስ አይቻልም። 
«ሽምግልና ግማሽ መንገድ ላይ መገናኘት ነው።ነገር ግን የተለያዩ ወገኖች በጣም ሥር የሰደዱ  ውጥረቶች እና አቋሞች ካሏቸው ጊዜ እና ሀብትን ማባከን ይሆናል።ጠቃሚ ስለሆነ  በግማሽ መንገድ ላይ ተገናኝተው ችግሩን እንዲፈቱ ተስፋ አደርጋለሁ። ወታደራዊ ሀይል በዚህ ዓለም መቼም የትም መፍትሄ ሆኖ አያውቅም።»
በፈረንሳይ የሚመራው አለም አቀፉ ማህበረሰብ የአባታቸውን ሞት ተከትሎ ለማሃማት ኢድሪስ ዴቢ ኢትኖ ድጋፍ አሳይቷል። ጄኔራል ዴቢ በወቅቱ ከአውሮፓ ኅብረትም ድጋፍ አግኝተዋል።ሳኒ እንደሚሉት ምንም እንኳን በክልሉ የሚደረገውን የፀረ ሽብር ትግል ለመቀጠል የአውሮፓ ህብረት ድጋፍ ቢያደርግም፤ ከወታደራዊው ሀይል ለሽግግሩ ሂደትም የቁርጠኝነትን ማየት ይፈልጋል።ከዚህ በተጨማሪ አማፅያን እና  ተቃዋሚዎች ዴቪ ሀገሪቱን ወደ ሲቪል አገዛዝ ከመለሱ በኋላ ለምርጫ እንደይቀርቡ ማረጋገጫ እየጠየቁ ነው። ይሁን እንጂ ይህ ሊሆን የማይችል ነው ይላሉ ሳኒ።እንዲያውም የእሳቸው ስጋት ከዚህ የተለዬ ነው።
«አባቱ ከሞተ በኋላ  እሱ ሁሉንም ነገር  ተቆጣጠሮታል። የእኔ ስጋት ምርጫ ቢደረግም (ዲቢ) እሱ ሊቆጣጠረው እና ሊያሸንፍ ይችላል። ከዚያም በመርህ ደረጃ እራሱን በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠ መሪ ብሎ ይጠራል።ከዚህ በጣም የራቀ ሆኖ እያለ።»በማለት ስጋታቸውን ገልፀዋል።
በሀገሪቱ ከዲሞክራሲያዊ አስተዳደር፣ ከአማፂያን እና ከሽብር ስጋት ባሻገር የኢኮኖሚ ችግርም ሌላው ራስምታት ነው።እንደ ተባበሩት መንግስታት ድርጅት 5.5 ሚሊዮን የሚሆኑ ቻዳውያን የአስቸኳይ ጊዜ  እርዳታ ያስፈልጋቸዋል።እንደ ዓለም ባንክ ዘገባ ደግሞ 16 ሚሊየን የሀገሪቱ ህዝብ 42 በመቶው በድህነት ውስጥ ይኖራል።በተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ልማት  ጠቋሚ መረጃ መሰረት ቻድ ከአለም ሶስተኛዋ ደሃ ሀገር ነች። በአሁኑ የዩክሬን ጦርነት እና የኮሮና ወረርሽኝ ተፅእኖ ደግሞ የቻድ ኢኮኖሚ ይበልጡኑ እያሽቆለቆለ ነው።ሳኒ እንደሚሉት ሀገሪቱ ቀላል የሚባለውን የዳቦ ችግር እንኳ መፍታት አልቻለችም።በመሆኑም ለእሳቸው ዘላቂ ደህንነትን ማረጋገጥ ለቻድ ብቸኛ የቀውስ መውጫ መንገድ ነው።
ፀሀይ ጫኔ
እሸቴ በቀለ

Tschad N'Djamena | Demonstration der wakit Tama Bewegung
ምስል Blaise Dariustone/DW
N'Djamena, Chad | Demonstration gegen die Junta
ምስል Djimet Wiche/AFP/Getty Images
Tschad l Mahamat Idriss Deby , Militär
ምስል Christopeh Petit Tesson/AFP/Getty Images
Sudan | Pro-Demokratie-Demonstranten trotzen dem harten Vorgehen nach dem Putsch
ምስል DW
Sudan politische Krise | Abdel Fattah al-Burhan
ምስል Mahmoud Hjaj/AA/picture alliance