1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሰዎች ለሰዎች ድርጅት በኢትዮጵያ

ረቡዕ፣ የካቲት 16 2014

የሰዎች ለሰዎች ድርጅ በምሥራቅ ኢትዮጵያ በድርቅ የተጎዱትን፣ በሰሜን ኢትዮጵያ ደግሞ ጦርነት ችግር ለጋረጠባቸው ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረግ እና ለመልሶ ማቋቋም ከፍተኛ በጀት መድቦ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አስታወቀ።

https://p.dw.com/p/47T6l
Äthiopien | Menschen für Menschen sendet Hilfe für Binnenvertriebene

«በጦርነት እና በድርቅ የተጎዱትን ለመርዳት እየተንቀሳቀሰ ነው»

በኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ የሚንቀሳቀሰው እና ላለፉት 40 ዓመታት ልዩ ልዩ የልማት ሥራዎችን በማከናወን ላይ የሚገኘው ሜንሽን ፊዩር ሜንሽን ማለትም ሰዎች ለሰዎች በመባል የሚታወቀው ድርጅት በዚህ ዓመት ለሚከውናቸው ሥራዎቹ 900 ሚሊዮን ብር በጀት መመደቡን ተናገረ። የኢትዮጵያውያን ወዳጅ ተብለው በሚጠሩት ዶ/ር ካርል ሃይንዝ በም የተመሰረተው ይኽ ግብረ ሠናይ ድርጅት በነፍስ አድን አስቸኳይ የምግብ እርዳታ፣ በትምህርት ፣ በጤና ፣ በንጹሕ የመጠጥ ውኃ ፣ በግብርና እና በተፈጥሮ ኃብት ጥበቃ ስድስት ሚሊዮን ኢትዮጵያውያንን ያለምንም ልዩነት ማገልገሉን እና ለዚህም እስከ ሰባት ቢሊዮን ብር ወጪ ማድረጉን የድርጅቱ አገር አቀፍ ተጠሪ አቶ ይልማ ታዬ ተናግረዋል። በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት የወደሙ መሠረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አመልክተዋል። 

የድርጅቱ ዋነኛ የገንዘብ ምንጭ የጀርመን ሕዝብ መሆኑንም ተገልጿል። ድርጅቱ በምሥራቅ ኢትዮጵያ በድርቅ የተጎዱትን፣ በሰሜን ኢትዮጵያ ደግሞ ጦርነት ችግር ለጋረጠባቸው ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረግና ለመልሶ ማቋቋም ከፍተኛ በጀት መድቦ እየተንቀሳቀሰ መሆኑንም ተናግሯል። የድርጅቱ መሥራች ዶ/ር ካርል ሃይንዝ በም ኢትዮጵያ ውስጥ ላበረከቱት ከፍተኛ የሰብዓዊ ድጋፍ ተግባር አዲስ አበባ ውስጥ ሐውልታቸው ካርል ተብሎ በተሰየመው አደባባይ ላይ ቆሞላቸዋል።

ሰሎሞን ሙጬ 

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ