1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጅ ዕድል እና ፈተና

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 16 2015

ለተለያዩ ተግባራት የጫኗቸው መተግበሪያዎች በእርሰዎ እንቅስቃሴ ላይ ተመስርተው ፍላጎተዎን በመገመት የተለያዩ ምርቶችን እንዲገዙ ማስታወቂያዎችን ሊያዥጎደጉድለዎት ይችላል።ዩቱብም በሚከታተሏቸው ይዘቶች ላይ ተመስርቶ ፍላጎተዎን በመገመት ተያያዥነት ያላቸውን ይዘቶች እንዲመለከቱ ሊጋብዘዎ ይችላል።እነዚህ ሁሉ የሰው ሰራሽ አስተውሎ ውጤቶች ናቸው።

https://p.dw.com/p/4Mwaa
Intelligente Technologie, künstliche Intelligenz und Datensicherheit
ምስል imago images/Imaginechina-Tuchong

ቴክኖሎጅው የራሱ የሆኑ ጥቅም እና ጉዳቶች አሉት


ሰው ሰራሽ አስተውሎት በአሁኑ ጊዜ በተለያዩ ዘርፎች ምርታማነትን ለመጨመር እንዲሁም አምራች እና አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ለማስተሳሰር ቁልፍ ቴክኖሎጂ ነው።ያም ሆኖ ቴክኖሎጅው በምዕራባዊያን እና በሩቅ መስራቅ ሀገራት  በሰፊው እየተተገበረ ሲሆን አፍሪካ ግን ገና በሙከራ ላይ ነች።ለመሆኑ የቴክኖሎጅው ጥቅሞቹ እና ጉዳቶች ምን ምን ናቸው? ኢትዮጵያ በዘርፉ ያላት ተሳትፎስ ምን ይመስላል?  በዘርፉ ያሉ ፈተናዎች እና እድሎችስ ?የዛሬው የሳይንስ እና ቴክኖሎጅ ዝግጅት የሚያተኩርባቸው ጉዳዮች ናቸው ።
ሰው ሰራሽ አስተውሎት/artificial intelligence/  በአሁኑ ወቅት በትምህርት፣ በኢንዱስትሪ፣ በጤና፣በደህንነት እና በግብርና ዘርፎች ምርታማነትን እና ቅልጥፍናን ለመጨመር ቁልፍ ቴክኖሎጂ ሆኖ እያገለገለ ነው።በኢኮኖሚው ረገድም መረጃዎች እንደሚያሳዩት የዚህ ቴክኖሎጅ ድርሻ በዓለም ገበያ  350 ቢሊዮን ዶላር በላይ ደርሷል። አፍሪቃም እያደገ የመጣውን ዓለም አቀፍ  የሰው ሰራሽ አስተውሎት ገበያ 10% ብቻ መያዝ ከቻለች በጎርጎሪያኑ 2030 አሁን ካለው የአህጉሪቱ አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት 50 በመቶ ሊጨምር ወይም በ1.5 ትሪሊዮን ዶላር ሊደርስ ይችላል። ለመሆኑ ሰው ሰራሽ አስተዉሎት ማለት ምን ማለት ነው። በሲውዘርላንድ ሀገር የሶፍትዌር መሀንዲስ የሆኑት አቶ ዳዊት ዓለሙ።«አረቲፊሻለል ኢነቴሌጀንስ ወይም የሰው ሰራሽ አስተውሎት ኮመፒዩተሮችን ልክ እንደ ሰው እንዲያመዛዝን' ነገሮችን እንዲገነዘብ  እንዲማር በዓለማችን ያሉ ችግሮችን እንዲቀርፍ የምናደርግበት የጥናት ዘርፍ ነው።» ብለዋል።
ይህንን በመገንዘብ  ይመስላል በአፍሪቃ እንደ ኬንያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ግብፅ እና ናይጄሪያን የመሳሰሉ ሀገራት በዚህ የቴክኖሎጅ ዘርፍ የተሻለ አፈፃጸም አላቸው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢትዮጵያም ዘርፉን ለማሳደግ በተለያዩ መስኮች የተጀመሩ ስራዎች መኖራቸውን ይገልፃሉ። በኢትዮጵያ የርቲፊሻል ኢንቴለጀንስ ኢንስቲቲዩት የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር  አቶ ተስፋዬ ዘውዴ ።

Ato Tesfaye Zewedie
በኢትዮጵያ የአርቲፊሻል ኢንቴለጀንስ ኢንስቲቲዩት የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር  አቶ ተስፋዬ ዘውዴምስል Ato Tesfaye Zewedie

የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጅ በምዕራባዊያን እና በሩቅ መስራቅ ሀገራት  በሰፊው እየተተገበረ ሲሆን ፤ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአፍሪካ የሚገኙ ኩባንያዎች ቴክኖሎጂውን  ድህነትን፣ ስራ እጥነትን እና ሌሎች በርካታ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተግዳሮቶችን ለመዋጋት እየተጠቀሙበት ነው።
ይህ ቴክኖሎጅ በሁሉም ዘርፎች ሰፊ ተግባራት ያሉት በመሆኑም  ከቅንጦት ይልቅ ለህብረተሰብ ያለው አስፈላጊነት ግንዛቤ እያገኘ ነው። ቴክኖሎጅው በተለይ በአፍሪካ  ከባድ በሽታዎችን ለማስወገድ፣ የጤና እንክብካቤን እና ትምህርትን ለማሻሻል፣ ድህነትን ለመቀነስ እና በአህጉሪቱ ለሚታየው የምግብ እጥረት የላቁ መፍትሄዎችን ለማምጣት ይረዳል።

Data Background - 3d Illustration
ምስል Alexander Limbach/Zoonar/picture alliance

ከአዳዲስ የፈጠራ ስራዎች አንፃርም የማህበራዊ ግንኙነቶችን፣ የትምህርት፣ የግብርና፣ የጤና እንክብካቤ እና የህዝብ አገልግሎት ጥራትን ለማሻሻል የሚያግዙ በሰው ሰራሽ አስተውሎት ላይ የተመሰረቱ መተግበሪያዎች ፈጠራም ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዲጨምር አድርጓል። ያም ሆኖ  በአፍሪቃም ሆነ በኢትዮጵያ የመረጃ ግብዓት ችግር ፣ የበይነመረብ ግንኙነት ችግር፣ በዘርፉ ሰለጠነ የሰው ሀይል እጥረት እናቴክኖሎጅው በስርዓት የሚመራበት ህጎች እና ደንቦች አለመኖር የዘርፉ ተግዳሮቶቹ ናቸው።እንደ አቶ ተስፋዬ በኢትዮጵያም ችግሩ ተመሳሳይ ነው። 
ባለሙያዎቹ እንደሚሉት ሰውሰራሽ አስተውሎት ማሽን ወይም ኮምፒዩተር የሰው ልጆችን ተክቶ ማመዛዘን፣ መማር፣ ማቀድ እና ፈጠራዎችን ማከናወን እንዲችል የሚያደርግ  ነው።በዚህ ሁኔታ ማሽኖቹ አካባቢያቸውን እንዲገነዘቡ፣ የተገነዘቡትን እንዲተነትኑ ፤ ችግሮችን እንዲፈቱ እና አንድ የተወሰነ ግብ እንዲደርሱ ለማድረግ ያስችላቸዋል።

Humanoider Roboter | Künstliche Intelligenz in der Justiz
ምስል Alexander Limbach/Zoonar/picture alliance

ይህም በተለይ የሰዎችን ንክኪ በመቀነስ ለምርት መጨመር፣ የጊዜ አጠቃቀምን ለማሻሻል፣ ብልሹ አሰራሮችን ለማስወገድ እና ውስብስብ ስራዎችን ያለ ከፍተኛ ወጪ ለመፈፀም ያስችላል።ከጊዜ አንፃርም ያለማቋረጥ እና ያለ ምንም እረፍት ይሰራል።በሌላ በኩል ማሽን ስሜት አልቫ በመሆኑ እና ባህልን እና ሥነምግባር የሚረዳ ባለመሆኑ የተሳሳተ ድምዳሜ ላይ ሊደርስ እና ሰዎችን በተሳሳሳተ መንገድ የመፈረጅ ሁኔታ ሊያጋጥም እንደሚችልም አቶ ዳዊት ገልፀዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ሰው የሰራሽ አስተውሎት ስልተ ቀመሮች/Algorithm/ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ አድሏዊ በሆነ  ውሂብ/data/ ላይ ከተገባ አድሏዊ ውጤትን  በማምጣት  መገለል እና አድልኦ የሚያስከትሉ አሉታዊ ገጽታዎችም አሉት። ስለዚህ ጥቅሞቹን እና ጉዳቶችን ማመዛዘን ያስፈልገዋል።ከዚህ አንፃር  የሳቸው መስሪያ ቤት የኢትዮጵያ ኢንተሌጀንስ ኢንስቲቲዩት ሃላፊነት በተሞላበት ሁኔታ እየሰራ መሆኑን አቶ ተስፋዬ ገልፀዋል።

Logo Ato Tesfaye Zewedie
የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት አርማ ምስል Ato Tesfaye Zewedie

ይህ ቴክኖሎጅ በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያችን እና ህይወታችንም ሰፊ ድርሻ እየያዘ መጥቷል።ለምሳሌ በፌስቡክ እና ቲውተርን በመሳሰሉ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የተጠቃሚዎቹን የግል መረጃዎች አብላልቶ የተጠቃሚዎችን ማንነትና ፍላጎት በመረዳት  የተለያዩ ሃሳቦችን ለተጠቃሚው ሊያቀርብ ይችላል። አማዞንን ከመሳሰሉ ገበያዎች እቃ ሲገዙም ድርጅቱ  ሌሎች ምርቶችን የሚጠቁምበት ሂደትም አለ። 
ለተለያዩ ተግባራት የጫኗቸው መተግበሪያዎች በእርሰዎ እንቅስቃሴ ላይ ተመስርተው ፍላጎተዎን በመገመት የተለያዩ ምርቶችን እንዲገዙ ማስታወቂያዎችን ሊያዥጎደጉድለዎት ይችላል።ዩቱብም በሚከታተሏቸው ይዘቶች ላይ ተመስርቶ ፍላጎተዎን በመገመት ተያያዥነት ያላቸውን ይዘቶች እንዲመለከቱ ሊጋብዘዎ ይችላል።እነዚህ ሁሉ በዘርፉ የሚካተቱ ናቸው። ምክንያቱም ይህ የሚሆነው የተጠቃሚውን መረጃ በመሰብሰብ እና በመተንተን በሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጅ አማካኝነት ነው።ይህም አንዳንዴ በተጠቃሚው ነፃነት የማጣት ስሜትን ሊያሳድር ይችላል። የሶፍትዌር መሀንዲሱ  አቶ ዳዊት ዓለሙ ደግሞ ይህ አካሄድ የሰዎችን የበለጠ የማወቅ እና የመሻሻል ዕድልን እንደሚገድብ ይገልፃሉ።

AfroRead- Bizuneh Birhan
አቶ ዳዊት ዓለሙ የሶፍትዌር መሀነዲሰ እና የአፍሮሪድ መተግበሪያ አበልጻጊዎች አንዱ ምስል Privat

በሌላ በኩል ቴክኖሎጅው በምርት እና አገልግሎት ዘርፍ  ያሉ የስራ ቦታዎችን በማሽን በመተካት ሰዎችን  ሥራ አጥ ያደርጋል የሚል ስጋት ያሳድራል። በተለይ  የሰው ሀይል ሀብት በሆነበት እንደ ኢትዮጵያ ላሉ አዳጊ ሀገራት ችግሩ ቀላል አይደለም። አቶ ተስፋዬ ግን ምንም ቢሆን ማሽን የሰውን የማሰብ ችሎታ ሊተካ አይችልም እና የሚያሳስብ አይደለም ይላሉ።
በአጠቃላይ የሰው ሰራሽ አስተውሎት እንደማንኛውም ቴክኖሎጅ የራሱ የሆኑ ደካማ ጎኖች ቢኖሩትም በሁሉም ኢንዱስትሪዎች  የሰው ልጅን የወደፊት ሁኔታ የሚቀርፅ ቴክኖሎጅ ነው። በመሆኑም  ባለሙያዎች እንደሚሉት ማህበረሰብን የቴክኖሎጅው ተጠቃሚ ለማድረግ ጥሩ የፖሊሲ መመሪያ ፣ ህጎች እና የሥነ-ምግባር ደንቦች የሚያስፈልገው ነው። ይህም የተጠቃሚዎችን ፈቃድ ለማግኘት ሰብአዊ መብቶችን ለማክበር ፣ የግል መረጃን ለመጠበቅ እና አድልዎን ለማስቀረት  ያግዛል።ከዚህ በተጨማሪ የአካባቢውን ቋንቋ እና ባህል የሚያውቅ  የሰለጠነ የሰው ሀይል ወሳኝ መሆኑን አቶ ዳዊት ዓለሙ ገልፀዋል።

ሙሉ ዝገጀቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።

ፀሀይ ጫኔ
ማንተጋፍቶት ስለሺ