1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሰኔ 29 ቀን፣ 2012 ዓ.ም ስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ሰኔ 29 2012

የጀርመኑ ኃያል ቡድን ባየር ሙይንሽን ኹለተኛ ዋንጫውን ትናንት አሸንፎ ወስዷል። ዘንድሮ ቡድኑን በዋና አሰልጣኝነት የተረከቡት ሐንሲ ፍሊክ ከረፍት መልስ ዐይናቸውን የሚያሳርፉት ሦስተኛው እና ወሳኙ የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ ላይ ነው።

https://p.dw.com/p/3eru5
DFB Pokal Finale I Bayer Leverkusen I Bayern
ምስል Getty Images/AFP/A. Hilse

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

የጀርመኑ ኃያል ቡድን ባየር ሙይንሽን ኹለተኛ ዋንጫውን ትናንት አሸንፎ ወስዷል። ዘንድሮ ቡድኑን በዋና አሰልጣኝነት የተረከቡት ሐንሲ ፍሊክ ከረፍት መልስ ዐይናቸውን የሚያሳርፉት ሦስተኛው እና ወሳኙ የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ ላይ ነው። የጀርመን ቡንደስሊጋ ባየር ሙይንሽንን ለዋንጫ አሸናፊነት ቢያበቃም ሙሉ ለሙሉ የሚጠናቀቀው ዛሬ ማታ በሚደረገው የወራጅ እና አዳጊ ቡድኖች የመጨረሻ ግጥሚያ ነው። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ማንቸስተር ሲቲ ትናንት በሳውዝሐምፕተን ሽንፈት ገጥሞታል። ሲቲ በዘንድሮ ውድድር ለዘጠነኛ ጊዜ ሲሸነፍ ነው። አሰልጣኝ ፔፕ ጓርዲዮላ የትናንቱ ሽንፈት ምክንያት ሊገባቸው እንዳልቻለ ተናግረዋል።

ቡንደስሊጋ

በጀርመን ቡንደስሊጋ 34ኛው ዙር ጨዋታ ተጠናቆ ባየር ሙይንሽን የዋንጫ ባለቤት ቢኾንም፤ የቡንደስሊጋው የመጨረሻ ግጥሚያ ዛሬ ማታ ይከናወናል። ዛሬ ማታ የሚደረገው ግጥሚያ ከቡንደስሊጋው ጠርዝ ላይ በሚገኘው ቬርደር ብሬመን እና ከኹለተኛ ዲቪዚዮን በሦስተኛነት ባጠናቀቀው ሐይደንሃይም መካከል ነው።

የቡንደስሊጋውን እና የጀርመን እግር ኳስ (DFB) ዋንጫ ያሸነፈው ባየር ሙይንሽን ቡድን ተጨዋቾች
የቡንደስሊጋውን እና የጀርመን እግር ኳስ (DFB) ዋንጫ ያሸነፈው ባየር ሙይንሽን ቡድን ተጨዋቾችምስል picture-alliance/dpa/A. Hassenstein

ባለፈው ሐሙስ ሐይደንሃይም ወደ ቡንደስሊጋው ለማለፍ ቬርደር ብሬመን ወደ ኹለተኛ ዲቪዚዮን ላለመውረድ ባደረጉት የመጀመሪያ ዙር ግጥሚያ ያለምንም ግብ ነበር የተለያዩት። ያም ማለት ዛሬ ማታ በሚደረገው የመጨረሻው የመልስ ግጥሚያ ኹለቱም ቡድኖች የቡንደስሊጋ ተሳታፊ ለመኾን እኩል ዕድል ይዘው ነው ወደ ሜዳ የሚገቡት።

17ኛ ደረጃ ይዞ ከቡንደስሊጋው ሊሰናበት ጫፍ ደርሶ የነበረው ቬርደር ብሬመን በቡንደስሊጋው የመጨረሻ ዙር ግጥሚያ ባልተጠበቀ ኹኔታ ኮሎኝን 6 ለ1 አንኮታኩቶ ነው በቀጥታ ከመውረድ የተረፈው። በወቅቱ በቡንደስሊጋው የመቆየት ዕድል የነበረው ፎርቱና ዱይስልዶርፍ በዑኒዮን ቤርሊን የ3 ለ0 ሽንፈት ስለገጠመው የመጨረሻ 18ኛ ደረጃ ከያዘው ፓዴርቦርን ጋር በቀጥታ ወደ ኹለተኛ ዲቪዚዮን ተሰናብቷል።

ቬርደር ብሬመን በመጨረሻ ግጥሚያው ኮሎኝን እንዲያ በሰፊ የግብ ልዩነት በማሸነፉ ከታችኛው ዲቪዚዮን የሚመጣው ሐይደንሃይምንም በቀላሉ ይረታል ተብሎ ተጠብቆ ነበር። ኾኖም በሐሙሱ ግጥሚያ ኹለቱ ቡድኖች ጨዋታውን ያጠናቀቊት ያለምንም ግብ 0 ለ0 ነበር። ዛሬ ማታ በሚደረገው ወሳኝ ግጥሚያ አሸናፊ የኾነው ቡድን በቀጣዩ የውድድር ዘመን በቡንደስሊጋው ውስጥ ከሚወዳደሩ 18 ቡድኖች መካከል አንዱ ይኾናል ማለት ነው።ቢሌፌልድ እና ሽቱትጋርት አንደኛ እና ኹለተኛ ኾነው ኹለተኛ ዲቪዚዮን ውስጥ በማጠናቀቃቸው በቀጥታ ወደ ቡንደስሊጋው በቀጥታ ማለፍ ችለዋል።

ኹለተኛ ዲቪዚዮን

በኹለተኛ ዲቪዚዮን 17ኛ እና 18ኛ ኾነው ያጠናቀቊት ቪስባደን እና ድሬስደን ወደ ሦስተኛው ዲቪዚዮን አሽቆልቊለዋል። በእነሱ ምትክ ኹለተኛ እና ሦስተኛ ኾነው የጨረሱት ቩይርስቡርግ እና ብራውንሽቫይግ  ወደ ኹለተኛ ዲቪዚዮን አልፈዋል።

በጀርመን እግር ኳስ ደንብ መሠረት ኹለተኛ ዲቪዚዮን ውስጥ አንደኛ እና ኹለተኛ ኾነው ያጠናቀቊ ቡድኖች በቀጥታ ወደ ቡንደስሊጋው ያልፋሉ። ሦስተኛ ኾኖ ያጠናቀቀው ደግሞ ከቡንደስሊጋ ዝቅተኛ ቡድን ጋር በደርሶ መልስ ተጋጥሞ ካለፈ ቡንደስሊጋውን ይቀላቀላል።

በሦስተኛ ዲቪዚዮን ተጋጣሚ የነበረው ኬሚንትስ ቡድን
በሦስተኛ ዲቪዚዮን ተጋጣሚ የነበረው ኬሚንትስ ቡድንምስል Imago Images/foto2press/S. Leifer

ለወትሮው ውድድሩ ከሦስተኛ ዲቪዚዮን ሦስተኛ ኾኖ ባጠናቀቀው እና ከኹለተኛ ዲቪዚዮን 16ኛ ደረጃ ላይ በሚገኘው ዝቅተኛ ቡድን መካከል ነበር። ለምን ታዲያ ዘንድሮ ከሦስተኛ ዲቪዚዮን አራተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ኢንግሎሽታድት ቡድን ተወዳዳሪ ኾነ? በሦስተኛ ዲቪዚዮን አንደኛ ኾኖ ያጠናቀቀው ቡድንስ ለምን ባለበት እንዲቆይ ተደረገ?

በጀርመን እግር ኳስ ሕግ መሠረት በአንደኛ ዲቪዚዮን ማለትም ቡንደስሊጋ ውስጥ የሚወዳደር ቡድን ሌላ ኹለተኛ ቡድን ካለው በኹለተኛ ዲቪዚዮን መጫወት አይፈቀድለትም። ይኽም አንድ ቡድን በተለያዩ ተከታታይ ዲቪዚዮኖች ብቸኛ ኃያል እንዳይኾን ለማድረግ በሚል የወጣ ሕግ ነው።

በዘንድሮ ውድድር የቡንደስሊጋውን ዋንጫ ያሸነፈው ባየር ሙይንሽን ኹለተኛ ቡድን ማለትም ባየር ሙይንሽን ኹለት የተባለው ቡድን በሦስተኛ ዲቪዚዮን አንደኛ ኾኖ ነው ያጠናቀቀው። በሕጉ መሠረትም ቡንደስሊጋ አንድ እና ኹለት ላይ ባየር ሙይንሽን ኹለት ቡድኖች እንዳይኖሩት ለመከላከል ባየር ሙይንሽን ኹለተኛ በአንደኛነት ቢያጠናቅቅም እዛው በሦስተኛ ዲቪዚዮን ለመወሰን ተገዷል። ለባየር ሙይንሽን ወጣት ቡድኖች አሸንፈው ባሉበት እንዲቀሩ ቢገደዱም አንድ ቡድን ብቻውን በየዲቪዚዮኑ ኃያል እንዳይኾን ለማድረግ ግን አስችሏል ሕጉ። በዚህም ለብቻው ለመግነን የሚንደረደር ቡድንን መቆጣጠር ተችሏል።

ከሦስተኛ ዲቪዚዮን አራተኛ ደረጃ የያዘው ኢንግሎሽታድት ከኑይርንበርግ ጋር ነገ ማታ የመጀመሪያ ዙር ግጥሚያውን ያከናውናል። የመልስ ጨዋታውን ደግሞ ቅዳሜ ዕለት አከናውኖ አሸናፊው የቀጣይ የውድድር ዘመን የኹለተኛ ዲቪዚዮን 18 ቡድኖች አንደኛው ተወካይ ይኾናል። ዘንድሮ ከሦስተኛ ዲቪዚዮን አራት ቡድኖች ወደታች አሽቆልቊለው ተሰናብተዋል። ከ17ኛ እስከ 20ኛ ደረጃ ይዘው ተሰናባች ቡድኖቹ፦ ኬሚንትስ፣ ሙይንስተር፣ ግሮሻስፓኽ እና ዬና ናቸው።

የጀርመን እግር ኳስ ዋንጫን (DFB)

የባየር ሙይንሽን ተጨዋቾች ለኹለት ዋንጫ ያበቋቸው አሰልጣኝ ሐንሲ ፍሊክን ከፍ አድርገው
የባየር ሙይንሽን ተጨዋቾች ለኹለት ዋንጫ ያበቋቸው አሰልጣኝ ሐንሲ ፍሊክን ከፍ አድርገውምስል Getty Images/A. Hassenstein

በዋናው ቡንደስሊጋ የዋንጫ ባለቤት የኾነው ባየር ሙይንሽን ቅዳሜ ዕለትም የጀርመን እግር ኳስ ዋንጫን (DFB) አሸንፎ ወስዷል። ቤርሊን ውስጥ በተከናወነው የፍጻሜ ግጥሚያ ባየር ሙይንሽን ተጋጣሚው ባየር ሌቨርኩሰንን 4 ለ2 ሲያሸንፍ ውጤቱ ይገባዋል የሚያስብል ነው።  ለባየር ሌቨርኩሰን ተጠብቆ የነበረው ካይ ሃቫርትስ መደበኛ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተጠናቅ  በተጨመረው 5ኛ ደቂቃ ላይ ለቡድኑ 2ኛዋን ግብ አስቆጥሯል። አንደኛዋን ግብ 63ኛ ደቂቃ ላይ ከመረብ ያሳረፍው ስቬን ቤንደር ነው። ከጨዋታው በኋላ በሰጠው አስተያየት ቡድኑ ደካማ እንደነበር ገልጧል።

«በመጀመሪያው አጋማሽ አቅመ ቢስ ነበርን። መኾን የነበረበትን ያኽል ጉጉ አልነበርንም። በጣም ፈዘን ነበር፤ የጨዋታው ስልትም አልመጠነንም። 90 ደቂቃ ሙሉ እንደዚያ ተጫውተህ፤ ኹለተኛው አጋማሽ ላይ ያገኘነውን ዕድል አልተጠቀምንበትም። ያገኘነውን ዕድል ብንጠቀም ጨዋታውን እንቀይረው ነበር። ሲጠቃለል፦ ባየርኖች ዛሬ በጣም ጠንካራ ነበሩ።»

ለባየር ሙይንሽን ተከላካዩ ዳቪድ አላባ በ16ኛ፣ ሠርጌ ግናብሬ በ24ኛ፤ እንዲሁም በ59 እና 89 ደቂቃዎች ላይ ግብ አዳኙ ሮቤርት ሌቫንዶቭስኪ አራት ግቦችን አስቆጥረዋል።

የባየር ሙይንሽን እና የጀርመን ብሔራዊ ቡድን ግብ ጠባቂ ማኑዌል ኖየር ኹለተኛ ዋንጫ ስላሸነፉበት ግጥሚያ የሚከተለውን አስተያየት ሰጥቷል።  

«ከእነዚህ በርካታ ግጥሚያዎች በኋላ ኹለት ዋንጫ በማሸነፋችን ደስታም እፎይታም ተሰምቶናል። ያ ለእኛ በጣም የተለየ ነው። በአቋማችን ኩራት ይሰማናል።»

ባየር ሙይንሽንን ዘንድሮ ከገባበት ችግር አውጥተው ለጣምራ ድል ያበቊት አሰልጣኝ ሐንሲ ፍሊክ በበኩላቸው ስለ ቡድናቸው ስኬት ቀጣዩን ብለዋል።

«በጣም ተደስቻለሁ። በቡድኔ አባላትም ኾነ በስልጠና ጓዶቼ ኩራት ተሰምቶኛል። እርስ በእርስ በደንብ የተቀናጀን ይመስለኛል። በስተመጨረሻ ስኬታማ ለመኾን አስፈላጊ የኾነው ጥሩ ስሜት ቡድናችን አለው፤ በዛ ላይ ደስ ብሎን ነው የተጫወትነው። ዛሬ መከወን የፈለግነው ቀጣዩ ርምጃችን ነበር።»

ለባየር ሙይንሽን ተከላካዩ ዳቪድ አላባ በ16ኛው ደቂቃ የመታትን ኳስ ግብ ጠባቂው ሉቃስ ሕራዴኪ ሊይዛት አልቻለም
ለባየር ሙይንሽን ተከላካዩ ዳቪድ አላባ በ16ኛው ደቂቃ የመታትን ኳስ ግብ ጠባቂው ሉቃስ ሕራዴኪ ሊይዛት አልቻለምምስል Getty Images/J. MacDougal

ባየር ሙይንሽን በቀጣይ ለሻምፒዮንስ ሊግ ሩብ ፍጻሜ የመልስ ጨዋታ ከእንግሊዙ ቸልሲ ጋር ይጋጠማል። በመጀመሪያው ዙር ጨዋታ ባየር ሙይንሽን 3 ለ0 ማሸነፉ ይታወሳል። የ55 ዓመቱ አሰልጣኝ ሐንሲ ፍሊክ፦ ለኹለት ሳምንት የበጋ ረፍት ወስደው ሲመለሱ ቡድናቸውን በሻምፒዮንስ ሊግ ውጤታማ ማድረግ «ቀጣዩ ግባቸው» መኾኑን ከወዲኹ ተናግረዋል።

ዘንድሮ በኮሮና ተሐዋሲ ስርጭት ምክንያት ከዚህ ቀደም የነበረው የደርሶ መልስ ግጥሚያ በሩብ እና ግማሽ ፍጻሜ የሻምፒዮንስ ሊግ ውድድር አይኖርም። ከዚያ ይልቅ ሩብ ፍጻሜ እና ግማሽ ፍጻሜ ግጥሚያዎች ደርሶ መልስ ሳይኾን በአንድ ግጥሚያ ጥሎ ማለፍ ይኾናል ማለት ነው። ውድድሮቹ ልክ የዛሬ ወር ይጀምራሉ። ሩብ ፍጻሜ፤ ግማሽ ፍጻሜ እና የዋንጫ ግጥሚያዎች ፖርቹጋል ሊዛቦን ከተማ ውስጥ እንደሚከናወኑ ተገልጧል።

በሻምፒዮንስ ሊግ ወደ ሩብ ፍጻሜ ማለፋቸውን ካረጋገጡ ቡድኖች ባሻገር አራት ግጥሚያዎች ይቀራሉ። ወደ ሩብ ፍጻሜ ለማለፍ ባየር ሙይንይሽን ከቸልሲ፤ ማንቸስተር ሲቲ ከሪያል ማድሪድ፤ ጁቬንቱስ ቱሪን  ከኦሎምፒያኮስ ሊዮን፤ እንዲሁም ባርሴሎና ከናፖሊ ጋር የመልስ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። እነዚህ ወደ ሩብ ፍጻሜ ለማለፍ የሚደረጉ ግጥሚያዎችም ፖርቹጋል ሊዛቦን ውስጥ ይከናወኑ ሌሎች ከተሞች ውስጥ ገና ውሳኔ አልተሰጠም። አሸናፊዎቹም ወደ ሩብ ፍጻሜ ማለፋቸውን ያረጋገጡ አራት ቡድኖች ማለትም ላይፕሲሽ፤  ቤርጋሞ፤  ፓሪስ ሴንጄርሜን እና አትሌቲኮ ማድሪድን ይቀላቀላሉ። የሻምፒዮንስ ሊግ የፍጻሜ ግጥሚያ ለነሐሴ 17 ቀጠሮ ተይዞለታል።

የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ዋንጫን ዘንድሮ ከ30 ዓመታት በኋላ የወሰደው ሊቨርፑልን ደጋፊዎች ፈንጠዚያ
የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ዋንጫን ዘንድሮ ከ30 ዓመታት በኋላ የወሰደው ሊቨርፑልን ደጋፊዎች ፈንጠዚያምስል picture-alliance/Offside/A. Devlin

ፕሬሚ ሊግ

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ግጥሚያ ዋንጫውን አስቀድሞ የወሰደው ሊቨርፑልን ባለፈው ግጥሚያ 4 ለ0 ያሸነፈው ማንቸስተር ሲቲ በሳውዝሐምፕተን 1 ለ0 ተሸንፏል። ሊቨርፑል በአንፃሩ አንፊልድ ስታዲየሙ ውስጥ አስቶን ቪላን ትናንት 2 ለ0 አሸንፏል።  ዛሬ ማታ ቶትንሀም ሆትስፐር ከኤቨርተን ጋር ይጋጠማል።

ስታምፎርድ ብሪጅ ላይ ቸልሲ ከትናንት ወዲያ ድል ቀንቶት ዋትፎርድን 3 ለ0 አሸንፏል። አርሰናል ዎልቭስን 2 ለ0 ድል አድርጓል። በእለቱ ማንቸስተር ዩናይትድ ቦርመስን በሰፊ ልዩነት 5 ለ2 አሸንፏል። ላይስተር ሲቲም በሰፋ ልዩነት ክሪስታል ፓላስን  3 ለ 0 ድል አድርጓል። አስቶን ቪላ፣ በርመስ እና ኖርዊች ከ18ኛ እስከ 20ኛ ደረጃ ወራጅ ቃጣና ውስጥ ይገኛሉ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ