1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሰብዓዊ ቀውስ በቻድ ሀይቅ አካባቢ

ቅዳሜ፣ ጳጉሜን 3 2010

በአፍሪቃ በቻድ ሀይቅ አካባቢ ዓለም አቀፉ ማህበረ ሰብ ያላስተዋለው ግዙፍ አሳሳቢ የሰብዓዊ ቀውስ ተከስቷል። በቻድ ሀይቅ አካባቢ የናይጀሪያ ዓማፅያን ቡድን ቦኮ ሀራም ባስፋፋው ሽብርተኝነት ሰበብ  ያካባቢው ሕዝብ ከመኖሪያው ተፈናቅሏል ወይም ለስደት ተዳርጓል።

https://p.dw.com/p/34VDU
Tschadsee-Konferenz im Auswärtigen Amt
ምስል picture alliance/dpa/B. von Jutrczenka

«ባካባቢው አስቸኳይ ርዳታ የሚያስፈልገው 10 ሚልዮን ሰው አለ።»

የሽብርተኝነት መስፋፋት ብቻ ግን አይደለም የዚህ አካባቢ ሕዝብን እንዲሰደድ ያደረገው። ካለፈው ምዕተ ዓመት ወዲህ በተከሰተው የአየር ንብረት ለውጥ የቻድ ሀይቅ የውሀ መጠን በጉልህ ቀንሷል። በሰበቡም የምግብ እጥረት ካጋጠማቸው በሀይቁ አካባቢ ካሉት ምዕራብ አፍሪቃውያት ሀገራት፣ ቻድ፣  ካሜሩን፣ ኒጀር እና ናይጀሪያ ሕዝቦች መካከል ብዙዎች በሀገራቸው ውስጥ ተፈናቅለዋል፣ ወደ ጎረቤት ሀገራትም ሸሽተዋል። የዚሁ የሰብዓዊ ቀውስ አሳሳቢነትን ለማጉላት እና  የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ግንዛቤ ከፍ ለማድረግ በሳምንቱ መጀመሪያ በበርሊን  ላካባቢው ርዳታ ማሰባሰቢያ የሁለት ቀን ጉባዔ ተካሂዷል።  ጀርመን፣ ኖርዌይ፣ ናይጀሪያ እና የተመድ በጋራ ያዘጋጁትን እና ወደ 50 የሚጠጉ የልዑካን ቡድኖች የተሳተፉበትን ጉባዔ የከፈቱት  የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሀይኮ ማስ እንደተናገሩት፣ ያካባቢው ሀገራት  በጋራ ባደረጉት ጥረት ቦኮ ሀራም ከተቆጣጠረው ቦታ ብዙውን ማስለቀቅ በመቻላቸው ሁኔታዎች በመጠኑ መሻሻል አሳይተዋል። ከአንድ ዓመት ተኩል በፊት በኦስሎ ኖርዌይ በተካሄደው ለቻድ ሀይቅ አካባቢ ሀገራት ርዳታ ማሰባሰቢያ ጉባዔ ወቅት ከ672 ሚልዮን ዶላር በላይ ሰብዓዊ ርዳታ ነበር የተገኘው።  ይህ ለጋሾች ያቀረቡት ርዳታም በቻድ ሀይቅ አካባቢ ረሀብ እንዳይከሰት በማከላከሉ እና በቀውሱ ለ የተጎዱትን በመርዳቱ ረገድ ከፍተኛ ድርሻ እንዳበረከተ  ተገልጿል፣ ይሁንና፣ አካባቢው እንደገና ወደ ሌላ አሳሳቢ ችግር እንዳይወድቅ አሁንም ብዙ ሊደረግ እንደሚገባ ሀይኮ ማስ አሳስበዋል።
« የቻድ ሀይቅ አካባቢ የሽብርተኝነት፣ የወንጀል እና የሰው አሸጋጋሪዎች መናኸሪያ እንዳይሆን፣ በዚህ አንጻር አካባቢው በሰሜን እና ከሰሀራ በስተደቡብ ባሉ አፍሪቃውያት ሀገራት መካከል አነቃቂ ኤኮኖሚያዊ ኃይል እንዲሆን  በጋራ እንደምንሰራ ግልጹን መልዕክት ማስተላለፍ በጣም አስፈላጊ ነው።»
ጀርመን ለቻድ አካባቢ ሀገራት እስከ ጎርጎሪዮሳዊው 2020 ዓም ድረስ  የ100 ሚልዮን ዩሮ ተጨማሪ፣አስቸኳይ ርዳታ ለመስጠት ቃል ገብታለች። በ2018 እና 2019 ዓምም 40 ሚልዮን ዩሮ ርዳታ እንደምትሰጥ  ቀደም ሲል ያስታወቀችው የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሀይኮ ማስ ባካባቢው ፖለቲካዊ መረጋጋት ማስገኘት ትልቅ ትርጉም መያዙን በማስታወቅ ትብብሩ እንዲጠናከር ጠይቀዋል።
« ይህን የምናደርገው ፀጥታ በጋራ  ስንሰራ ብቻ እንደሚረጋገጥ ስለምናውቅ ነው። እንደ አውሮጳውያንም አሁን በቻድ ሀይቅ አካባቢ የተጀመረው ትብብር የኛ ሙሉ ድጋፍ እንደሚያስፈልገው እርግጠኞች ስለሆን ነው። »
ከሰሜናዊ ናይጀሪያ የሚንቀሳቀሰው አክራሪው የሽብርተኞች ቡድን ቦኮ ሀራም በጎረቤት ሀገራት የሚያካሂደው ጥቃት ባካባቢው ያስከተለው ግዙፍ መፈናቀል እና በወቅቱ አካባቢውን ያሰጋው የረሀብ አደጋ አሳሳቢ ችግር መደቀኑን የተመድ የሰብዓዊ ርዳታ አስተባባሪ መስሪያ ቤት ኃላፊ ማርክ ሎውኮክ ገልጸዋል።
« አሁንም በአካባቢው ትልቅ የሰብዓዊ ቀውስ ይታያል። ምንም እንኳን የሰዉን ችግር ለመቀነስ ባደረግነው ጥረት አንዳንድ መሻሻል ብናስገኝም፣ ቀውሱ በሰዎች ላይ እያደረሰ ያለው ስቃይ ገና አልተወገደም። በአራቱ ሀገራት ፣ ማለትም፣ በቻድ፣ ኒጀር፣ ካሜሩን እና ናይጀሪያ አሁንም ለዕለታዊ ኑሯቸው ርዳታ የሚያስፈልጋቸው 10 ሚልዮን ሰዎች አሉ። አንዳንዶቹ ርዳታ ጠባቂዎች ያሉበት በቀላሉ የማይደረስበት ቦታ መድረሱ ግን ቦኮ ሀራም  እና ሌሎች ሰርጎ ገቦች በሚጥሉት ጥቃት የተነሳ እጅግ አዳጋች እንደሆነ ይገኛል። በመሆኑም፣ ትኩረታችንን ልንደርስላቸው ባልቻልናቸው ርዳታ ጠባቂዎች ላይ ማሳረፍ መቀጠል አለብን። »
ከቦኮ ሀራም ጋር በቀጠለው ውዝግብ የተፈናቀለውን 2,4 ሚልዮን ያካባቢው ነዋሪ ለመርዳት የሚደረገው ጥረት እንዲሳካ ቻድ የበኩሏን እንደምታደርግ በበርሊን ጉባዔየተሳተፉት የቻድ የኤኮኖሚ እና ልማት እቅድ ሚንስትር ሂሴይን ታሂር ሱጉሚ ገልጸዋል።
« የቻድ መንግሥት ደህና ሁኔታ ለመፍጠር፣  ለሲቭሉ ደህንነት ከለላ ለመስጠት እና የተለያዩ የርዳታ እና የመልሶ ማቋቋም መርሀ ግብሮች መጀመር ለማስቻል  መስራቱን ይቀጥላል። »
ከአንድ ዓመት ተኩል በፊት ለቻድ ሀይቅ አካባቢ ሀገራት በኦስሎ፣ ኖርዌይ እንደሚሰጥ ቃል ከተገባው 672 ሚልዮን ዶላር ርዳታ መካከል 90% ቢገኝም፣  የዓለሙ መንግሥታት ድርጅት አሁንም  ያጋጠመው የገንዘብ እጥረት ፣ ርዳታ ለሚያስፈልገው ሰው ሁሉ ርዳታ ማቅረብ እንዳልቻለ የተመ የልማት መርሀግብር መስሪያ ቤት፣ በምህፃሩ ዩኤንዲፒ ኃላፊ አኺም ሽታይነር አስታውቀዋል።  
« ይህ፣ በተግባር ሲተረጎም፣ የምንሰጠውን ምግብ መጠንን መቀነስ፣ በመጠለያ ጣቢያዎች የተከፈቱትን  ትምህርት ቤቶች መዝጋት፣ ባጭሩ፣ መረዳት ያለባቸውን ሰዎች መርዳት አለመቻል ማለት ነው። ካልተጠነቀቅን እና ለቀጣዩ ዓመታዊው ዑደት የሚያስፈልገው ርዳታ ካልቀረበልን፣ ርዳታችንን ማቋረጥ እና በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙትን ተረጂዎችም ፣  እጣ ፈንታቸውን ራሳቸው እንዲወጡ ፣ብቻቸውን መተው ማለት ነው። »
የተመድ ለቻድ ሀይቅ አካባቢ ሀገራት 1,5 ቢልዮን ዶላር ርዳታ እንዲቀርብለት ጥሪ ቢያቀርብም፣ ከዚሁ እስካሁን ወደ ግማሽ ያህሉን ብቻ ነው ያገኘው። 
ያካባቢው መንግሥታት ተወካዮች ቀውሱ በቀላሉ የማይገመት ማህበራዊ እና ኤኮኖሚዊ መዘዝ ማስከተሉን ገልጸዋል። የካሜሩን ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ፌሊክስ ምባዩ እንዳሉት፣ ቀውሱ ግብርናን እና ቱሪዝምን   የመሳሰሉ ኤኮኖሚ ዘርፎችን አብዝቶ ጎድቷል። ከሰሜን ምሥራቅ ካሜሩን በቦኮ ሀራም ሽብር የተፈናቀሉ ወደ 230,000 የሚሆኑ ሰዎች እስካሁን ወዳካባቢያቸው መመለስ አለመቻላቸውን በማመልከት፣ የቀውሱን ሰለባዎች ለመርዳት ተጨማሪ ድጋፍ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል። ያካባቢው ሁኔታ ይበልጡን እየከፋ እንዳይሄድየናይጀሪያ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ኸዲጃ ቡካር አባ ኢብራሂም ዘላቂ መፍትሔ እንዲገኝን ጠይቀዋል።  

Logo UNDP United Nations Development Programme
ምስል APGraphics
Boko Haram
ምስል Java
Karte Tschadsee EN
ምስል DW

« የስራ እድል በመፍጠር፣ የሙያ ስልጠና በመስጠት እና መሰል እንቅስቃሴዎችን በማጠናከር  የተፈናቃዮችን አቅም መገንባት እና መልሶ ማቋቋም የቻድ ሀይቅ አካባቢ ለገጠመው ተግዳሮት ዘላቂ መፍትሔ  ለማስገኘት ወሳኝ ርምጃዎች ናቸው። »

አርያም ተክሌ/ዳንየል ፔልስ

ተስፋለም ወልደየስ