1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሰቆጣ ከተማ ነዋሪዎችን የታደጉት የሃይማኖት አባት 

ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 20 2014

የሕወሓት ኃይሎች በሰቆጣ ከተማ በቆዩባቸው ከ2 ወራት በላይ ኅብረተሰቡ ለከፍተኛ ርሀብ ተጋልጦ ነበር። በዚህ ክፉ የርሀብ ጊዜ ሕይወት እንዳያጠፋ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደርና የምዕራብ ካናዳ ሊቀ ጳጳስ አቡነ በርናባስ ህዝብ በማስተባበር የምግብ እህልና ገንዘብ በማቅረብ የተቸገሩ ወገኖችን ታድገዋል።

https://p.dw.com/p/44xZd
Äthiopien Bishop Bernabas
ምስል Alemnew Mekonnen/DW

የሰቆጣ ከተማ ነዋሪዎችን ከረሀብ የታደጉት የሃይማኖት አባት

ሕወሓት በአማራ ክልል የዋግ ኽምራ ቤሔረሰብ አስተዳደር በሰቆጣ ከተማ በቆየበት ወቅት ኅብረተሰቡ በራብ እንዳይሞትና እንዳይቸገር የዋኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደርና የምዕራብ ካናዳ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ባርናባስ ገንዘብና ምግብ በማሰባሰብ ህዝቡን መታደጋቸውን ተናገሩ፣ አቡነ በርናባስ ሰዎችን በሰውነት ብቻ በመመዘን ያለልዩነት እርዳታ ያደርጉ አንደነበር የሰቆጣ ከተማ ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡ የህወሓት ኃይሎች በሰቆጣ ከተማ በቆየባቸው ከ2 ወራት በላይ ጊዜ ህብረተሰቡ ለከፍተኛ ርሀብ ተጋልጦ መቆየቱን የአካባቢው ነዋሪዎችና  ባለስልጣናት ይናገራሉ።

ይህ ክፉ የርሀብ ጊዜ ሕይወት እንዳያጠፋ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደርና የምዕራብ ካናዳ ሊቀ ጳጳስ አቡነ በርናባስ ከውጫና ከአገር ውስጥ ያለውን ህዝብ በማስተባበር የአምግብ እህልና ገንዘብ በማቅረብ የተቸገሩ ወገኖችን መታደግ መቻሉን ለዶይቼ ቬለ ገልፀዋል። በሁለተኛው ዙር የወረራ ወቅት ቡድኑ አመጣጡ ያስፈራ እንደነበር የተናገሩት አቡነ ባርናባስ ታጣቂዎቹ ክፉ ነገሮችን እንዳይፈፅሙ ከብሔረሰብ አስተዳደሩ አገረስብከት ጋር በመሆን ጥረት ይደረግ ነበር ብለዋል፡፡ በሰሜን ወሎ ወልዲያ ከተማም የክርስትናና የእስልምና አባቶች ያለ ልዩነት በመስራት ከ22ሺህ በላይ የሚሆነውን የከተማዋ ነዋሪ ብድርና እርዳታ በመስጠት በርካታ ህይወት መታደጋቸውን የወልዲያ ሰላም መስጊድ ኮሚቴ አባል ሀጂ ያሲን እንደሪስ ተናግረዋል፡፡ 

አለምነው መኮንን

ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ