1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሰሬብሬኒሳ ጭፍጨፋ አስትምሮ ይሆን?

ሰኞ፣ ሐምሌ 13 2012

«ነርሚን፣ነርሚን ሆይ አዚሕ ወደ ሰርቦቹና።ደሕና ነዉ።እኔም እዚሕ ነኝ።ከሰርቦቹ ጋር።» ልጅ መጣ እጁንም ሰጠ።ሁለቱም ተረሸኑ።በድምሩ ስምንት ሺሕ።ዘንድሮ ባለፈዉ ሳምንት 25ኛ ዓመታቸዉ።ሰረብሬኒሳ።አስተምራን ይሆን?

https://p.dw.com/p/3fc3o
Bosnien und Herzegowina - Gedenken an Srebrenica-Massaker
ምስል Reuters/D. Ruvic

የሰሬብሬኒሳ ጭፍጨፋ 25ኛ ዓመት ዝክር

ኢትዮጵያዉያን ለአራት ዓመት መሪዎቻቸዉ «የሽግግር» የምትለዋን ቅድመ-ቅፅል ግንቦት ላይ በሰጡት ድምፅ ፍቀዉ «በብሔር ላይ የተመሠረተ ቋሚ፣ ፌደራዊ መንግስት» በመዋቀሩ፣ዩጎዝላቪያን ወይም ሩዋንዳን ከመሆን የመዳናቸዉ ብስራት ከገዢዎቻቸዉ እየተንቆረቆረላቸዉ ነበር።ኃምሌ 11፤ 1995 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ።) ጄኔራል ራድኮ ሚላጂች የሚመሩት የቦስኒያ ሰርብና የሰርቢያ ጦር ለወራት የከበባትን ከተማ ተቆጣጠረ። ልጅ እንደ ብዙ የእድሜ አቻዎቹ ወደ ጫካ ሸሸ።አባት ግን ከሚስት፣ ሴት ልጆቻቸዉ ተነጥለዉ ለድል አድራጊዉ ጦር እጅ ሰጡ።የጄኔራሉን መልዕክት  እንደሰሙ ወደ ጫካ የሸሸ ልጃቸዉን ወደ ከተማ እንዲመለስ ተጣሩ።
«ነርሚን፣ነርሚን ሆይ አዚሕ ወደ ሰርቦቹና።ደሕና ነዉ።እኔም እዚሕ ነኝ።ከሰርቦቹ ጋር።» ልጅ መጣ እጁንም ሰጠ።ሁለቱም ተረሸኑ።በድምሩ ስምንት ሺሕ።ዘንድሮ ባለፈዉ ሳምንት 25ኛ ዓመታቸዉ።ሰረብሬኒሳ።አስተምራን ይሆን? ላፍታ አብረን እንጠይቅ።
የዘር፣ ብሔር ፣ ጎሳ፣ ኃይማኖት ልዩነትን የስልጣን ጥማት መርኪያቸዉ ለማድረግ ያለሙ የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ዘርን ከዘር ለይቶ ለማጥፋት ታሕሳስ 1991 አርባጉጉ፣ በአምስተኛ ወሩ በደኖ ላይ የጫሩት እሳት በትንሽ ግምት የ300 ሰዎችን ሕይወት፣ ግምቱ የማይታወቅ ሐብት ንብረት አዉድሟል።ለረጅም ዘመን «ተጋብተን ተዋልደን አብረን ኖረናል» የሚለዉ፣ በፖለቲካ ተንታኞች ቋንቋ «ዝም ያለዉ ብዙሐን» ዝም በማለቱ፣የፖለቲከኞቹ ወይም የዘረኞቹ የጥፋት ስብከት ካደረሰረሰዉ በላይ ጥፋት ሳያደርስ እሳቱ ላጭር ጊዜም ቢሆን ተዳፍኗል።ግን ዛሬም አልጠፋም።
አብዛኛዉ ኢትዮጲያዊ አስፈሪዉ እሳት መጥፋት መዳፈኑን በቅጡ ባለየበት በዚያ ዘመን የዩጎዝላቪያ ፌደሬሽን ሪፐብሊኮች በአብዛኛዉ ዘር፣ ጎሳና ኃይማኖት መሠረት ባደረገ ፖለቲካዊ ጠብ ምክንያት የየራሳቸዉን ነፃነት እያወጁ ነበር።የቦስኒያና ሔርሶ ጎቪና ሶሻሊስት ሪፐብሊክ ሕዝብም የካቲት ማብቂያ 1992 በሰጠዉ ድምፅ፣ ግዛቱ እንደ  አብዛኞቹ ሪፐብሊኮች ነፃ መንግስት መሆንዋን አፀደቀ።
ከቦስኒያ ሔርሶ ጎቪና ሕዝብ 41 ከመቶዉ ሙስሊም ቦስኒያክ፣ 31 ከመቶዉ የኦርቶዶክስ ክርስትናን የሚከተል ሰርብ፣ 17 ከመቶዉ ደግሞ የካቶሊክ ክርስቲያን ክሮአት ነዉ።ሙስሊሞቹና ካቶሊኮቹ ነፃነቱን በመደገፍ ድምፅ ሲሰጡ ግዛቲቱ ከጠንካራዋ ሰርቢያ ሪፐብሊክ መነጠልዋን የሚቃወሙት የሰርብ ኦርቶዶክሶችና የራስዋ የሰርቢያ ጦር ገና በሁለት እግሯ ያልቆመችዉን ቦስኒያ ሔርሶ ጎቪናን በተለይም ቦስኒያክ የሚባሉትን ሙስሊሞች ይወጉ ገቡ።1992።
የዘርና ኃይማኖት መልክና ባሕሪ የያዘዉ ጦርነት ከታጣቂዎች ዉጊያነት ባጭር ጊዜ ተለዉጦ  ሰዉ፣የሰዉነት ማሰቢያ፣ ክብር፣ማዕረጉን ጥሎ ጠንካራዉ ሰዉ ደካማ ብጤዉን በየቤቱ እያጎረ ያነድ፣ እጁን እየጠፈረ ይረሽን፣አስገድዶ ይደፍር ገባ።ዘግናኙ የሰረብሬንሳዉ ጭፍጨፋ ነበር።የክሮኤሺያዉ ፕሬዝደንት ዞራን ሚላኖቪች በቀደም እንዳሉት ያ የአረመኔዎች ምግብር ትዉስታ ዛሬም ድረስ ያምማል።
«በዘመናዊቱ አዉሮጳ ታሪክ፣ በተለይም በአንድነት በኖረዉ እና ባንድ መንግስት በሚተዳደረዉ የቦስኒያ ሔርዞጎቪና ሕዝብ ላይ እንዲያ እይነት ጭፈጨፋ መድረሱ ዛሬም ድረስ የሚያም፣ሰብአዊነታችንንም የሚፈታተን ነዉ።»
የዚያ ዘመኑን ምርጥ ጦር መሳሪያ፣ በተለይም ታንክ፤ መድፍ፤ ባዙቃና መትረየስ እስካፍንጫዉ የታጠቀዉ የሪፑብሊካ ስርፕስካ ጦር (VRS በሰርብ ምሕፃሩ) እና ስኮርፒዮ (ጊንጥ)  የተባለዉ የሰርቢያ ፈጥኖ ደራሽ ጦር በ1992 ሰሬብሬንስካ አካባቢ የሚኖሩ ከ3 ሺሕ በላይ ሙስሊሞችን ጨፍጭፈዋል።296 መንደሮችን አጋይተዉ 70 ሺዎችን አፈናቅለዉ ነበር።
ከየአካባቢዉ ያፈናቀለዉ የቦስኒያ ሙስሊም እየተግተለተለ ወደ ሰረብሬንሳ ሲተም የተባበሩት መንግስታት በተለይም የኔዘርላንድስ ጦር ጠመንጃዉን ታቅፎ  በቅርብ ርቀት ይመለከት ነበር።ሙስሊሞቹ ሰረብሬንሳን ሙጥኝ ያሉት የተባበሩት መንግስታት ጦር ያድነናል-አንድ፣ ዓለም አቀፉ ድርጅት ከተማይቱን ከዉጊያ «ጥብቅ ቀጠና» ብሎ በመሰየሙ-ሁለት ምክንያት ነበር።
የሰርቢያዉ ገዢ ስሎቮዳን ሜሎሶቪች ለታላቋ ሰርቢያ  ቅዠታቸዉ እዉንነት «ግፋ» ይላሉ። የቦስኒያ ሰርቦች መሪ ራዶቫን ካራዚች በሙያቸዉ የስነልቡና ሙሕር ናቸዉ።ዘር የማጥፋት ስነ-ልቡናዊ  እብደታቸዉን  አዋጅ ቁጥር 7 ባሉት መግለጫ በግልፅ አስታዉቀዉ ነበር።መጋቢት 1995።
«-----በቅጡ በታቀደና  በተጠና ወታደራዊ ዘመቻ የሰሬብሬንሳ ነዋሪዎች የመኖር ተስፋ ጨርሶ እንዳይኖራቸዉ የሚያደርግ ሁኔታ መፍጠር---»
ይላል።የአዋጁ አንድ አረፍተ ነገር።የሰርብ ፖለቲከኞችና የጦር መሪዎች ሙስሊሞችን በየመንደሩ ሲጨፈጭፉ፣ ተጨማሪ ደም የማፍሰስ ስካራቸዉን በግልፅ ሲያቀረሹ ፣ቢል ክሊንተን ከዋሽግተን፣ ቦሪስ የልሲን ከሞስኮ፣ኮፊ አናን ከኒዮርክ፣ የለንደን፣ ፓሪስ በርሊን መሪዎችም እንደ ሩቅ ታዛቢ ከመመልከት ባለፍ ዘግናኙን እልቂት «ኃይ» ለማለት የደፈረ፣የፈለገም አልነበረም።
የሰሬብሬንሳዉ ጭፍጨፋ 25ኛ ዓመት ሲዘከር በቀደም ግን የያኔዉ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ቢል ክሊንተን  እንዳሉት ያ ዕለት ዓለም ለሰብአዊነት ክብር ጀርባዉን የሰጠበት ክፉ ቀን ነበር።
 «ኃምሌ 11 በቦስኒያ ያለፈ ታሪክ ዉስጥ ጨለማ ጊዜ ብቻ አልነበረም።ሁላችንም በጋራ ልንቆምለት ለሚገባዉ ሰብአዊነት ጀርባችንን የሰጥንበት አሳፋሪ ዕለትም ነበር።»
አባት እና ልጅ እንደ  ሚሊዮን ብጤዎቻቸዉ ዓለም  ፊቱን እንዳዞረባቸዉ  ሊያዉቁ  በርግጥ አይችሉም ነበር።የካራዚችን የመጋቢት አዋጅ፣ የጄኔራል ሚላጂችን የከዚያ ቀን በፊት ምግባር ወይም የሁለቱንም ሹማምንት አዉሬነት፣ ሙስሊሞችን ጠራርጎ የማጥፋት  ዕቅድ፣ አላማን  ባለፍ አገደም ከመስማት ዉጪ በቅርብ የሚከታተሉበት ምክንያት፣ ቢከታተሉትም በቅጡ የሚያስተነትኑበቅ ዕዉቀት፣ ብስለትም የላቸዉም። 
ጄኔራል ሚላጂጅች የሚያዙት የሰርቦች ጠንካራ ጦር፣ ከመጋቢት ጀምሮ የከበበዉን የቦስኒያክን ደካማ ጦር ደፍልቆ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ጦር ገፍትሮ ሰሬብሪንሳን ተጠቆጣጠረ።
 ጄኔራሉ ከተማይቱን  ቀድሞ የያዙ ወታደሮቻቸዉን ጎበኙ።«ጎበዛዝት እንኳን ደስ አላችሁ።ጥሩ ሥራ ነዉ።ሰዎቻችን ቀድመዋል አይደል።ሲሌ፣ ሲሌ ክርስቲች ወዲሕ ኑ።ይሕን (የቦስኒያ) ባንዲራ አዉርዱ።ከእንግዲሕ መዉለብለብ የለበትም።መሬት ላይ ጣሉት።----»
ወዲያዉ የድል ብስራቱን ለሰርቢያና ለቦስኒያ ሰርቦች ሕዝብ አወጁ።«እዚሕ ነን።ኃምሌ 11፤ 1995።የሰርብ ሴሬብሬንሳ ነዉ ያለነዉ።የታላቅዋ ሰርብ በዓል በሚከበርበት ዋዜማ ይሕቺን ከተማ ለሰርብ ሕዝብ ስጦታ አበርክተናል።በመጨረሻም በዳሒስ ላይ ከተቀሰቀሰዉ አመፅ ወዲሕ በዚሕ ግዛት በሚኖሩ የሚኖሩ ቱርኮችን የምንበቀልበት ጊዜ አሁን ነዉ።»
ዳሂስ፣ በ18ኛዉ መቶ ክፍለ ዘመን የክሮኤሺያ ጦር ያመፀባቸዉ የቱርክ ቅጥረኛ ወታደሮች ስም ነዉ።
ልጅ፣ ጦሩን ሲያይ ጠረጠረ ወይም ፈራ።እና ከጥቂት ጓደኞቹ ጋር ወደ ጫካ ሸሸ።አባት አልፈሩም።አልሸሹምም።ወይም አልቻሉም።የጄኔራሉን ዛቻም አልሰሙም።የሰሙት፣ «ዉጊያዉ አብቅቷል።እጃችሁን ከሰጣችሁ የሚነካችሁ የለም  የሚለዉን የጄኔራሉን ማታለያ ነዉ።
የወለደ አንጀት። የሸሸ ልጃቸዉ እርምጃ እንዳይወሰድበት ፈሩ።እና ቢቢሲ -እንደዘገበዉ ልጃቸዉ ከተሸሸገበት ጫካ ወጥቶ እጁን እንዲሰጥ ጠሩት።ያባት ነገር-ሊያድኑት።ልጅም ያባቱን ጥሪ ሰምቶ ተቀየጣቸዉ።ሊድን።ሁለቱም እጅ ሰጡ።ሁለቱም ተረሸኑ።
የስነልቡናዉ ዶክተር ራድኮ ካራዚች  መጋቢት ላይ ባወጁት መሠረት፣የጄኔራል ሚላጂች ጦር፣ የኔዘርላንድ ጦር ከሚቆጣጠረዉ ቅጥር ግቢ የተጠለሉትን  ቦስኒያኮች (የቦስኒያ ሙስሊሞችን) ሳይቀር በተጠና ስልት፣ አባትን ከልጅ፣ አያትን ከልጅ-ልጅ  ጋር የፊጥኝ እየጠፈረ ጨፈጨፋቸዉ።ስምንት ሺሕ።በጣም ወጣቱ 23 ዓመት፣ ሽማግሌዉ ደግሞ 70 ዓመታቸዉ ነበር።
የሰባ ዓመቱ አዛዉንት የሐሰን ፔሲክ፣ ቅሬተ-አፅም የተለየዉ በቅርቡ፣ የተቀበረዉ ደግሞ  ጭፍጨፋዉ በተጀመረ በ25ኛ ዓመቱ፣ የዛሬ አስር ቀን ነበር።ቅዳሜ።አባቴን ቀበርኩ አለ ልጃቸዉ።
 «አባቴን ዛሬ ቀበርኩ፣ ሐሰን ፔሲክን።ከሰለቦቹ ሁሉ አንጋፋዉ ነበር።ከ25 ዓመታት በኋላ አፅሙን መለየት ቻልን።ከእንግዲሕ የመጨረሻ ማረፊያዉን አግኝቷል።»
ሰርቦች ወንዱን ፈጁት።ሴቱን ደግሞ ሚስትን ከባል፣ልጃገረዷን ከእናት አባቷ፣ እሕትን ከወንድሟ እየመነጨቁ ደፈሩ።ደበደቡ።አጋዙ።ሰሬብሬንሳ።ጋዜጠኞች አዲስ ድቅል ቃል አገኙ።ጎሳ ወይም ብሔርን ማፅዳት የሚል።ከዘር አፅጂዎቹ አለቆች ሶሎቮዳን ሜሎሶቪች ወሕኒ ቤት አርፈዋል።ራዶቫን ካራዚች እና ራድኮ  ሚላጂች ወሕኒ ቤት ናቸዉ።በዘር ማጥፋቱ ወንጀል የሚጠረጠሩ ብዙ ሰዎችን ለፍርድ የማቅረቡ ሒደት እንደቀጠለ ነዉ።ዓለም ከዘግናኙ የዘር ማፅዳት ጥፋት፣ ከፍትሕ ሒደቱ ተምሮ ይሆን? ነዉ-መልስ የሚሻዉ ጥያቄ። ኢትዮጵያዉያንስ? ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

Deutschland Gedenkveranstaltungen zum Jahrestag von Srebrenica in Dortmund
ምስል DW/M. Smajic
Bosnien Herzegowina Srebrenica |
ምስል DW/S. Huseinovic
Bosnien und Herzegowina - Gedenken an Srebrenica-Massaker
ምስል Reuters/D. Ruvic
Bosnien und Herzegowina | Gedenken an Srebrenica-Massaker
ምስል Getty Images/D. Sagolj

ነጋሽ መሐመድ

ኂሩት መለሰ