1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሰሜንና ምዕራብ አማራ ክልል ተዘግተዉ የነበሩ ት/ቤቶች ተከፈቱ

ማክሰኞ፣ ኅዳር 22 2013

መንግስት ህግ የማስከበርና የህልውና ዘመቻ ባለው ውጊያ ምክንያት በአንዳንድ የሰሜንና ምዕራብ አማራ ዞኖች ተዘግተው የነበሩ ትምህርት ቤቶች ተከፍተው አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አስታወቀ፣ የ8ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና በቀጣዩ ወር ይሰጣልም ተብሏል፣ ለፈተናው ከ415 ሺህ በላይ ተማሪዎች ይቀመጣሉ፡፡

https://p.dw.com/p/3m4q6
Äthiopien Amhara staatliches Bildungsbüro
ምስል Alemenew Mekonnene/DW

ውጊያዉ ምክንያት በሰሜን ወሎ፣ ዋግኸምራ፣ ሰሜን ጎንደር፣ ምዕራብ ጎንደርና ማዕከላዊ ጎንደር ዞኖች 193 ትምህርት ቤቶች ተዘግተዉ ነበር

መንግስት ህግ የማስከበርና የህልውና ዘመቻ ባለው ውጊያ ምክንያት በአንዳንድ የሰሜንና ምዕራብ አማራ ዞኖች ተዘግተው የነበሩ ትምህርት ቤቶች ተከፍተው አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አስታወቀ፣ በኮቪድ ምክንያት ሲገፋ የነበረው የ2012 ዓ ም የ8ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና በቀጣዩ ወር ይሰጣልም ተብሏል፣ ለፈተናው በ5ሺህ 162 ትምህርት ቤቶች የሚገኙ ከ415 ሺህ በላይ ተማሪዎች ይቀመጣሉ፡፡

 የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ይልቃል ከፋለ ዛሬ በጽ/ቤታቸው በሰጡት መግለጫ ሰሞኑን በአገሪቱ ተከስቶ በነበረውና መንግስት በትግራይ ክልል “ህግ የማስከበርና የህልውና ዘመቻ” ባለው ውጊያ ምክንያት በሰሜን ወሎ፣ ዋግኸምራ፣ ሰሜን ጎንደር፣ ምዕራብ ጎንደርና ማዕከላዊ ጎንደር ዞኖች 193 ትምህርት ቤቶች ተዘግተው ቆይተዋል፡፡

ቢሮ ኃላፊው እንዳሉት አሁን በአካባቢዎች አንፃራዊ ሰለም የሰፈነ በመሆኑ ትምህርት ቤቶቹ ከትናንትና ጀምሮ ተከፍተው ተማሪዎች እየተማሩ እንደሆነ አብራረወተዋል፡፡  ይህ በእንዲህ እንዳለ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ባስከተለው ችግር ትምህርት ቤቶች ባለፈው መጋቢት 2012 ዓም መዘጋታቸውንና እንደገና ጥቅምት 2013 ዓም ቢከፈቱም ተፈጥሮ በነበረው ወቅታዊ ሁኔታ ምክንያት በሰሜንና ምዕራባዊ የአማራ ክልል ዞኖች በርካታ ት/ቤቶች እንደገና ተዘግተው በመቆየታቸው አገር አቀፍና ክልል አቀፍ ፈተናዎች መራዘማቸውን አስታውሰዋል፡፡

 ጊዜው እየገፋና ሁኔታውም ጫና እየፈጠረ ሰኔ ላይ ይሰጥ የነበረው የ2012 ዓ ም የ8ኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተና በቀጣዩ ወር እንደሚሰጥ ዶ/ር ይልቃል ተናግረዋል፡፡ ፈተናውን መስጠትየሚያስችሉ ዝግጅቶች ሙሉ በሙሉ የተጠናቀቁ መሆናቸውን ቢሮ ኃላፊው አመልክተው ለተግባራዊነቱ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ትብብር እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡

ተማሪዎችም ፈተናው ከሌላው ጊዜ የተለየ አለመሆኑን አውቀው ባለችው አጭር ጊዜ ተዘጋጅተውና በስነልቦናም ዝግጁ ሆነው ፈተናቸውን እንዲፈተኑ አሳስበዋል፡፡  የቢሮው የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ቢያዝን በበኩላቸው የ2013 የ8ኛ ክፍል ተፈታኞች ሁሌም እንደሚደረገው በመደበኛ የመፈተኛ ጊዜያቸው ሰኔ ወር አጋማሽላይ እንደሚሰት ተናግረዋል፡፡

ዓለምነው መኮንን

አዜብ ታደሰ

ነኃሽ መሐመድ