1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«የእስረኞች መፈታትና ክስ መቋረጥ ለዕርቅ፣ ለመግባባትና ሰላምን ለማምጣት ጥሩ ርምጃ ነው።»

እሑድ፣ ግንቦት 26 2010

የኢትዮጵያ መንግሥት በተለያዩ ምክንያቶች የተፈረደባቸውን እና ክሳቸዉ በሂደት ላይ ያሉ እስረኞችን ክስ ለማቋረጥ እና በይቅርታ ለመፍታት ከወሰነ ካለፉት ጊዚያት ወዲህ ብዙዎች ከወህኒ ቤት ወጥተዋል። በሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን በወጣ አንድ ዘገባ መሰረት፣ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 10ሺ 63 ታራሚዎችና የቀጠሮ እሥረኞች ከእስር መለቀቃቸው ተገልጿል።

https://p.dw.com/p/2yoq4
Äthiopien Oppositioneller Andargachew Tsige  begnadigt
ምስል DW/Yohannes Gebreegziabher

የእስረኞች መፈታት እና ክሳቸው መቋረጥ

 መንግሥት የአገር አንድነትን ለማጠናከር፣ እንዲሁም የዴሞክራሲ ሥርዓቱን ለማስፋት ሲባል ባለፉት ወራት ፣ በተለይ ዶክተር አብይ አህመድ አዲስ ጠቅላይ ሚንስትር ሆነው ከተሰየሙ ጀምሮ በወሰደው ርምጃ ብዙ የፖለቲካ እስረኞች፣ ጋዜጠኖች እና በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው የታሰሩ ተለቀዋል። ሰሞኑን ከተለቀቁት 576 መካከል 137ቱ በሽብርተኝነት፣ 31ዱ ደግሞ በሙስና ክስ የታሰሩ ናቸው።

ከነዚህም መካከል በሽብረትኝነት ወንጀል ታስረው የነበሩት የቀድሞዉ የግንቦት 7 የፍትሕ፤የነፃነት እና የዴሞክራሲ ዋና ጸሐፊ  አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ፣  የቀድሞዉ የአንድነት ለፍትሕ እና ለዴሞክራሲ ምክትል ሊቀመንበር አቶ አንዱዓለም አራጌ፣ የልብ ሕክምና ባለሙያው ዶክተር ፍቅሩ ማሩ፣ እና  የፌደራሉ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ባቀረበው ጥያቄ መሰረት  ክሳቸው ከተቋረጠ መካከል የግንቦት 7 የፍትሕ፤ የነፃነት እና የዴሞክራሲ መሪ ዶክተር ብርሃኑ ነጋ እና የኦሮሞ ሚዲያ ኔትዎርክ፣ በምህፃሩ ኦ ኤም ኤን ዋና ስራ አስኪያጅ ጃዋር መሀመድ፣ እንዲሁም፣  ኢሳት እና ኦ ኤም ኤን የቴሌቪዥን ጣቢያዎች፣  አቶ መላኩ ፈንታ፣ አቶ ገብረዋሕድ ገብረሥላሴ፣ አቶ ዓለማየሁ ጉጆና ሌሎች ባለሥልጣናት ባለሀብቶች ይገኙባቸዋል።

ቀደም ባሉ ሳምንቶችም እስከቅርብ ጊዜ በፊት ድረስ ከኢትዮጵያ ዉጪ ሲንቀሳቀሰዉ የነበረው የተቃዋሚው ፓርቲ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር፣ ኦዴግ ከመንግሥት ጋር በደረሰው ስምምነት መሰረት የፓርቲዉ አመራሮች በኢትዮጵያ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ዉስጥ ለመሳተፍ አዲስ አበባ ገብተዋል። ይህ አሁን እየታየ ያለው የታሳሪዎች ፣ የታዋቂ ፖለቲከኞች እና ጋዜጠኞች መፈታት እና ክሳቸው መቋረጥ በሀገሪቱ የወደፊት የፖለቲካ ሂደት ላይ ስለሚኖረው አንደምታ ውይይት አካሂደናል።

ሙሉ ዝግጅቱን ከድምፅ ማዕቀፉ መከታተል ይቻላል።

አርያም ተክሌ

እሸቴ በቀለ