1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሰላም ስምምነቱ ገቢራዊ እንዲሆን እገዛ ተጠየቀ።

ሰኞ፣ ኅዳር 12 2015

ሲቪክ ማሕበረሰብ ድርጅቶች ስለ ሰላም ውትወታ በማድረግ ደቡብ አፍሪካ ላይ በመንግሥት እና በህወሓት መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት ገቢራዊ እንዲሆን እንዲያግዙ ተጠየቁ። ድርጅቶች ጦርነት ያወደማቸውን አካባቢዎች በመገንባት፣ በሕዝብ ሥነ ልቦና ላይ የደረሰውን ጉዳት በማከም፤ የተደረሰው ሰላም የማውረድ ትምምን እንዲጠናከር እንዲያስችሉ ጠይቋል።

https://p.dw.com/p/4Jpz3
Treffen des äthiopischen Rates der Organisationen der Zivilgesellschaft
ምስል Solomon Muchie/DW

በሕዝብ ሥነ ልቦና ላይ የደረሰውን ጉዳት በማከም ድጋፍ እንዲደረግ

ሲቪክ ማሕበረሰብ ድርጅቶች ስለ ሰላም ውትወታ በማድረግ ደቡብ አፍሪካ ላይ በመንግሥት እና በህወሓት መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት ገቢራዊ እንዲሆን እንዲያግዙ ተጠየቁ። የኢትዮጵያ ሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት በሥሩ የሚገኙ 4 ሺህ ያህል ድርጅቶች ጦርነት ያወደማቸውን አካባቢዎች በመገንባት፣ በሕዝብ ሥነ ልቦና ላይ የደረሰውን ጉዳት በማከም ፣ የሻከሩ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቶች እንዲስተካከሉ በማድረግ የተደረሰው ሰላም የማውረድ ትምምን እንዲጠናከር እንዲያስችሉ ጠይቋል።

ምክር ቤቱ በኦሮሚያ ክልል በየ ጊዜው እያገረሸ በንፁሃን ዜጎች ላይ እየደረሰ ያለው ግፍ እና ግድያ እንደሚያሳስበው ገልጾ ችግሩ የመንግሥትን ትኩረት የሚፈልግ ነው ብሏል። ማንኛውም ፍላጎቶች በሰላማዊ መንገድ ብቻ መፍትሔ እንዲያገኙ ማድረግም የተገባ ነው ሲልም ገልጿል። ለሁለት ዓመታት ዘልቆ በተለይ ሰሜን ኢትዮጵያን ክፉኛ ያደቀቀው ጦርነት ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ በፌዴራሉ መንግሥት እና ምርጫ ቦርድ ሕልውናውን በዘረዘው፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ደግሞ አሸባሪ ብሎ በፈረጀው ሕወሓት መካከል የሰላም ስምምነት ተደርጎበት ፣ ኬንያ ላይ በአተገባበረ ዙሪያ የሁለቱም የጦርነቱ ተዋንያን የጦር አዛዦች ውይይት ተደርጎበት ትምምን ላይ ተደርሷል።

"ለዚህ ትምምን አተገባበር የሁለቱንም አካላት ቁርጠኝነት ይጠይቃል" የሚለው የኢትዮጵያ የሲቪክ ማሕበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ይህ እንዲሳካ የሲቪክ ድርጅቶች ከፍተኛ እገዛ እንዲያደርጉ የምክር ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሄኖክ መለሰ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ጠይቀዋል። "የሻከሩ ማሕበራዊ ትስስሮችን ለማደስ፣ የላላውን የሕዝቦች መስተጋብር ለማከም፣ የተበላሸውን ለማስተካከል እና ወደነበረበት ለመመለስ የሕዝብ ለሕዝብ ሥራዎችን ጨምሮ በርካታ ሥራዎችን መሥራት ይገባል"

Treffen des äthiopischen Rates der Organisationen der Zivilgesellschaft
ምስል Solomon Muchie/DW

በህወሓት በኩል የኤርትራ ሠራዊት ከትግራይ ክልል ይውጣ ያሚለው ጥያቄ ከሰሞኑ በስፋት እየቀረበ ነው። ይህ አዝማሚያ የሰላም ስምምነቱን ይጎዳ ይሆን ? ጥያቄ አጭሯል። ሲቪክ ማሕበረሰብ ድርጅቶች ምን ሊያግዙ ይችላሉ የተባሉት አቶ ሄኖክ "ሁለቱም ወገኖች ቁርጠኝነት እንዲኖራቸው ውትወታ ማድረግ" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሲቪክ ማሕበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ዋና ዳይሬክተር በሥራቸው የሚገኙ ድርጅቶች በኦሮሚያ ክልል በንፁሃን ዜጎች ላይ በሚደርሰው ግድያ እና ማፈናቀል ላይስ ምን ሰሩ ተብለው ተጠይቀዋል። "ሁኔታው በጣም ያሳስበናል። በኦሮሚያ ክልልም ሆነ በሌላ አካባቢ ያለ ችግሮችን በኃይል ለመፍታት ከመሞከር ይልቅ ወደ መሃል መጥተው ተመሳሳይ በሆነ ምልኩ በጠረንጴዛ ዙሪያ እንዲፈቱ እናሳስባለን" ብለዋል። ኃላፊው አክለውም በትግራይ ክልል ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የሲቪክ ድርጅቶች ጋር በመልሶ ግንባታ ረገድ እየተገናኘን ለመሥራት ተዘጋጅተናል ብለዋል።

"ግንኙነት እናደርጋለን። እንነጋገራለን። ያሉት የግንኙነት ሁኔታዎች አስቸጋሪ ቢሆኑም አንዳንዴም እየተዘጉ አየተቆራረጠ ቢሆንም ተቀናጅቶ መሥራት ደግሜ ያስፈልጋል። ከዚህ አንፃር ጥረት ይጠይቃል" የኢትዮጵያ የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት በደቡብ አፍሪካው የሰላም ስምምነት ውስጥ የተካተተው የሽግግር ፍትሕ እውን እንዲሆን የአፍሪካ የሽግግር ፖሊሲ ማእቀፍን መሰረት በማድረግ ለሚዘጋጀው የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ አስፈላጊውን ድጋፍ አደርጋለሁ ብላል።

 

ሰለሞን ሙጬ

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሐመድ