1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የራስታፋሪያኑ ማህበረሰብ በኢትዮጵያ

ሰኞ፣ ጥቅምት 10 2012

በኢትዮጵያ የሚገኙት የራስታፋሪያን ማህበረሰብ ቁጥር እየተመናመነ መምጣቱን ያዉቃሉ? ራስታፋሪያን ማለትስ ምን ማለት ነዉ? የዶይቼ ቬለ «DW» የጀርመንኛዉ ክፍል የአዲስ አበባ ወኪል ማርያ ጌርት ኒኮልሲ በቅርቡ ወደ ሻሸመኔ ተጉዛ ጃማይካኑን ጎብኝታና አነጋግራ የዘገበችዉን በዛሬዉ የባህል መሰናዶ ይዘን ቀርበናል።

https://p.dw.com/p/3RTHe
Äthiopien - Rastas Shashamane - Bob Marley Plakat
ምስል DW/M. Gerth Niculescu

በሻሸመኔ ወደ 200 የሚሆኑ ራስታፋሪያን ይኖራሉ፤ በ 1990 ዎቹ ወደ 2000 ሺህ ይኖሩ ነበር

ራስታፋሪያን በጃማይካ በ1930ዎቹ ዓ.ም  የተነሣ እንቅስቃሴ እምነትና የአኗርኗር ዘይቤ ነዉ። ዛሬ በዓለም ዙርያ ምናልባት አንድ  ሚሊዮን ራስታዎች መኖራቸዉ እንደሚገመት አንዳንድ ዘገባዎች ያመለክታሉ። «ራስታፋራይ»የሚለዉ ስያሜ የመጣዉ ከአጼ ኃይለ ሥላሴ ቀድሞ አርእስት ከራስ ተፈሪን በማክበር መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ። አብዛኛዉ የማኅበረሰብ ክፍል ከአፍሪቃ እንደመጣ የሚነገርለት የጃማይካ ነዋሪ፤ በከጎርጎረሳዉያኑ 1800 ቀደም ብሎ ጀምሮ ከአፍሪቃ ለሸንኮራ አገዳ እርሻ ለስኳር ምርት ከአፍሪቃ የተወሰደ ሕዝብ እንደሆነ ተመልክቶአል። በጎርጎረሳዉያኑ 1962 ዓ.ም ከታላቅዋ ብሪታንያ ቅኝ ግዛት የተላቀቀችዉ ጃማይካ ከነጻነት በኋላ በሃገሪቱ የሸንኮራ ምርት ቀጥሎአል። የጃማይካ ሕዝብም ጥልቅና ጽኑ መንፈሳዊነት ያለዉ የመጽሐፍ ቅዱስ አንባቢ በመሆኑ በወቅቱ ሃገሪቱ በርካታ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎችን መጀመራቸዉ ይነገራል። አብዛኛዉ የጃማይካ ሕዝብ ከአሻንቲ መንግሥት የመጣ በመሆኑ፤ ከምዕራብ አፍሪቃ የተዘረጉ ልማዶች፣ እምነቶች ወይም ተጽእኖችም አሉት።  አሻንቲ መንግሥት ከ1662 እስከ 1949 ዓ.ም ድረስ በዛሬዋ ጋና አካባቢ የነበረ ግዛት ነው። ከአካን ብሔር ግዛቶች አንዱም ነበር። የብሔሩ ስም በአካንኛ በትክክል «አሳንቴ»፣ የአገሩም ስም «አሳንቴማን» ተብሎ ይጠራል ። አካን የተባሉት ብሔሮች ከጥንታዊትዋ ጋና መንግሥት (በዛሬው ማሊና ሞሪታኒያ) ከ1068 ዓ.ም በኋላ እንደ ፈለሱ ነዉ የታሪክ መዝገባት የሚያሳዩት። ታድያ ዛሬ ስለ ጃማይካ ሲወራ ጋና ሞሪታንያብሎም የጥቁር አፍሪቃዉያን ሕዝብ ሁሉ ያካትታል።

Äthiopien - Rastas Shashamane - Ras Paul
ምስል DW/M. Gerth Niculescu

ምሽት ላይ ነዉ ከአዲስ አበባ 255 ኪሎሜትር ርቀት ላይ የምትገኘዉ የሻሸመኔ ሰማይ ቀጋ መስሎአል። የኢትዮጵያዉያን ዓለም አቀፍ ማኅበር «EWF» ቅጽር ግቢ በሚገኘዉ ቤት ዉስጥ ጥቂት ራስታፋሪያዎች ሰብሰብ ብለዉ በምርምር ላይ የሚገኙ ጥቁሮች ምን ያህል በደል እንደሚደርስባቸዉ የሚያሳይ  አንድ ዘጋቢ ፊልምን ይከታተላሉ። ዘጋቢ ፊልሙን በተመስጦ ከሚከታተሉት ራስታፋሪያዎች መካከል « የስ ልክ ነዉ» ሲል ይሰማል። ፊልሙን በክፍሉ ከተደረደሩት ወንበሮች መጀመርያ ረድፍ ላይ ሆነዉ ከሚከታተሉት ራስታፋሪያዎች መጀመርያ ረድ ፍ ላይ የተቀመጠዉ እና በአረንጓዴ ቢጫ ቀይ ቀለም ያሸበረቀ የሹራብ ኮፍያ ያጠለቀ ራስታፋሪያን ራስ ፓዉል ተቀምጦአል። የኢትዮጵያዉያን ዓለም አቀፍ ማኅበር «EWF»  አለ ራስ ፓዉል ለራስታፋሪያዎች ብቻ ሳይሆን ለጥቁር ኢትዮጵያዉያን ሁሉ ነዉ። ራስ ፓዉል ሻሸመኔ ላይ የሚገኘዉ የኢትዮጵያዉያን ዓለም አቀፍ ማኅበር «EWF» ብቸኛዉ ሰራተኛ ነዉ። የኢትዮጵያዉያን ዓለም አቀፍ ማኅበር «EWF» የጥቁር ሕዝቦችን አንድነት ለማጠናከር  እና ኢጣልያ በኢትትዮጵያዉያ ላይ የጀመረችዉን ወረራ ለመታገል በ 1930 ዓ.ም በዩናይትድ ስቴትስ የተቋቋመ ማኅበር ነዉ።  ማኅበሩ ዓላማዉን አሳክቶ በ 1941 ንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ከስደት ተመልሰዉ የስልጣን መንበራቸዉን ዳግም ለመቆናጠጥ በቁ። ከዝያም ነዉ፤ጃንሆይ ሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት እንዳበቃ  ወደ ኢትዮጵያ ለሚመጡና መጠግያ ለፈለጉ ጥቁሮች በሻሸመኔ 200 ሄክታር መሬት በስጦታ መልክ ያበረከቱት። ከዝያን ጊዜ ጀምሮ ነዉ በሻሸመኔ የኢትዮጵያዉያን ዓለም አቀፍ ማኅበር «EWF» ከዩናይትድ ስቴትስ  ብሎም ከጃማይካ የሚመጡ ጥቁሮችን በመቀበል ማደራጀት የጀመረዉ።     

«እጅግ በጣም ጥሩ የሆነ ዉሳኔ ነበር» ሲል የማኅበሩን ምስረታ ዉሳኔን ያደንቃል ፤ በሻሸመኔ የሚገኘዉ የዚህ ማኅበር ብቸኛ ሰራተኛ የራስታፋሪያንማኅበረሰብ አባል ራስ ፓዉል

«በሃይማኖታዊ አሳቤ እኛ በሮማ ካቶሊክ ቤተ-ክርስቲያን እና በፕሮቴስታንት ቤተ-ክርስቲያን በባርነት ተገዝተናል ፣ እነዚያም አብያተ-ክርስቲያናት ከአፍሪካ የፈለቁ አይደለም፣ በሃይማኖትም አመለካከታቸው በጣም አውሮጳዊ ነው።  አብዛኛዎቹ የዓለም ሃይማኖቶች መሰረቶቻቸውን በአፍሪካ ውስጥ ማግኘት ይችላል። የባርነት ሰንሰለቱ ከተበጠሰልን በኋላ ደግሞ በፖለቲካ በምዕራብ ውስጥ ደግሞ ሕጋዊነትን ለማግኘት በመሞከር ለረዥም ጊዜ ታግለናል። እውነታው ግን የፖለቲካ ስልጣን ማግኘት የምንችለዉ፣ ራሳችንን መምራት ከቻልን፤ እንዲሁም ብቁ ሆነን ከተገኘን ብቻ ነዉ። ይህንን ማድረግ የምንችለዉ ደግሞ ወደ አፍሪቃችን ከተመለስን ነዉ። »

Äthiopien - Rastas Shashamane - Ras Paul
ምስል DW/M. Gerth Niculescu

ንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ከጣልያን ወረራ በኋላ ከስደት ወደ ሃገራቸዉ ኢትዮጵያ ከተመለሱ በኋላ ይህን የመሬት ይዞታ ለጥቁር ሕዝብ ሁሉ የሰጡ ቢሆንም ፤ ወደ ሻሸመኔ ከመጡት መካከል አብዛኞቹ ጃማይካዉያን ሆነዉ ተገኙ። ጃማይካኖች ደግሞ ወደ አፍሪቃ ያመጣቸዉ ጉዳይ ጃንሆይን ለረጅም ጊዜ ሲጠበቅ የነበረዉ ሚሲህአችን  ብለዉ ስለሚያምኑባቸዉ ነዉ። ከዝያም ነዉ ጀማይካዉያኑ ይህን እሳቤያቸዉን ወደ ጠንካራ እመነት የቀየሩት። በጎርጎረሳዉያኑ 1966 ዓ.ም ንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ  ለጉብኝት ወደ ጃማይካ ባቀኑበት ወቅት ራስታፋሪያኑ ሻሸመኔ መኖር  እንፈልጋለን ሲሉ በግልፅ ጥያቄ አቀረቡላቸዉ። 

በ 1930 ዓም የተጀመረዉ የራስታፋሪያኑ ንቅናቄ «ራስታ» በመባልም አጠር ባለ ስሙ ይታወቃል። በአሁኑ ወቅት በዓለም ዙርያ ባሉ ሃገራት ዉስጥ ሁሉ ይህ የእምነት ንቅናቄ ሲተገበር ይታያል። ሻሸመኔ ላይ የሚገኘዉና የኢትዮጵያዉያን ዓለም አቀፍ ማኅበር «EWF» በሚል የሚታወቀዉ የራስታፋሪያኑ ማኅበር ብቸኛ ሰራተኛ ፓዉል ራሱ ከሃገሩ ከታላቅዋ ብሪታንያ ወደ ኢትዮጵያ የመጣዉ የዛሬ 20 ዓመት እንደሆን ይናገራል። የራስታፋሪያኑ እምነት በብሉይ ኪዳን ላይ የተመሰረተ እንደሆን የእምነቱ ተከታዮች  ይናገራሉ። ራስ ፓዉልም ይህን ይናገራል።

«በባርነታችን መጽሐፍ ቅዱስ እንድናነበዉ የተሰጠን ብቸኛ መጽሐፍ ነበር። በመጽሐፍ ቅዱስ መንፈሳዊ ቁርኝታችንም ኢትዮጵያን በመጽሐፍ ቅዱሱ ውስጥ አየን፤ ራሳችንንም ከዚያ ጋር አገናኘን። እስራኤላዉያንም ወደ ግብፅ ሄደው ለ 400 ዓመታት በባርነት መቀመጣቸዉን፤ ከዚያም ወጥተው ኃያሉ አምላክ የገዛ አገራቸውን እንደሚያዘጋጅላቸዉ የሚነግረዉን ታሪክንም አወቅን። »      

የመጀመርያዎቹ ራስታፋሪያን ወደ ሻሸመኔ መግባት የጀመሩት በጎርጎረሳዉያኑ  1960 መጨረሻ እና 1970 አጋማሽ እንደነበር ተመልክቶአል። ሁለተኛዉ እና በርካታ ራስታፋሪያን ወደ ኢትዮጵያ የገቡት ደግሞ በ 1990ዎቹ መጀመርያ ላይ እንደነበር ተጠቅሶአል።  በሻሸመኔ ቀደም ብለዉ በገቡትና በአዲሶቹ  ራስታፋሪያን መካከል ክፍተት እንደሚታይ ራስታፋሪያኑ ይናገራሉ። ቀደም ብለዉ የመጡቱ ቀደም ባሉት ዓመታት የነበረን የኢትዮጵያ ኑሮአችን አስፈሪ አሳዛኝ ችግር የተሞላዉ ሲሉ በመሳቀቅ ያወሳሉ። ይህን ታሪካቸዉን ደግሞ ለአዲሱ ትዉልድ ማለት በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ ለመጡት ትዉልዶች ማዉራትን አይፈልጉም ። ቆየት ያሉት ትዉልዶች አዲስ የመጡት ራስታፋሪያን አካባቢዉ ላይ ለመኖር እና ለመላመድ ልክ እንደቀደመዉ ጊዜ የከፋ ችግር አልገጠማቸዉም ብለዉም ያምናሉ። ለበርካታ ዓመታት የመንግሥት ድጋፍና ተቀባይነት ወደ እኛ ያጋደለ ነበር ሲል የሚያስታዉሰዉ ራስ ፓዉል፤ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን በራስታፋሪያኑ መካከል ግጭት ዉዝግብ፤ ድሕነት እንዲሁም በኢትዮጵያኑ ማኅበረሰብ ዉስጥ ተዋህዶ ለመኖር ያለዉ ከባድ ችግር አብዛኞቹን ራስታፋሪያን ስራ ፍለጋ ወደ አዲስ አበባ እንዲሄዱ አልያም ወደሌሎች ሃገሮች እንዲሰደዱ መዳረጉን ይናገራል። በአሁኑ ወቅት በሻሸመኔ ወደ 200 የሚሆኑ ራስታፋሪያን እንደሚገኙ የገለፀዉ ፓዉል ፤ በ 1990 ዎቹ ዓመታ ወደ 2000 ሺህ የሚሆኑ ራስታፋሪያ በሻሸመኔ ይኖሩ እንደነበርም ራስ ፓዉል ያስታዉሳል።     

Äthiopien - Rastas Shashamane - Ras Kawintesseb
ምስል DW/M. Gerth Niculescu

ራስ ክዊንቴሴብ የተባለዉና ከትሬኒዳድ እና ቶቤጎ የመጣዉ ሙዚቀኛዉ ራስታፋሪያን ኑሮዬን በኢትዮጵያ ለማድረግ ወስኜ ወደዚህ ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት ያሰብኩት የዛሬ 40 ዓመት ነበር ሲል ይናገራል።

«ወደዚህ ለመምጣት ያሰብኩት ከ 40 ዓመታት በፊት ነበር። ነገር ግን  እዚህ እስክደርስ ብዙ ጊዜን ነዉ የወሰደብኝ። ምክንያቱ ደግሞ ከመገለጥ ላይ የተመሠረተ ነው፤ ይህም በግል ነገሩ እስኪገለጽልኝ ማለት ነው፤ በመጽሐፍ ቅዱስም እንደሚጠቅሰዉ እንደ ንጉሥ ሆኖ የሚመጣው ክርስቶስ እስኪገለጥልኝ ድረስ ማለት ነው። በዚህም የታየኝና የተገለጠልኝ ያ መለኮታዊ ባህሪ ያለው ገጸ-ባሕሪ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ መሆናቸዉ ነዉ። »   

በቅርቡ የኢትዮጵያ መንግሥት በሃገሪቱ ከ 10 ዓመታት በላይ ለሚኖሩ ራስታፋሪያን ብሔራዊ የመኖርያ መታወቅያ መስጠት መጀመሩ ተመልክቶአል። ይህ ለራስታፋሪያኑ የተሰጠዉ መታወቅያ ለመኖርያ ፈቃድ ብቻ ሳይሆን፤ የመኖርያ ፈቃድ የሌላቸዉ ሰዎች መክፈል ያለባቸዉን አልያም ድንበር ሲያቋርጡ መክፈል የሚጠበቅባቸዉን ገንዘብ መክፈል አይጠበቅባቸዉም። 

ራስታፋሪያኑ ነዋሪነታቸዉ ኢትዮጵያ የሆነ የዉጭ ሃገር ዜጎች በሚል በተሰጣቸዉ መታወቅያ ቤተሰቦቻቸዉን ጠይቀዉ መመለስ ይችላሉ። የፈለግንበት መሄድን እንችላለን ያለዉ ከኢንጊሊዝ የመጣዉ ራስታፋሪያን ራስ ፓዉል፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ይህን መታወቅያ እንደሚሰጥ ባስታወቀ ጊዜ፤ በራስታፋሪያኑ ማኅበረሰብ ዘንድ ትልቅ ደስታ ከፍተኛ ድግስ እንደተካሄደ ገልፆአል። በመሆኑም አሁን ራስታፋሪያን ሁሉ ኢትዮጵያ ዉስጥ በሕጋዊ መንገድ መስራት ይችላሉ ልጆቻቸዉንም ትምህር ቤት መላክ ይችላሉ ብሎአል። 

ለአንዳንዶች ራስታፋሪያ ግን ይህ በመታወቅያ የተሰጠ ሕጋዊነት በቂ አይደለም። እኔ እራሴን ወደ ሃገሬ የተመለስኩ ዜጋ አድርጌ ነዉ የምቆጥረዉ ሲል የሚናገረዉ ከትሬኒዳድ እና ቶቤጎ የመጣዉ ራስ ክዊንቴሴብ ፤ምክንያቱን እንዲህ ይናገራል።  

«ለዚህ ነው እኔ እራሴን ወደ አገሩ  እንደተመለሰ ኢትዮጵያዊ የምቆጥረው። እናም ይህንን ሀገር ጥሎ ለመመለስ ወይም ወደ ሌላ ሀገር  ሄዶ ለመኖር ፍላጎት የለኝም። ስለዚህ እኔ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ለመሆን መፈለጌ ትርጉም ይሰጠኛል። የዉጭ ሀገር ዜጋ በመሆኔ ርካታ ስላላገኘሁ፤ ኢትዮጵያዊ ዜግነትን ለማግኘት አመልክቻለሁ። በነገራችን ላይ ይህ አዲስ የዜግነት ጉዳይ  በተመለከተ የሚያስደስተው፤ ማለት ይሄ ከዉጭ ለተመለሱ ትዉልደ ኢትዮጵያዉያን የሚሰጠዉ እና ብዙ ገንዘብ የሚያወጣዉ የዲያስፖራ ካርድ እያሉ የሚጠሩት መታወቅያን በተመለከተ መንግሥት ትልቅ ነገር አድርጓል ማለት ይቻላል።»

Äthiopien - Rastas Shashamane - ehemalige königliche Flagge Äthiopiens
ምስል DW/M. Gerth Niculescu

ሙዚቀኛዉ የትሬኒዳድ እና ቶቤጎ ተወላጁ ራስታፋሪያን በሻሸመኔ አንዲት ኢትዮጵያዊትን አግብቶ ነዉ  ቤተሰብ መስርቶ ሙዚቃን በተለያዩ መድረኮች እያቀረበ ይኖራል።  በሙዚቃዉ ምክንያትም በኢትዮጵያዉያኑ ማኅበረሰብ ይበልጥ ተዋህዶ ተዋህዶ እንደሚኖር ተመክቶአል። በሻሸመኔ በሚኖሩ ራስታፋሪያን ዘንድ ይህ አይነቱ አጋጣሚ ግን በጣም ጥቂት መሆኑ ነዉ የተመለከተዉ። ራስታፋሪያኑ በኢትዮጵያዉያኑ መሬታችን ይወሰዳል ብለዉ ስለሚፈሩ፤ ሌሎች አማርኛ ለመማርና ለመግባባት አልያም ባህሉን ለመተዋወቅ ምንም አይነት አጋጣሚ ስለሌላቸዉ ተዋህደዉ ለመኖር አለመቻለቸዉ ነዉ በምክንያትነት የተቀመጠዉ። ራስ ፓዉል ከኢትዮጵያዉያን ጋር ተዋህዶ መኖርን እንደሚሻ ይናገራል ግን ይላል በቁጭት፤

«በኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ዉስጥ የምኖረዉ እኔ እንደምፈልገዉ ተቀላቅዬ አይደለም ። ከዚህ በላይ በውስጣቸዉ ተዋህጄ መኖርን እሻለሁ። ሆኖም በሀገሪቱ የፖለቲካ ችግር ምክንያት፤ በተለይም በስጦታ በተሰጠው መሬት ላይ ያለው የፖለቲካ አመለካከት ውጥረት የሞላበት ነው።  እዚህ  ከፍተኛ ስጋት አለን፤ በራስተፈሪያን ላይ ጥቃት ይደርሳል፣ የራስተፈሪያንን መሬት እና የቤት እቃዎችንን የመንጠቅ፣ በዚያም ላይ ለዓመታት በተለይ በንጉሠ ነገሥቱ የልደት ቀን ቤቶቻችንን የመዝረፍ ታሪክ በመኖሩ ስጋት አለ። » እኛ የተቀደሰ ቀን ብለን በመረጥነዉ በጃንሆይ ልደት ጥቃት ይደርስብናል ሲል ፤ ንዴትና ቁጭቱን ይገልፃል። 

ሙሉ ቅንብሩን የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን!

 

አዜብ ታደሰ

ሸዋዬ ለገሠ