1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሦስት የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ መግለጫ

ማክሰኞ፣ ግንቦት 23 2014

የ«ሀገር ጉዳይ ያሳስበናል» ያሉ ሦስት የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍል ሥርዓት አልበኘነት የሕጋዊነት ያህል ነግሷል በማለት የጋራ መግለጫ አወጡ። መግለጫውን ያወጡት፦ እናት ፓርቲ፣ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) እና የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ናቸው።

https://p.dw.com/p/4C693
Äthiopien Addis Abeba | Pressekonferenz - Enat Party, EPRP und "All Ethiopian Unity Party"
ምስል Somlomon Muchie/DW

«አገር በሕግና በሥርዓት እንጂ በአፈና አትመራም»

የ«ሀገር ጉዳይ ያሳስበናል» ያሉ ሦስት የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍል ሥርዓት አልበኘነት የሕጋዊነት ያህል ነግሷል በማለት የጋራ መግለጫ አወጡ። መግለጫውን ያወጡት፦ እናት ፓርቲ፣ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት(መኢአድ) እና የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ናቸው። ፓርቲዎቹ «አገር በሕግና በሥርዓት እንጂ በእፈና አትመራም» በሚል ዛሬ በጋራ ባወጡት መግለጫ የችግሮች ሁሉ ምንጭ የሆነው የጎሳና ማንነት አደረጃጀት አለመስተካከሉ እና ጥያቄው መልስ አለማግኘቱ አገር የጥቂት ቡድኖች ሀብት ወደ መምሰል እንድትጓዝ እያደረገ ነው ብለዋል። ፓርቲዎቹ ኢትዮጵያ በምጣኔ ሀብት በኩል የገጠማት ምስልቅል በፖለቲካውና በፀጥታው ዘርፍ ከገጠማት የባሰ እንጂ የተሻለ አይደለም ሲሉ የዋጋ ግሽበትን ለአብነት በመጥቀስ አቋማቸውን ይፋ አድርገዋል። የፓርቲዎቹ የጋራ መግልጫ «አዲስ አበባ ላይ እየተሠራ ያለው ደባ እና ከልክ ያለፈ ጠቅላይነት ተው ባይ አጥቶና መረን ለቆ የነገ አገር ተረካቢ ተማሪዎች ላይ አዲስ ማንነት ለመጫን በሚደረግ መፍጨርጨር ትምህርት ቤቶች ተረጋግተው የሚጠበቅባቸውን የመማር ማስተማር ሂደት መተግበር ወደማይችሉበት ኹኔታ እየገፋ ይገኛል» ብለዋል። በሰሜን ኢትዮጵያ የተከሰተው ጦርነት አማራ፣ አፋር እና ትግራይ ክልሎችን አውድሟል ያሉት ሦስቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ኢትዮጵያንም አክስሯል ሲሉ ገልፀዋል። ፓርቲዎቹ «መንግሥት ማኅበረሰብን በሃይማኖት፣ በወንዝና በቡድን እየከፋፈለ ለመምታትና ለማፈን የሚያደርገውን ጥረት እንዲያቆም» በማለትም ክስና አቤቱታን በአንድ አሰምተዋል። ሕግ በማስከበር ሰበብ የታፈኑ ያሏቸው ንፁሃን ጋዜጠኞች፣ ማኅበረሰብ አንቂዎች፣ የፀጥታ ተቋማት አባላት፣ የፓርቲ አመራሮች እና ሌሎችም እንዲለቀቁ ጠይቀዋል።        

ሰለሞን ሙጬ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

እሸቴ በቀለ