1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሥዕል ጥበብ በብዕር

ዓርብ፣ ታኅሣሥ 17 2012

ስነጥበብን በተፈጥሮ ጸጋነት የሚቀበሉ እንዳሉ ሁሉ ተምሮም በጥበቡ መካን እንደሚቻል የሚናገሩ አልጠፉም። የዕለቱ የወጣቶች ዓለም መሰናዶ  እንግዳ ተፈጥሮ የለገሰችውን  የሥዕል ጥበብ ተጠቅሞ ከእርሳስ ባልተናነሰ በብዕር ሥዕሎችን ይሠራል።

https://p.dw.com/p/3VMCw
Äthiopien l Kugelschreiberkunst von Dagim Haile Mariam
ምስል Dagim Haile Mariam, Foto: M. Teklu

የወጣቶች ዓለም፦የሥዕል ጥበብ በብዕር

እድገቱ ድሬደዋ የሆነው ወጣት ዳግም ኃይለ ማርያም ተፈጥሮ በአፍላነት የቸረችውን የሥዕል ችሎታ ተረድቶ ሥዕልን በራሱ ግዜ መጫጫር የጀመረው በልጅነቱ ነው። እድሜው እየበሰለ ሲሄድ ለአሳሳል ትኩረቱን የሳበውን ብዕር ወይም እስክርቢቶ የመጠቀም ልምድ ተከትሎ የሥዕል ሥራውን በስፋት መስራት መቀጠሉን ይናገራል። ዳግም እየሠራቸው ያሉ የሥዕል ሥራዎች አሁን አሁን በብዙዎች አድናቆት እያገኙ ናቸው። ብዕርን ከወረቀት አገናኝቶ በሚሰራቸው ሥራዎች፤ ከትውልድ አካባቢው ተነስቶ ፣ በእድገት ጉዞው ቀልቡን የገዙትን፤ ከፍ ሲልም በበጎ አድራጎት ሥራ ስማቸው የሚነሱ ግለሰቦች ትኩረቱን እየሳቡት እነሱን መሳል መጀመሩን ይገልፃል። በተፈጥሮ የሥዕል ችሎታን የተካነው ወጣት ዳግም ከታዋቂ ሰዎች በተጨማሪ ሌሎች ሥራዎቹን ከፍ ባለ መጠን ወይም እሱ እንደሚለው A3 መጠን ባለው ወረቀት ሲሰራ ለንድፍ ሥራዎቹ ብቻ እርሳስ ሲጠቀም ትክክለኛ ይዘታቸውን ለማምጣት ግን ብዕሩን ተጠቅሞ በማቅለም ይሠራቸዋል ። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ዳግም የሚሰራቸውን የሥዕል ሥራዎች በተለያዩ ማኅበራዊ  መገናኛ ዘዴዎች በማቅረብ ራሱን እያስተዋወቀ ይገኛል። አሱ እነደሚለው በዚህም ጥሩ ግብረ መልሶች ለማግኘትና ሀሳብ ለመለዋወጥም እየረዳው ነው። ከልጅነቱ ጀምሮ የተፈጥሮ የሰጠችውን ችሎታ የተረዳው ዳግም ከዚያው የልጅነት ግዜ አንስቶ የተለያዩ የሥዕል ሥራዎችን ሲሰራ ነበር የሚለው አብሮ አደግ ጓደኛው፤ በችሎታው ዛሬ ስለሚሰራው ብቻ ሳይሆን ብሩህ መፃዒ ተስፋ ያለው ስለመሆኑ ይናገራል። የሥዕል ጥበብ ችሎታውን የማሳደግ ብርቱ ሕልም እንዳለው የሚናገረው ዳግም በቀጣይ በትምህርት በመደገፍ ሞያውን የተሻለ ደረጃ ማድረስ ውጥኑ መሆኑን ይገልፃል። ወጣትነት ዕድሜ ላይ የሚገኘው ዳግም በአንደ የግል ድርጅት በእንጨት ሥራ የውስጥ ዲዛይነርነት ሞያ በመሥራት ሕይወትን ለማሸነፍ ጥረት ሲያደርግ የሚወደውን የሥዕል ሥራ ባለው ትርፍ ሰዓት ይከውናል። ሁሉንም ነገሮች እዚህ እንዲያደርስ የቤተሰቤ እገዛ ትልቅ ነው ብላል። ዳግም ብዕር ተጠቅሞ የሣላቸውን ሥዕሎች ኤግዝቢሽን ለማሳየት ጥረት እያደረገ ይገኛል። የዳግም ውጥን ብዙ ነው፤ ከሩቁ ምዕራፍ ለመድረስ ከሚያደርገው የዛሬ ጥረት በመለስ አሁንም ቢሆን ከሌሎች መሰል ጓደኞቹ ጋር የድሬደዋን ስም ለማስጠራት ይረዳል ያሉትን እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ናቸው። በየመስኩ ጥበብ የተቸሩ ፍሬዎችን የምታፈራው ድሬደዋ ያፈራቸውን ማሳደግና ለተሻለ ደረጃ በማድረስ ረገድ ያለባትን ተግዳሮት ተቋቁሞ በሥዕል ሥራ የላቀ ደረጃ ለመድረስ ጥረቱን ቀጥሏል፤ ቸር እንዲገጥመው እየተመኘን የእለቱን መሰናዶ እዚህ ላይ ቋጨን ሠላም። ሥራውን የተመለከተው የድሬደዋ  ዘጋቢያችን መሣይ ተክሉ ነጋግሮት ተከታዩን አጠናቅሮታል።

Äthiopien l Kugelschreiberkunst von Dagim Haile Mariam
ምስል Dagim Haile Mariam, Foto: M. Teklu
Äthiopien l Kugelschreiberkunst von Dagim Haile Mariam
ምስል Dagim Haile Mariam, Foto: M. Teklu

መሣይ ተክሉ

ሸዋዬ ለገሠ