1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የምዕራብ ጉጂ ተመላሾች አሁንም ስጋት ላይ ናቸው

ሐሙስ፣ ሰኔ 13 2011

ባለፈው ዓመት በጌዲኦና በጉጂ ማሀበረሰብ አባላት መካከልተከሰቶ በነበረው ግጭት ተፈናቀለው ከነበሩት ግማሽ ሚሊዮን ነዋሪዎች መካከል አብዛኞቹ ወደ ቀድሞው ቀያቸው እየተመለሱ ይገኛሉ። የዝናቡ ወቅት ሳያልፍ ወደ ቀድሞ አካባቢያቸው ተመልሰው የእርሻ ስራ እንደሚጀምሩ ቃል ቢገባላቸውም እስካሁን ተግባራዊ አለመሆኑ እንደሚያሳስባቸው ገልጸዋል።

https://p.dw.com/p/3KmoA
Äthiopien Gedeb Binnenflüchtlinge aus West-Guji
ምስል picture-alliance/dpa/World Vision/Fitalew Bahiru

የምዕራብ ጉጂ ተመላሾች አሁንም ስጋት ላይ ናቸው

በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የጌዲኦ ማሀብረሰብ አባላት ከተፈናቀሉባቸው ቀበሌዎች መካከል በምዕራብ ጉጂ ዞን ቀርጫ ወረዳ የምትገኝው ሂንሺ ቀበሌ ትጠቀሳለች። በዚህች ቀበሌ ከዓመት በፊት በአካባቢው በነበረው ግጭት ጣሪያቸው የተነቃቀሉ፣ ግርግዳቸው የፈራረሱ ቤቶች ዛሬም ድረስ በመንደሩ ይስተዋላሉ።

በቀበሌዋ በሚገኙ መንደሮች ባደረግኩት ቅኝት ከወራት በፊት ወደዚሁ መንደር የተመለሱ ተፈናቃዮች በፕላስቲክ በተሰሩ ጎጆዎች ዳግም ኑራቸውን ጀምረው ተመልክቻለሁ። ከሶስት ልጆቿ ጋር ለወራት በገደብ ወረዳ ተጠልላ የነበረችው ድንገቴ መሪሳ ከተመላሽ ተፈናቃዮች መካከል አንዷ ናት። የዝናቡ ወቅት ከማለፉ በፊት በምዕራብ ጉጂ ዞን ወደሚገኘው የቀድሞ መንደራቸው ተመልሰው የእርሻ ስራ እንደሚጀምሩ በአካባቢው ባልስልጣናት የተገባላቸው ቃል እስከአሁን ተግባራዊ አለመደረጉን ለዶይቼ ቬለ (DW) ተናግራለች። 

“መንግስት ቀድሞ ወደነበርንበት አካባቢያችን እንድንመለስ ባመቻቸው መሰረት በመንደራችን ገብተናል። ወደ እዚህ ከተመለስን በኋላ ግን ቀደም ሲል የነበረን የእርሻ መሳሪያ በመውደሙና በመቃጠሉ እስከአሁን የእርሻ ስራ መጀመር አልቻልንም። የዝናቡ ወቅት ከማለፉ በፊት እንደተመለስን የምርጥ ዘርን ጨምሮ የእርሻ መሳሪያዎች እንደምናገኝ የተነገረን ቢሆንም እስከአሁን ግን ምንም አላገኝንም” ብላለች።

Äthiopien Gedeb Binnenflüchtlinge aus West-Guji
ምስል picture-alliance/dpa/World Vision/Fitalew Bahiru

ቀደም ሲል ተፈናቅለው ከሄዱበት ገደብ ወረዳ ተመልሰው በዚሁ ቀበሌ መኖር ከጀመሩ አንድ ወር እንደሆናቸው የሚናገሩት ሌላው የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ዘለቀ ደያሴ ወደ ቀድሞው አካባቢያቸው በመመለሳቸው ደስተኛ መሆናቸውን ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል። ይሁን እንጂ ከቅርብ ቀናት ወዲህ በተደጋጋሚ ወደ መንደሩ በሚመጡ ታጣቂዎች የተነሳ የደህንንት ስጋት እንዳለባቸው ይናገራሉ። በተለይም ባለፈው ሳምንት ባለቤታቸው በእነኚህ ታጣቂዎች ተይዘው ከተለቀቁ ወዲህ ስጋታቸው ማየሉን ገልጸዋል። 

ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው የምዕራብ ጉጂ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አበራ ቡኖ ተፈናቃዮቹ ያቀረቡት የአርሻ መሳሪያዎችና የምርጥ ዘር ጥያቄ ትክክለኛ መሆኑን ይቀበላሉ። ከጸጥታ ጋር ተያይዞ የተነሳውን ስጋት በተመለከተ አሁንም በአንዳንድ አካባቢዎች ስጋቶች ቢኖሩም መስተዳድራቸው ግን ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን የዞኑን ሰላም ለማስጠበቅ እየሰራ ነው ብለዋል። 

ባለፈው ዓመት በጌዲኦ እና በጉጂ ማህበረሰብ አባላት መካከል ተከሰቶ በነበረው የጎሳ ግጭት ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎች መፈናቀላቸው አይዘነጋም። የፌደራሉ መንግስት እና የደቡብ ክልል ተፈናቃዮችን ወደ ቀድሞ ቀያቸው የመመለስ ስራዎችን ሲያከናወኑ መቆየታቸው ይታወሳል።

ሙሉ ዘገባውን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ። 

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

ተስፋለም ወልደየስ 

እሸቴ በቀለ