1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የምዕራብ ወለጋ ግድያ

እሑድ፣ ሰኔ 12 2014

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ ቶሊ ቀበሌ ትናንት በታጣቂዎች በደረሰ ጥቃት 40 የሚደርሱ ሰዎች አንድ ቦታ ተገድለው ማየታቸውን የዓይን እማኞች ለDW አብራርተዋል፡

https://p.dw.com/p/4CuXf
Äthiopien | Straßenszene in Mendi
ምስል Negassa Deslagen/DW

የምዕራብ ወለጋ ግድያ

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ ቶሊ ቀበሌ ትናንት ጠዋት 3 ገደማ ተጀመረ በተባለው ጥቃት በርካታ ሰዎች ህይወት ማለፉን የአካባቢው ነዋሪዎች ለDW ተናግረዋል፡፡  ከአካባቢው የሸሹ የአይን እማኞች 40 የሚደርሱ ሰዎች አንድ ቦታ ተገድለው ማየታቸውን አብራርተዋል፡፡ በንብረት ላይም ጉዳት መድረሱን ጠቁመዋል፡፡ 
በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ ቶሌ በተባለች ቀበሌ የሸኔ ቡድን ባደረሰው ጥቃት የሰዎች ህይወት መጥፋቱንና ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን የኦሮሚያ ክልል መንግስት ትናንት ማምሻን በማህበራዊ መገናኛ ዘዴ ገልጸዋል፡፡ በታጣቂዎች ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የጠቀሰው መግለጫው ስለ ጉዳት መጠኑ በዝርዝር አልገለጸም፡፡ የኢትየጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽ አሁን ባወጣው መግለጫው በተጠቀሰው ስፋራ በሲቪል ሰዎች ላይ በሸኔ ታጣቂዎች ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን ይፋ አድርጓል፡፡
ከምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ከተማ በ45 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በሚትገኘው ቶሊ በተባለች ቀበሌው ውስጥ ትናንት ታጣቂዎች አደረሱት በተባለው ጥቃት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውና የሰዎች ህይወት ማለፉን ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡ ትናንት በስፍራው የደረሰው ጥቃት በመሸሽ ሌላ ወረዳ ውስጥ እንደሚገኙ የነገሩን አንድ ነዋሪ በጥቃት 12 የበተሰባውን አባላትና ዘመዶችን ማጣታቸውን ተናግረዋል፡፡ ከጠዋቱ 3 ሰዓት ገደማ ታጣቂዎች በተለያዩ አቅጣጫ ተኩስ መክፈታቸውንና በአንድ ስፍራ  40 የሚደርሱ ሰዎች ተገድለው እንደነበርም ነዋሪው ጠቁመዋል፡፡ በርካታ የነዋሪዎች መኖሪያ ቤቶች መቃጣላቸውንም አመልክቷል፡፡ 
ሌላው የቶሊ  ቀበሌ ነዋሪ በስልክ እንደተናገሩት በጥቃቱ ህይወታቸውን ያለፉ ሰዎች ቁጥር ከ50 በላይ እንደሆኑ ገልጸው በቀበሌዋ የሚኖሩ አብዛኛው አርሶ አደሮች  ወደ ጫካ መሸሻቸውን ተናግረዋል፡፡ ቤተሰባቸውን ጨምሮ 25 ሰዎች እሳቸው ከሚኖሩበት ሰፈር ህይወታቸውን ማለፉንም ነዋሪው ለዲዳቢሊው አስታውቋል፡፡ ትናንት በጊምቢ ወረዳ ቶሊ ቀበሌ በነበረው የጸጥታ ችግር በርካታ የቁም እንስሳትም እንደተወሰዱ ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ትናንት ማምሻውን በማህበራዊ መገናኛ ዘዴ ባሰራጨው የሐዘን መግለጫ በምዕራብ ወለጋ ጊምቢ ወረዳ ቶሊ ቀበሌ በደረሰው ጥቃት  የሰዎች ህይወት ማለፉንና ንብረት መውደመውን አስታውቋል፡፡ መግለጫው በደረሰው ጥቃት የደረሰው የጉዳት መጠን አልገለጸም።
በጉዳዩ ላይ ከክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽና ጸጥታ ዘርፍ ቢሮ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረከት ጥረት ስልክ ባለማንሳታቸው ማካተት አልተቻለም፡፡ ሆኖም የክልሉ መንግስት በመግለጫው በታጣቂዎች ላይ የሚወሰደው እርምጃም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አክሏል፡፡ 
በምዕራብ ኦሮሚያ በተለያዩ ጊዜያት በሚፈጠሩት ግጭቶች እና ጥቃቶች ከዚህ ቀደምም በርካታ ሰዎች ህይወት ሲያልፍ እና ንብረት ላይ ጉዳት ሲደርስ ቆይቷል፡፡  በሚደርሱት ጉዳቶች በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች እና መንግስት እርስ በእርሳቸው ሲወነጃጀሉም ይስተዋላል፡፡
ነጋሳ ደሳለኝ
ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር
ታምራት ዲንሳ