የምዕራብ እና ምሥራቅ ጀርመኖች ድንበርና የግንቡ ቅሪቶች
ጀርመንን ምዕራብ እና ምሥራቅ ብሎ የሚከፍለው ግንብ ከ30 አመታት በፊት ቢፈርስም ለታሪክ የተቀመጡ ቅሪቶቹ እና በአገሪቱ ዜጎች ዘንድ ጥሎት ያለፈው አሉታዊ ትዝታ በተለያዩ ከተሞች ይታያል።
ግንብ በሞደለሮይትዝ
ይኸ ሞደለሮይትዝ የተባለች አነስተኛ ከተማን ለሁለት አገር ይከፍል የነበረ ግንብ ቅሪት ነው። በምሥራቅ ጀርመን በኩል በሚገኘው የግንቡ ክፍል ወደ ምዕራብ ጀርመን መሸሽ የሚፈልጉ ዜጎች ግንቡን ቢሻገሩ ለመከልከል ተዘጋጅቶ የነበረ ተጨማሪ የሽቦ አጥር ይገኛል። ከዚህ በተጨማሪ የምሥራቅ ጀርመን ወታደሮች ጥበቃ የሚያደርጉባቸው ማማዎች እና ምሽጎችም አሉ።
የጥበቃው ማማ
በቱይሪንገን እና በባየርን ግዛቶች አዋሳኝ ድንበር ላይ የምትገኘው የሞደለሮይትዝ መንደር የምሥራቅ ጀርመን መንግሥት ባቆመው ግንብ ለሁለት ተከፍላ ነበር። የምሥራቅ ጀርመን ወታደሮች የአገሪቱ ዜጎች ግንቡን ዘለው ወደ ምዕራብ ጀርመን እንዳይሸሹ በእንዲህ አይነት ማማዎች ጥበቃ ያደርጋሉ
ሞደለሮይትዝ
የሞደለሮይትዝ መንደር በምዕራብ እና ምሥራቅ ጀርመን ለሁለት የተከፈለች ነበረች። ዛሬም የመንደሯ አንድ ጎን በቱይሪንገን ቀሪው ደግሞ በባየርን ግዛት ይገኛል። ጀርመንን ሁለት ከፍሎ የነበረው ግንብ ቅሪት እና ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች የሚገኙበት ቤተ መዘክርም በዚሁ መንደር አለ።
የጦር መሳሪያዎቹ
ይኸ በሞደለሮይትዝ መንደር ካለው ቤተ መዘክር ከሚገኙ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች አንዱ ነው።
የጦር መሳሪያዎቹ
ይኸ ብረት ለበስ የውጊያ ተሽከርካሪ በሞደለሮይትዝ መንደር ካለው ቤተ መዘክር ከሚገኙ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች አንዱ ነው። በቤተ መዘክሩ ሶቭየት ኅብረት እና አሜሪካ የሰሯቸው እና በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ግልጋሎት ላይ የዋሉ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች ይገኛሉ።
ወንዞች እና የፍሳሽ ማስወገጃዎች ጭምር ቁጥጥር ይደረግባቸው ነበር
የምሥራቅ ጀርመን መንግሥት ዜጎች ወደ ምዕራቡ እንዳይሻገሩ ክልከላ ባደረገባቸው አመታት ወንዞች እና የፍሳሽ ማስወገጃዎች ጭምር ቁጥጥር ይደረግባቸው ነበር። ይኸ በሞደለሮይትዝ መንደር የሚገኝ ሲሆን በወቅቱ የምሥራቅ ጀርመን ሰዎች ሾልከው ወደ ምዕራቡ እንዳይሻገሩ ከብረት መከልከያ ተበጅቶለት ነበር።
የሽቦው አጥር እና የጥበቃ ማማ
ይኸ በሎወር ሳክሰኒ ግዛት ኖየ ዳርካው በተባለ ቦታ በሽቦ አጥር የተበጀ የምሥራቅ እና ምዕራብ ጀርመን ድንበር ቅሪት ነው። በቦታው ረዥም የጥበቃ ማማ ጭምር ይገኛል።
የሽቦው አጥር
አንድ ሺሕ አራት መቶ ኪሎ ሜትር ገደማ የሚረዝመው የቀድሞዎቹ ምሥራቅ እና ምዕራብ ጀርመን ድንበር የብረት አጥርን ያካተተ ነበር። በአንዳንድ ቦታዎች ለግንቡ ማጠናከሪያ ተጨማሪ የሽቦ አሊያም የብረት አጥር ነበር። ይኸ በሎወር ሳክሰኒ ግዛት ኖየ ዳርካው በተባለ ቦታ በሚገኝ አነስተኛ ቤተ መዘክር ውስጥ የተቀመጠ ነው።
ግንብ ለ40 አመታት የዘጋው ዕድሜ ጠገብ ድልድይ
ይኸ በሔሰ ግዛት የምትገኘው ፍሊፕስታይል ከተማ በቱሪንጊያ ግዛት ካለችው ቬራ ለማገናኘት የተገነባ ድልድይ ነው። 225 ሜትር የሚረዝመው ይኸ ድልድይ ከ30 አመታት ገደማ በፊት ከወታደሮች በቀር የሚሻገርበት አልነበረም። የሔሰ እና የቱሪንጊያ ግዛት ሰዎችን ለማገናኘት ከ650 አመታት በፊት ይገንባ እንጂ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ግብሩን ተነጥቆ በስሙ ብቻ ቀርቶ ነበር።
የግንቡ ቅሪቶች
በሳክሰኒ አንሐልት ግዛት በምትገኘው የስታፔልቡርግ መንደር ግንቡ ፈርሶ ዜጎች እንዳሻቸው መንቀሳቀስ የተፈቀደላቸው በጎርጎሮሳዊው ኅዳር 11 ቀን 1989 ዓ.ም. ነበር። ይኸ ማለት ግንቡ በበርሊን ከፈረሰ ከሁለት ቀናት በኋላ መሆኑ ነው።
የሐርዝ ደንን የሚያቋርጠው የድንበር ቁጥጥር መንገድ
ይኸ በሐርዝ ደን ውስጥ አቋርጦ የሚያልፈውን የምሥራቅ እና የምዕራብ ጀርመን ድንበር ወታደሮች ቁጥጥር የሚያደርጉበት መንገድ ነው። ዛሬ አገር ጎብኚዎች በዚሁ መንገድ መመላለስ ያዘውትራሉ።