1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የምዕራባዉያን ግፊትና ኢትዮጵያ

ሰኞ፣ መጋቢት 6 2013

የዩናይትድ ስቴትሱ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከን ባለፈዉ ሮብ ለሐገራቸዉ ምክር ቤት እንደነገሩት በጉዳዩ ላይ ከኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ጋር መነጋገራቸዉን ገልጠዋል።በዉይይታቸዉ ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ ሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ  (ሕወሓት) ያደርሳል ያሉትን ችግር እንደሚረዱ አስታዉቀዋልም።

https://p.dw.com/p/3qfEI
Iran - Atomabkommen | US-Staatssekretär Antony Blinken
ምስል Saul Loeb/AFP/Getty Images

ኢትዮጵያና የምዕራባዉያን ግፊት

ግንቦት 1983 የአዲስ አበባና የአስመራ አብያተ መንግሥታትን የተቆጣጠሩት የእስከያኔዎቹ አማፂ ቡድናት መሪዎች ጦርነት የገጠሙት ፍቅር-አድነታቸዉ፣ብልሐት-ትብብራቸዉ የምሥራቅ አፍሪቃ አብነታቸዉንም አስነግረዉ-ተነግሮላቸዉም ሳያበቃ ነበር።1990።ፍቅር፣ወዳጅነቱ ባፍታ በጥላቻና ዉጊያ መለወጡ እንደብዙዎቻችን ሁሉ ያስገረመዉ የኒዉስ ዊክ ጋዜጣኛ የኤርትራዉን ከፍተኛ ባለስልጣን «ለምን?» ዓይነት ብሎ ጠየቀ።መለሱ ሰዉዬዉ «አሁን ጠላቶች የሚሉን፣ወዳጆች ይሉን የነበሩት ራሳቸዉ ናቸዉ» እያሉ።ከመጋቢት 2010 ጀምሮ የኢትዮጵያን ተስፋ፣ የአፍሪቃ አብነቷን፣ የመሪዋን ለዉጥ አራማጅነት ሲያደንቁ፣ሲያወድሱ፣ ሲደግፉ፣ ሲሸልሙ የነበሩት ምዕራባዉያን መንግስታት አሁን በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ጫና፣ ማስጠንቀቂያ፣ማዕቀቡን እያዥጎደጉት ነዉ።ታሪክ እራሱን ደገመ እንበል? ወይስ ሌላ? ሰበብ ምክንያቱን እየጠቃቀስን ላፍታ እንጠይቅ?

የዋሽግተን-ብራስልስ አደባባዮች የኢትዮጵያ መንግስትን የሚደግፉና የሚቃወሙ ሰልፈኞች ሲፈራረቁባቸዉ፣ የየፖለቲካ፣ ዲፕሎማሲ ቢሮዎቻቸዉ የኢትዮጵያን መንግስት የሚቃወሙና የሚያሳስቡ መግለጫዎች ሲንቆረቆርባቸዉ ሳምንቱ አለፈ።

አዲስ አበባም ለዋሽግተን-ብራስልሶች መግለጫ አፀፋ በመስጠት፣ መቀሌ ዲፕሎማቶችን በማስተናገድ ሲባትሉ ነበር።የሁሉም ምክንያት ትግራይ ዉስጥ በተደረገዉ ጦርነት ሰላማዊ ሰዎች ግፍ ተዉሎባቸዋል መባሉ ነዉ።

የዩናይትድ ስቴትሱ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከን ባለፈዉ ሮብ ለሐገራቸዉ ምክር ቤት እንደነገሩት በጉዳዩ ላይ ከኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ጋር መነጋገራቸዉን ገልጠዋል።በዉይይታቸዉ ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ ሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ  (ሕወሓት) ያደርሳል ያሉትን ችግር እንደሚረዱ አስታዉቀዋልም።

ይሁንና ዉጪ ጉዳይ ሚንስትሩ በተለይ ምዕራባዉ ትግራይ ዉስጥ ተፈፅሟል ያሉት የዘር-ማፅዳት ግፍ መቆም አለበት ባይናቸዉ።

EU flags at half-staff after terror attacks in Vienna, Nice
ምስል picture alliance / Kyodo

«ከፀጥታ ጋር በተገናኘ ባሁኑ ወቅት ሁለት ፈተናዎች አሉ።አንዱ፣ እንደምታዉቁት እዚያ (ትግራይ) የሚገኘዉ የኤርትራ ኃይል ነዉ።የአጎራባች ክልል ኃይልም አለ።የአማራ።መዉጣት አለባቸዉ።እና ትግራይ ዉስጥ የሕዝብን ሰብአዊ መብት የማይጥስ ኃይል ያስፈልገናል፣ ወይም ምዕራብ ትግራይ ዉስጥ እንዳየነዉ የዘር ማፅዳት ርምጃ መቆም አለበት።ሙሉ ተጠያቂነት መኖርም አለበት።እዚያ የተፈፀመዉን የሚያጣራ ገለልተኛ መርማሪ ያስፈልገናል።ሐገሪቱ በፖለቲካዉ ወደፊት ትቀጥል ዘንድ የሆነ ዓይነት ሒደት፣ የዕርቅ ሒደት ያስፈልገናል።ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ ኖቤል የተሸለሙ ተስፋ ያጫሩ ነበሩ።አሁን እርምጃ ሊወስዱ ይገባል።ትግራይ የሚኖረዉ የራሳቸዉ ሕዝብ የሚያስፈልገዉና የሚገባዉን ከለላ ማግኘቱን ማረጋገጥ አለባቸዉ።»

የአዉሮጳ ሕብረት ምክር ቤትም በማግስቱ ሐሙስ ባወጣዉ ባለ 24 ነጥብ መግለጫ ትግራይ ዉስጥ ይፈፀማል ያለዉ የሠብአዊ መብት ጥሰት፣ ግድያና የሴቶች መደፈር እንዲቆም ጠይቋል።ኢትዮጵያን የአዉሮጳ ሕብረት «ስልታዊ ወዳጅ» ያለዉ መግለጫ ኢትዮጵያ የገጠማት ዉስብስብ ችግር ለአካባቢዉም ትልቅ እድምታ አለዉ ይላል።

ብሊንከን የሰጡትን መግለጫ የራሳቸዉ የዉጪ ጉዳይ ሚንስትሩና የፕሬዝደንት ጆ ባይደን ቃል አቀባዮች በየፊናቸዉ አስተጋብተዉታል።ባለፈዉ አርብ ደግሞ ዩናይትድ ስቴትስ ለኢትዮጵያ ትሰጥ የነበረዉን የፀጥታ ድጋፍ ማቋረጥዋን  የአሜሪካ ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር አስታዉቋል።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይን ለዉጥ አራማጅ፣የሰላም ጠበቃ፣ የአፍሪቃ አብነት፤ ኢትዮጵያን የሠላም፣የዴሞክራሲ የመቻቻል ተምሳሌት እያሉ ሲያደቅ፣ ሲደግፍ፣ ሲረዳ የነበረዉ ምዕራቡ ዓለም በኢትዮጵያ መንግስት ላይ የዲፕሎማሲ ግፊትና ጫናዉን ያጠናከረዉ በርግጥ ትግራይ ዉስጥ ተፈፀመ የተባለዉ ግፍ መፈፀሙን አረጋግጦ ነዉ? ዉይስ ሌላ።

Äthiopien Abiy Ahmed
ምስል Amanuel Sileshi/AFP

በኪል ብሪታንያ ዩኒቨርስቲ የሕግ ረዳት ፕሮፌሰር አወል ቃሲም አሎ እንደሚሉት ምዕራባዩኑ ጫና ግፊታቸዉን ያጠናከሩት ያለምክንያት አይደለም።                                        

የኢትዮጵያ መንግስት ግን ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጓች ተቋማትን ዘገባ፣ የምዕራባዉያን መንግስታትን ማሳሰቢያ አልተቀበለዉም።የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናትና ደጋፊዎቹ እንደ አፀፋ ስልት የተጠቀሙት ደረሰ የተባለዉን ጥፋት ከማጣራት ይልቅ ዘገባዉን ያቀረቡትን ድርጅቶች፣ የድርጅቶቹን መግለጫ ጠቅሰዉ የዘገቡ መገናኛ ዘዴዎችን ማበሻቀጥ ምዕራባዉያን መንግስታትን መቃወም ነበር።

የዩናይትድ ስቴትስ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትርና የአዉሮጳ ሕብረት ምክር ቤት መግለጫ ባለፈዉ ሳምንት ከመሰማቱ በፊት በነበረዉ ሳምንት የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት በጉዳዩ ላይ ተነጋግሮ ነበር።እርግጥ ነዉ ምክር ቤቱ የጋራ መግለጫ አላወጣም።መግለጫ ያለወጣዉ ሩሲያና ቻይናን የመሳሰሉ የምክር ቤቱ ቋሚ አባላት በመቃወማቸዉ እንጂ ከዚሕ ቀደም «የአፍሪቃ ጉዳይ በአፍሪቃዉያን ይፈታ» የሚሉት ኬንያንና ኒዠርን የመሳሰሉት አፍሪቃዉያን የምክር ቤቱ ተለዋጭ አባላት በመቃወማቸዉ አልነበረም።

ከዑይግሁሩ ሙስሊሞች እስከ ሆንግኮንግ ሕዝቦችዋን በመርገጥ፣ ማፈን መጨቆን፣ ክሪሚያን በኃል ከመያዝ እስከ ሶሪያ፣ አሌክሲ ናቫልኒን የመሳሰሉ ተቃዋሚዎችን ከመመረዝ-እስከ ማሰር የሚወገዙ፣ የሚከሰሱ፣ በማዕቀብ የተቀጡት የቤጂንግ እና የሞስኮ መንግስታ መግለጫዉን የተቃዉመዉት በርግጥ ኢትዮጵያን ፈቅደዉ ነዉ? አናዉቅም።የምናዉቀዉ የኢትዮጵያ የዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ባለፈዉ ሳምንት ማክሰኞ የሰጡትን መልስ ነዉ።

ዋሽግተን ዉስጥ ባለፈዉ ሳምንት  አሜሪካ ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር ፅሕፈት ቤት አጠገብ የተሰለፉትን ኢትዮጵያዉያንን ካስተባሩት አንዱ አቶ ከባዱ ሙሉቀን በላቸዉም አሜሪካ አቋሟን እንድታስተካክል ነዉ የጠየቁት።የአዉሮጳ ሕብረትን አቋም በመቃወም ሮብ ብራስልስ አደባባይ የወጡት  ሰልፈኞች አስተባባሪ ጋዓስ አሕመድም ደገሙት።

Tigray-Konflikt | Militär Äthiopien
ምስል Ethiopian News Agency/AP/picture alliance

 የኢትዮጵያ መንግስት ማስተባበያ፣የደጋፊዎቹ ተቃዉሞ ሰልፍና አቤቱታ በርግጥ ክፋት የለዉም።መደረግ የነበረበት ግን ዶክተር አወል እንደሚሉት አልተደረገም።የምዕራባዉያን መንግሥታትም ሆኑ ዓለም አቀፉ ተቋማትና ድርጅቶች  የኢትዮጵያ መንግስት ሕግና-ሥርዓት በመጣስ የወነጀለዉን የቀድሞዉን የትግራይ ገዢ ፓርቲ ሕወሓትን የሚደግፍ መግለጫ በግልፅ አላወጡም።እንዲያዉም የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ኮሚሽንና ሌሎች የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ትግራይ ዉስጥ ተፈፀመ ላሉት የሰብአዊ መብት ጥሰት ተጠያቂ ካደረጓቸዉ ኃይላት አንዱ ሕወሓት ታጣቂ ቡድን ነዉ።

የዩናይትድ ስቴትሱ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከንም የጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ሥጋት ይገባኛል ነዉ-ያሉት።«ጠቅላይ ሚንስትሩ ( ዐብይ አሕመድ) ሥለ ሕወሓትና እርምጃዎቹ ያላቸዉን ሥጋት በጣም እረዳለሁ።ይሁንና ትግራይ ዉስጥ ዛሬ ያለዉ ሁኔታ ተቀባይነት የለዉም።መቀየር አለበት።»

የኒዉዮርክ፣ ዋሽግተን፣ብራስልስ ዲፕሎማቶች ጫናና ግፊት በግልፅ በተሰማበት ባለፈዉ ሳምንት በአዲስ አበባ  ከ50 የሚበልጡ ሐገራት አምባሳደሮች ወይም ተወካዮች መቀሌን ጎብኘተዋል።ከትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር ባለስልጣናት ጋር ተነጋግረዋልም።

እስከ ጉብኝት ዉይይቱ ድረስ የኢትዮጵያ መንግስትና ደጋፊዎቹ  በጥሞና ቢያስተነትኑት ምናልባት ከማንም በላይ ለራሳቸዉ የሚጠቅሟቸዉን ወቀሳና ትችቶች ከመቀበል ይልቅ ፌንጥ ያሉት ተቺዎቹን፣ አጥኚዎችን፣ መካሪዎችን፣ ገለልተኛ መገናኛ ዘዴዎችንም ጭምር እንደእዉር ተርብ መናደፉን ነዉ።

ማሳሰቢያ፣ ጫና፣ ምናልባትም የዕቀባ እርማጃዉ ሲጠናከር የኢትዮጵያ መንግስት የገባቸዉ ቃሎች፣ ከዲፕሎማቶቹ የመቀሌ ጉብኝትና ዉይይት ጋር ተዳምሮ ታዛቢዎች እንደሚሉት፣የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ለተገቢዉ እርምጃ ተገቢዉን አፀፋ የመስጣቸዉ ምልክት ሊሆን ይችላል።ምናልባት ብሊከን «መቀየር» አለበት ያሉት የትግራይ ሁኔታን ለመቀየር የመጀመሪያዉ እርምጃ ሊሆንም ይችላል። ዶክተር አዉል እንዳሉት ደግሞ ቢዘገየም መሻሻል የመኖሩ ምልክት ነዉ።ግን በቂ አይደለም።

በቂ ለማድረግ ጅምሩን ማጠናከር ከማንም በላይ የሚጠቅመዉ ለኢትዮጵያ መሪዎችና ለኢትዮጵያዉያን ነዉ።ኢትዮጵያ፣ ትግራይ ብቻ ሳይሆን ሌሎች አካባቢዎችም ሳምንት-በሳምንት ሰዎች ይገደሉ፣ ይፈናቀሉባታል።ከግብፅና ሱዳን ጋር የገጠመችዉ ዉዝግብ ወዴት እንደሚወስዳት ለመገመትም አዳጋች ነዉ።ከሁሉም በላይ የመንግስቷ በጀት ሳይቀር በምዕራባዉያን ገንዘብ የሚደጎም ደሐ ሐገር ናት።

Tigray-Konflikt | Flucht in den Sudan
ምስል ASHRAF SHAZLY/AFP

ዘገቦች እንደሚጠቁሙት ኢትዮጵያ ከአዉሮጳ ሕብረት ብቻ በዓመት ባማካይ 214 ሚሊዮን ዩሮ የልማት ርዳታ ታገኛለች።ዩናይትድ ስቴትስ ለኢትዮጵያ በየዓመቱ የምትሰጠዉ ርዳታ ወደ 1 ቢሊዮን ዶላር ይደርሳል።የዚች ሐገር መሪዎች፣ የምዕራቡም-የምሥራቁም የፖለቲካ አዋቂ እንደሚመክረዉ የሚመሯትን ሐገር፣ ሕዝብና በዓለም ያላትን ሥፍራ ጠንቅቀዉ ሊያዉቁ ይገባል።አለበለዚያ እናንተዉ አወደሳችሁ እናንተዉ አወገዛችሁን ብሎ ዲፕሎማሲ የብልሕ መሪዎች ሊሆን አይችልም።

ነጋሽ መሐመድ 

እሸቴ በቀለ